ገና ሳይወለድ፤ ከእናቱ ሆድ ውስጥ ቁልቁል ተዘቅዝቆና በውሀው ተዘፍቆ ሲንሳፈፍ በሀሳብ ተውጦ ነበር። ከሆድ ውስጥ ሳለ ጀምሮ ከውጭ የሚከናወነውን ሁሉ የሚመለከት፣ የሚሰማ፣ የሚያስብ፣ የሚናገር፣ ሁሉንም ነገሮች አስቀድሞ የሚያውቅ በእውቀት ባህር የጠለቀ ጉደኛ ህጻን፤ ከአንዲት ምስኪን እናት ሆድ ውስጥ ነበር። እናት ሆዷ ገፍቶ የምጧ ሰዓት በደረሰ ጊዜም አይኗን በአይኗ ለማየት ተመኝታ ነበር።
ከብዙ ጭንቅ በኋላ የምታገኘውን ልጇን ታቅፋ ለመሳም ብትጓጓም እርሱ ግን “እምቢ አልወለድም” ሲል አንደበቱን አውጥቶ ተናገረ። የዚህን ህጻን ልጅ ድምጽ የሰማችው እናት ብቻ አነበረችም፤ ታላቁ ብዕረኛ አቤ ጉበኛ በትክክልም ሰምቶት ነበር። ጨቅላው ህጻን አልወለድም ሲል እሪ ለማለቱ እናት በውሉ ያላጤነችው፤ አስቀድሞ የተመለከተው አስፈሪ ነገር አለና ነው። እያለቀሰ ተወልዶ እያለቀሰ በመኖር፤ በለቅሶ ተጀምሮ በለቅሶ የሚያልቅን ሕይወት ለማየት አልፈለገም።
ልጄ እባክህን እሺ በለኝና ተወለድ። እምቢ አልወለድም! በእናቱ ተማጽኖ በልጁ እምቢታ መሃል ሆኖ አቤ ጉበኛ የሁለቱንም የልብ ትርታ አደመጠና “አልወለድም” ሲል ለመጻፍ ብዕሩን አነሳ። ያኔ ከዛሬ 61 ዓመታት በፊት። ገና በቅጡ ሳይከፈቱ በእንባ የረጠቡትን የህጻኑን አይኖች እየተመለከተ ልቡ በሀዘን በተሰበረ ጊዜ። ህጻኑም የሚረዳውን ሰው በማግኘቱ ደስ ብሎት የልቡን ከልቡ ያጫውተውና ይነግረው ጀመር። አልወለድም ይናገራል አቤም ይጽፋል። ብዕር የምናብ ህቅታ ብቻም ሳይሆን የልብን የደም ዕንባ ማንቢያ የደስታ ማጣጠሚያና የሀዘን መሸሸጊያም ነው። አቤ ጉበኛ ተወልዶ ካደገና ከጎለመሰ በኋላ መልሶ ግን አልወለድም ሲል እርሱም እንደ ህጻኑ ለመሆን ተመኘ። እናም አቤ በህጻኑ ውስጥ፤ ህጻኑም በእናቱ ሆድ ውስጥ ሆነው “አልወለድም” አሉ።
አልወለድም ማነው? አልወለድም የመጽሐፉ ርዕስና የዋና ገጸ ባህሪውን ውክልና የወሰደ የታሪኩ ተራኪም ጭምር ነው። ከእናቱ ሆድ ውስጥ ሆኖ አልወለድም የሚል ሞገደኛ ህጻን። በብዙ መጽሐፍት ላይ እንደምናውቃቸው አይነት ገጸ ባህሪያት ቁመቱ ረዘም ብሎ… ፊቱ ሾጠጥ ያለ…ባለ ግራጫ ካኪ ሱሪ…አዳፋው ኮቱ…በሳንቃው ደረቱ…ችፍ ችፍ ባለው ጺሙ…ጸጉሩ ተንጨፍርሮ..ከነበልባል አይኖቹ በታች ስልክክ ያለው አፍንጫው….ጉራማይሌ ጥርሱ…የሚሉ ምስል ከሳች ማንነቶች የሉትም።
