ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። የሀገሪቱ አምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎችም አሏት።
ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪው ያላትን ይህን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች። በዓይነትም ሆነ በብዛት የሚታወቁት እነዚህ በርካታ የዘርፉ ችግሮች፡- የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፡ – ከሀገሪቱ አቅምና ከችግሮቹ ስፋት አንፃር ግን መፍትሔዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ስላላቸው ሚና ይፋ ባደረገው ጥናት ላይ እንደተመለከተው፣ ምንም እንኳ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተለየ የማበረታቻና ድጋፍ ፓኬጆች አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፡- አብዛኛው የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብት የመጀመሪያ ምርጫው አምራች ኢንዱስትሪው ሳይሆን የንግድ፣ የሪል እስቴትና የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው። ለዚህ ደግሞ ጥናቱ በምክንያትነት የጠቀሳቸው ቀድመው በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች በብዙ ችግሮችና ማነቆዎች ምክንያት ውጤታማ ባለመሆናቸው ወደ ዘርፉ መግባት ለሚፈልግ ባለሀብት ጥሩ አርአያ መሆን አለመቻላቸውን እና በንግድና አገልግሎት ዘርፎች የሚገኘው ትርፍ በጣም የተጋነነና ሳቢ መሆኑን ነው።
ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ ነው። የኃይል አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ተደጋግመው የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው። አብዛኞቹ የማምረቻ ዘርፎች ከ25 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ጥሬ እቃዎቻቸውን የሚያገኙት ከውጭ ሀገራት በማስገባት ነው። አምራቾቹ ይህን ከውጭ የሚገባ ጥሬ እቃ በበቂ መጠን ለማግኘት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት ስላለባቸው የምርት ግብዓቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ እንዳያገኙና በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ያደርጋቸዋል።
ከውጭ የሚገቡ የምርት ግብዓቶች አቅርቦት አስተማማኝ አለመሆንም ሌላው የዘርፉ ችግር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ክስተቶች ግብዓቶቹ በበቂ ሁኔታ እንዳይገኙ ማድረጋቸው በአምራቾች ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። የገበያ እድል እጦትም አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት ሆኗል። ለአንዳንድ ምርቶች በቂ የሆነ የሀገር ውስጥ ገበያ አማራጭ አለመኖር ኢንዱስትሪዎቹ በአቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል። የብድር አቅርቦትም ሌለው የዘርፉ ችግር ነው። አምራቾች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው የምርት ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ አሟልቶ ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ይቸገራሉ።
በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የሰባት በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን በቀጣይ 10 ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን ከ55 በመቶ ያልበለጠውን የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል።
የግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ የሰው ኃይል፣ የቦታ፣ የኃይል፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮችን በአስተማማኝነት ለመፍታት የአምራች ዘርፉን አቅም የሚያሳድግ የአቅም ልማት ስትራቴጂ ማዘጋጀትና መተግበር አንዱ ወሳኝ የመፍትሔ ርምጃ ተደርጎ ተለይቷል። በዚህ መነሻነትም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር የዘርፉን ችግሮች በመለየት ወደ መፍትሔው የሚያደርሱ አሰራሮችን የሚመራ የአምራች ዘርፍ የአቅም ልማት ስትራቴጂ አዘጋጅቷል።
ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እድገት ዋና ባለድርሻ እንዲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያላቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ መንግሥት ለባለሃብቶች በቂ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ፣ ለባለሀብቱ የተፈቀዱ ማበረታቻዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪው በግል ባለሀብቶች ተመራጭ ዘርፍ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንዲያግዝ ታስቦ የተዘጋጀ የአሰራር መመሪያ ነው።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ዓባይ እንደሚገልፁት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ያስፈለገው በመንግሥትና በግል ተቋማት ያለው ተቋማዊ አቅም (የሰው ሀብት፣ አደረጃጀት፣ የአሠራር ሥርዓት፣ መሠረተ ልማት) በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ነው። ስትራቴጂው የአምራች ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት የዘርፉን ችግር በሚገባ ተረድተው የተሟላና ውጤታማ የሆነ ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም ዘርፉ ያለበትን አጠቃላይ ደረጃ ለመገምገም ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ስትራቴጂው ትልቅ አቅም ያላቸውን አምራቾች ለመሳብ፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት፣ የዘርፉ ተቋማዊ አቅም ሙሉ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ፣ ለውጦችን ቀጣይና ዘላቂ ለማድረግ እና በዘርፉ ያለውን የእውቀት፣ የአመለካከትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ያግዛል። በአጠቃላይ ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው የምጣኔ ሀብት ድርሻ ውስጥ ትልቁን ሚና እንዲወጣ የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር እገዛ እንደሚያደርግና በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ በማምረቻው ዘርፍ የተቀመጠውን መዋቅራዊ ሽግግርን የማሳካት እቅድን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አቶ ጥላሁን አመልክተዋል።
