የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም 850ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ገለጸ።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽንና ዓለምአቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ልዑልሰገድ በላይነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በስምንት ክልሎች 371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎች አሉ። እነዚህን የቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል።

በመጀመሪያው ዓመት 50ሺ ከትግራይ እንዲሁም 25ሺህ ከሌሎች ክልሎች በአጠቃላይ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት ዕቅድ ተይዞ እንደነበረ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ዕቅዱን ለማሳካት የገንዘብ ችግር አጋጥሟል ብለዋል።

እንደ አቶ ልዑልሰገድ ገለጻ፤ እቅዱን ዝቅ በማድረግ 50 ሺ የትግራይ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት ዕቅድ ቢያዝም ለሥራው የሚያስፈልገውን 162 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ባለመቻሉ ኮሚሽኑ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ መቸገሩን ገልጸዋል። የሚፈለገው ገንዘብ የሚገኝ ከሆነ በመጪው ጥር ወር ዕቅዱ

 እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡

274 ሺህ የሚጠጉትና 75 በመቶ የሚሆኑት የቀድሞ ታጣቂዎች በትግራይ ክልል የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ በቀድሞው ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎቹን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታጣቂዎቹን ከማደራጀት ጀምሮ ከኅብረተሰቡ ጋር እስከመቀላቀል ድረስ ለሚሆነው ሥራ የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ያጋጠመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍና በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለመግባት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አምባሳደሮች ጋር እየተወያየ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ልዑልሰገድ፤ ኮሚሽኑ አሁን ላይ አደረጃጀት የመፍጠር፣ የሰው ኃይል የማሟላት፣ የሥልጠና ሰነዶችን የማዘጋጀት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋርም ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ድርጅቶቹ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም መግባቢያ ስምነት መፈራረሙንም ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ ታጣቂዎቹን ለማቋቋም ዕቅድ ሲታቀድ 85 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ለማግኘት እንዲሁም 15 በመቶ የሚሆነውን ከመንግሥት ለማግኘት ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተው፤ ባለው አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አሁን ላይ ብሩ እንዳልተለቀቀ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት በሰላም ስምምነቱ ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ቢሆንም እስከ አሁን ያደረጉት ድጋፍ ከቢሮ ማደራጀት ተግባር የሚበልጥ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ልዑልሰገድ፤ እያጋጠመ ያለው የገንዘብ ችግር ኮሚሽኑ ወደ ሥራ እንዳይገባ እንቅፋት እንደሆነበት ጠቁመዋል፡፡

ሥራው ሠላምን ለማጽናት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፎቻቸውን እንዲሰጡ ጠይቀው፤ መንግሥትም ለሥራው ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኅብረት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች የቀድሞ ታጣቂዎችን በማደራጀቱ ሂደት የበኩላቸው አስተዋፅዖ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You