እንደሌሎቹ ህጻናት የመጠሪያ አባት ስም የለውም። አባቱም ማን እንደሆነ አይታወቅም። እዚህ ተወለደ እዚያ አደገ የሚባል ነገርም የለውም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚያነሳቸው ሀሳቦች የራሳቸው የሆኑ የገሀዱ ዓለም ውክልና አላቸው። ምንና ስለማን እያወራ ነው፤ ብለን ስንጠይቅ ከፊታችን፣ ከበስተጀርባችን አሊያም ከግራና ቀኝ ምላሾቹን እናገኛቸዋለን። ሁላችንም ግን አንድ አይነት ምላሽ ተመሳሳይ ምስል እንመለከት ይሆናል። በሚያጋጥመን፣ በምናየው፣ በምናውቀውና በምንረዳው መጠን ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን በአልወለድም ውስጥ የኛ የሆነ ቢያንስ አንድ ጥያቄና አንድ እውነት አለ። የአልወለድምን መልክና ቁመና ደራሲው ለኛው የተወውም ለዚሁ ነው።
አንድ በሆድ ያለ ጨቅላ ህጻን እንዴት ይህን ያህል በእውቀት ይራቀቃል…እንዴትስ አንደበተ ጣፋጭ የቋንቋ ፈላስፋ ይሆናል…ህጻኑ አልወለድም በማይመስል ነገር ውስጥ የኛን የሕይወት እውነታ የሚናገር ነብይ፣ አስተማሪ፣ ጠቢብና እንዲሁም ፖለቲከኛም ጭምር ነበር። እናት በሆዷ የተሸከመችው የዚህ ጉደኛ ህጻን ነገር በእጅጉ አስደንቋታል። ግራም አጋብቷታል። የምትሰማው ድምጽ አንዳች መንፈስ እንጂ የልጇ ድምጽ ስለመሆኑ ማመን ከብዷታል። እሷ ለመውለድ በምጥ ስትታገል እሱ ግን “አልወለድም” ሲል በእምቢታው ጸና። እኛም እስቲ ከገጽ ወደ ገጽ እየዘለልን የሚለውን እናድምጠው።
“ታዲያ ለምን አትወለድም?” አለች። “ተወልጄ በችግር መሰቃየት አልፈልግም።” “እኔ በተቻለኝ መጠን አሳድግሃለሁ።” “ሊያኖረኝ የሚችል ሀብት አለሽ?” “እንደዚሁ ለምኜም ቢሆን አሳድግሃለሁ።”
“ሞት ይሻላል!…ልመናን ተማምኜ ነው የምወለድልሽ? በገዛ ሀገርሽ ላይ የምትችይውን ሰርተሽ በመኖር ፈንታ እንዴት ልመናን ተስፋ አድርገሽ ትኖሪያለሽ? ያንቺ በዚህ ሁኔታ መጎሳቆል አንሶ ደግሞ ማደሪያ ሌለው ልጅ ለምን ትወልጃለሽ?”
………
እሺ መሬት አለሽ?” “የለኝም”
“ቤት አለሽ?” “የለኝም”
“ታዲያ ምን አለሽ?”
“ምንም የለኝም።”
……..
“ታዲያ ድህነትን፤ በሽታንና ድንቁርናን ልታወርሺኝ
ነው ተወለድ የምትይኝ?”
“እድልህን እንዴት ታውቀዋለህ ልጄ?”