‹‹ወደፊት የግል ዘርፉ በአምራች ኢንዱስትሪው ትልቁን ሚና እንዲጫወት ይፈለጋል። ስለሆነም ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ የራሱን አደረጃጀት አጠናክሮ እንዲሰራ ማድረግን ጨምሮ የዘርፍና የሙያ ማኅበራት እንዲጠናከሩ፣ ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት፣ የቴክኖሎጂ አስተዳደር ብቃት እንዲያድግ እና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር እንዲጠነክር ትልቅ ሚና ይኖረዋል›› ይላሉ። በስትራቴጂው ትግበራ በዘርፉ ቁልፍ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በእውቀት ላይ የተመሠረተና ኢንዱስትሪውን መሠረት ያደረገ ድጋፍ በሚሰጡበት ሂደት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፣ ስትራቴጂው የአመራር አቅምን በማጎልበት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት እንደሚረዳ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የብዙ ዘርፎችን ተሳትፎ የሚፈልግ በመሆኑ ስትራቴጂው ይህን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ለማቀናጀት በጎ ሚና ይኖረዋል። የስትራቴጂው ትግበራና ስኬት ከዘርፎች ቅንጅት በተጨማሪ የማኅበረሰብ ንቅናቄ ይፈልጋል። ‹‹የኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ለኢኮኖሚ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት ነው›› የሚሉት አቶ ታረቀኝ፣ ስትራቴጂውን የዘርፉን ችግሮች በመለየትና መፍትሔዎችን በማመላከት የኢኮኖሚውን ችግሮች ለማቃለል እገዛ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
የስትራቴጂዎች መዘጋጀት ችግሮችን ለማቃለል ሁነኛ ግብዓት እንደሚሆን የሚናገሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ ትግበራውም ከዝግጅቱ የበለጠ ትኩረትና ክትትል የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹ብዙ ጊዜ ‹በዚህ ጊዜ ይህን እናከናውናለን› ብለን እናቅዳለን፡- ‹እንዴት ይከናወናል/ይሳካል?› የሚለው ጥያቄ ግን አጥጋቢ ምላሽ አያገኝም። አንድ የእቅድ ዘመን ያለስኬት አጠናቅቀን፣ ሁለተኛውን የእቅድ ዘመን ስንጀምር በመጀመሪው የእቅድ ዘመን እቅዱ ያልተሳካበትን ምክንያት ለይቶ ችግሩን ሊፈታ የሚችል አቅጣጫ በበቂ መጠን ማስቀመጥ ያስፈልጋል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
በስትራቴጂዎች ዝግጅትና ትግበራ ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶች ችግሮች ሳይፈቱ ለበርካታ ዓመታት እንዲቀጥሉ ምክንያት እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ የኢንዱስትሪ ፖሊሲውን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ‹‹ነባሩን የኢንዱትሪ ፖሊሲ በዝርዝር ስንመለከተው ይዘቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን የፖሊሲውን ዓላማ ሊያሳኩ የሚችሉና ከፖሊሲው ቀጥለው መውጣት የነበረባቸው ስትራቴጂዎች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተው አለመተግበራቸው ትልቅ ጉድለት ነበር። ይህም ብዙዎቹን እቅዶች አየር ላይ የቀሩና የተንሳፈፉ ያደርጋቸዋል።›› ብለዋል።
‹‹ፖሊሲዎች ከተዘጋጁ በኋላ የፖሊሲዎቹን ማስፈፀሚያዎች ማዘጋጀትና መተግበር ያስፈልጋል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለእዚህም የማስፈፀም አቅምን ፈትሾ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚስፈልግ ይናገራሉ። ‹‹ኢንዱስትሪ እውቀት ይፈልጋል፡- ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ በእውቀት የታገዘ አሰራር መከተል ያስፈልጋል። ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና መተግበር ለዚህ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› ይላሉ። በትግበራ ያልታገዘ የስትራቴጂዎች ዝግጅት ፋይዳ እንደሌለው የሚገልፁት አቶ መላኩ፣ የአምራች ዘርፍ የአቅም ልማት ስትራቴጂ መዘጋጀቱ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ስትራቴጂዎች ወደ መፍትሔ የሚወስዱ መንገዶች በመሆናቸው መፍትሔው ላይ ለመድረስ ስትራቴጂዎችን በሙሉ አቅም መተግበር ያስፈልጋል። ችግሮችን ለመፍታት የችግሩን መነሻና መድረሻ መረዳት ያስፈልጋል። መፍትሔ የሚገኘው በስትራቴጂዎች ትግበራ ነው። የስትራቴጂው ዝግጅት ብዙ ገንዘብና የሰው ኃይል ተመድቦ የተከናወነ በመሆኑ ሰበብና ምክንያት መፍጠር ሳያስፈልግ ለትግበራው ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል። ስትራቴጂዎች ለተሻለ አፈፃፀም እገዛ ያደርጋሉ ማለት እንጂ ከችግር ፍፁም የፀዱ ናቸው ማለት እንዳልሆነና በሂደት የሚደረጉ ማሻሻያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያመለክታሉ።
ከዚህ በተጨማሪም አቶ መላኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ መሰናክሎች እንዳሉበትና የሀገሪቱ አቅምና የገበያ ፍላጎትም ከዘርፉ አሁናዊ አፈፃፀም በላይ እንደሆነ ጠቁመው፣ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችን ዘላቂ ለማድረግ ለኢንዱስትሪዎች የሚደረጉትን ድጋፎች በብዛትም ሆነ በጥራት መጨመር እንደሚገባ በአፅንዖት ይገልፃሉ።
የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት የሚመጣጠኑ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉን ችግሮች መፍታት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሔ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የአምራች ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የዘርፉ አጠቃላይ አሰራር የሚመራባቸውን አስፈላጊ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016