“ቀማኞችና ነፍሰ ገዳዮች፤ እንዲሁም የነፃነት ጠላቶች በሰለጠኑበት ደግሞ ምን እድል አለ? የድሆችን ልጆች የሚጠብቃቸው የወላጆቻቸው መከራና ችግር ብቻ ነው። መከራና ችግርን ከድሆች ትከሻ ለማውረድ እንደኔ ከሆድ ውስጥ ጀምሮ ለመብትና ለነፃነት መሟገት ያስፈልጋል።”
እያለ ሙግቱን ይቀጥላል። ይህ የአልወለድም ታሪክ ብቻ አይደለም። ገና ወደዚህች ምድር ሳንመጣ አስቀድሞ፤ በእናቶቻችን ሆድ ውስጥ ሳለን ልክ እንደ አልወለድም የወደፊቱን እጣ ፈንታችንን የማወቅና የመጠየቅ እድሉ ቢገጥመን፤ የአብዛኛዎቻችን ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ይሄው ነው። አቤ ጉበኛ በምናብ እረቆ፤ በእውቀት ጠልቆ የወከለው ይህንን ገጸ ባህሪንም ሆነ ቅኔ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፤ ወርቁን ከምናገኝበት ከርሰ ምድር ላይ ለመድረስ ብዙ ማወቅንና ያወቅነውንም መቆፈርን ይጠይቃል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አልወለድም ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡንም ከተኛበት የጦፈ እንቅልፍ ውስጥ ቀስቅሶ ለማንቃት ሲጥር እንመለከተዋለን። ነገር ግን መጽሐፉ በወቅቱ ለነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ዳፍ ሆነ። ሀሳቡን ያልወደዱት አካላት ደራሲውን ከነመጽሐፉ ጠምዝዘው መስቀለኛው የፖለቲካ መንገድ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ። አልወለድም አስቀድሞ በሆድ ውስጥ ሳለ የተናገራቸው ትንቢቶች ይፈጸሙ ጀመረ። “አልወለድም” ዘውዳዊውን ሥርዓት ለመናድ የሚታገል ‘ሽብርተኛ’ ነው ሲባል ተፈረደበት። ከዚህም የተነሳ በውስጡ ከያዘው ታሪክ በተጨማሪ፤ መጽሐፉ እራሱ አንድ መጽሐፍ የሚወጣው ሌላ ታሪክ ከበስተጀርባው ተፈጠረበት።
“አልወለድም” ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ በ1955 ዓ.ም ለሕትመት በቅቶ ነበር። በመጀመሪያ የመጸሐፉን አካሄድ የገመገሙት የሳንሱር አባላት አጻጻፉን በግልጽ እንዲህ ነው ብሎ ለመወሰን ባለመቻላቸው በውስጣቸው ጥርጣሬን ቢያሳድርባቸውም በብዙ መፍጨርጨርም ቢሆን ለሕትመት እንዲበቃ ሆነ። ብዙም አልቆየም ሲብሰለሰል የከረመው ጉዳይ መጽሐፉ እየታተመ የስርጭት ጉዞውን ለመጀመር ሲሰናዳ ፈንድቶ ወጣ። መጽሐፉ ሕትመቱን እንዲያቆምና ከአንባቢያን እጅ እንዳይገባ ፈጣን የሆነ አስቸኳይ እገዳ ከላይ ተላለፈ።
እውነቱን ለመናገር የዚህ መጽሐፍ ይዘት በቀጥታ የዘውዳዊውን ሥርዓት ሥጋት አነበረም። በግልጽ የአማርኛ ቃላት ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚወረወሩ ፈንጂዎችንም የታጠቀ አይደለም። በሳንሱር አጥር ሾልኮ ቢያልፍም የሕትመትና የስርጭት ግንቡን ለመዝለል ግን አልተቻለውም። ዙፋናችን ሊደፈር ነው ያሉ ሹማምንትና አንዳንድ አካላት ‘የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው’ ሲሉ፤ እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው ተነሱ። ነገሩ ‘ምን ያለበት ዝላይ አይችልም’ ሆኖባቸው አሊያም ሌላ ምክንያት ቢኖራቸው እንጂ ጉዳዩስ ቅኔ ነበር።
ቅኔም ህልም እንደፈቺው ሆኖ፤ ሰሙ ተበርብሮ ቅኔው ሲፈታ፤ ምንም እንኳን ወርቁ ውስጥ ስለ ሥርዓቱ የሚናገሩ ነገሮች ቢኖሩትም የአልወለድም ሀሳብ ግን ከዚያም ያለፈ ነበር። ቅኔውም ሌላ ቅኔን ያዘለ በመሆኑ ወርቁ እያደር የሚገባ ነበር። በግልጽ እንዲህ ነው ባትልም ነገር ግን እንዲህ ለማለት አስበህ ነው በማለት በጠላትነት ፈረጁት። ምስቅልቅሉ የወጣ ግዙፍ ጨለማ የሕይወቱን ብርሃን ጋረደው።
1967ዓ.ም የዘውዳዊው ሥርዓት ማብቂያ የ”አልወለድም” መጽሐፍ መጀመሪያ ሆነ። ለአንዱ ሲጨልም ለአንደኛው ነጋ። ንጉሥ ሄደ ንጉሥ መጣ። ያለው እንዳለ ሆኖ፤ የያዘውን እንደያዘም ለ”አልወለድም” ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ከላዩ ተጭኖ ያዳፈነው የእገዳ ቀንበር ተነስቶ፤ ዳግም ለንባብ በቃ። በጊዜው በነጻነት የሚነበብበትን መብት ቢቸረውም የተፈላጊነቱና የተነባቢነቱን ያህል ዳግም የሕትመትን ደጅ እንዲረግጥ ግን አልተደረገም ነበር።
“አንድ ሰው ሲያልፍ ስለ መድሃኔአለም አለችውና /እናቱ መሆኗ ነው/ ሳንቲም ሲሰጣት ከእጅዋ ላይ ከነበረው ሌላ ሳንቲም ጋር ተጋጭቶ ቅጭል ሲል በሆዷ ውስጥ ከተኛሁበት ብንን አልሁ። ከእንቅልፍ መንቃት ብቻ አይደለም፤ ከድንቁርና ስሜትም ነቃሁ።” በማለት አልወለድም ገና በእናቱ ሆድ ውስጥ ሳለ የእርሱንና የተሸከመችውን እናት መጥፎ እጣ ፈንታ ትንቢታዊ በሆነ መልኩ ታየው። ገና ሳይወለድ ይህንን ስቃይ መታገልና ከባርነት ነጻ ለመውጣት መፋለሙን ጀምሮ ነበረ። ከተኛበት ነቃ። ህጻኑ አልወለድም የተፈጥሮን ህግ ሽሮ አልመወለድ የማይቻለው ነገር ነበርና በመጨረሻም ተወለደ። ነገር ግን የተወለደውም ለነጻነት ትግልና ለአርነት ነበር። ከተወለደ በኋላም አላማው እናቱ የተዘፈቀችበትን ረሀብንና ድንቁርናን አሸንፎ ከዘመናት ቀንበር እሷን ነጻ ማውጣት ነበር። ይህቺ ምስኪን እናት ኢትዮጵያ ነበረች፤ ህጻኑ አልወለድም ደግሞ ለሀገራቸው የብርሃንን ላምባ ለመለኮስ ከንፋሱ ጋር የሚታገሉ ልጆቿ ናቸው።
አልወለድም፤ መለወጥ አለብን! እስከመቼስ ነው በእንዲህ አይነት ሁኔታ የምንኖረው? የሚል የለውጥ መንገድ ጠራጊ ቢሆንም፤ ለውጥ ናፋቂነቱ ግን እንደ ነውጥ ናፋቂ አመጸኛ አስቆጠረውና በጨቋኞች መዳፍ ስር ወደቀ። አልወለድም ለምድራዊ ሰቆቃ ታልፎ ተሰጠ። ለእስር፣ ለእንግልት እና ለግርፋት ተዳረገ። ከዚህም የተነሳ በመጨረሻዋ ሰዓት በጥይት ግንባሩን ብለው ደፉት። እሱም እንዲህ አለ፤ “ወላጆቼ ወይም ፈጣሪዬ ወደዚህ ዓለም እንድመጣ ፈልገው እንደሆን አስቀድመው ወደ ዓለም መጥቼ ከዓለም እስክወገድ ድረስ በሰላም፤ በፍቅር፤ በደስታ ከሁሉም ይልቅ በነፃነት ልኖር የምችልበት እድል ማዘጋጀት ነበረባቸው። ይህንን ስላላገኘሁ ግን በአመፅ ተወልጄ በአመፅ ሞትሁ” በማለት ተራኪው ሞቱንም ያረዳናል።
የአልወለድም ታሪክና እውነት ትናንት በነበረ የሚታለፍ አይደለም። ደራሲው አቤ ጉበኛ ትናንትናን ብቻ ሳይሆን ዛሬና ነገንም ጭምር እያየ የጻፈው በመሆኑ ለአፍታ እንኳን የማይቀዘቅዝ የዘመናት ወላፈን ነው። አቤ “አልወለድም” ሲል በመጽሐፉ የወከለው ገጸ ባህሪ በርግጥም በራሱ የተመሰለ ነበር። ይህ መጽሐፍ የእርሱን ውስጣዊ ማንነት በማውጣት በታሪክ ጎልቶ እንዲወጣ ቢያደርገውም በ1968 ዓ.ም የታተመው “ፖለቲካና ፖለቲከኞቹ” የተሰኘውን መጽሐፍ ጨምሮ በተመሳሳይ መልኩ ጭቆናና ድንቁርናን የተጋፈጠባቸው ሌሎች ሥራዎችም አሉት።
በዘውዳዊ ሥርዓት ወቅት የጀመረውን ወርቃማ የብዕር ትግል በደርግም አልተገታም ነበር። በሁለቱም ሥርዓቶች ለእስራትና ለእንግልት ተዳርጓል፤ በተለይ ደግሞ አልወለድምን ተከትሎ የመጣው ዱላና ያፈራው ጠላት ብዙ ነበር። የደራሲው የመጨረሻ እጣ ፈንታ አልወለድም ከተሰኘው ገጸ ባህሪ የተለየ አነበረም። አቤ ጉበኛ የካቲት 4 ቀን 1972 ዓ.ም አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በድንጋይ ተቀጥቅጦ ሞቶ ተገኘ። ነብሰ ገዳዮች በበዙባት ምድር ፍትህ ከወዴት ይገኛል? ሲል አልወለድም ለእናቱ የጠየቃት ጥያቄ ምላሹ እራሱ አቤ ጉበኛ ሆነ። ያለ ፍትህ ተወለደ፤ ያለ ፍትህ ኖረ፤ ያለ ፍትህ ሞተ። ሲኖር እንዲያ የተጠማትን ፍትህ፤ ከሞት በኋላም ነብሱ ተጠማችው። የአሟሟቱ ጉዳይ እንቆቅልሽ እንደሆነ ተደፋፍኖ ቀረ።
ስለምን በድህነት ተወልደን አድገን በድህነት እንሞታለን? ይህ ፈጽሞ መሆን የለበትም። ደስታ ያስፈልገናል፤ ነጻነታችን ሊጠበቅ መብታችንም ሊከበር ይገባል በማለቱ፤ የመጽሐፉ አልወለድም በሽብርተኝነት በከሰሱት ባለጠመንጃ ጉልበተኞች መገደሉ የራሱ የትንቢት ፍጻሜ ነበር። አቤ ጉበኛ ለረሀብ፣ ለድርቅ ለመሀይምነትና ድንቁርና “አልወለድም” ሲል ለጨለማ ሞቶ ለብርሃን ተወለደ። እኛስ ዛሬ ለየትኛው ይሆን እምቢ፤ አሻፈረኝ ስንል አልወለድም የምንለው? ለኑሮ ጉስቅልናና ሕይወት? ለፖለቲካ እንቆቅልሽ? ለዘረኝነት?…ለሃይማኖተኝነት?…ለጥላቻና በቀል? ወይንስ…?
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016