ተስፋ ያልታየበት የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጅማሬ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርገውን ጉዞ ከሳምንት በፊት ከሴራሊዮን ጋር በሞሮኮዋ ኤል-ጀዲዳ ከተማ በሚገኘው ኤል-አብዲ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ ጀምሯል። በመጀመሪያው ጨዋታ ካለምንም ግብ አንድ ነጥብ ተጋርተው ያጠናቀቁት ዋልያዎቹ ትናንትም ሁለተኛውን የማጣሪያ ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ጋር በተመሳሳይ ስቴድየም አድርገው የ3ለ0 ሽንፈት ደርሶባቸዋል::

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ዋልያዎቹ በኳስ ቁጥጥር ተበልጠው አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም ግብ አላስተናገዱም:: በሁለተኛው አጋማሽ በተለይም ከ69ኛው ደቂቃ ላይ ብላቲ ቱሬ ለቡርኪናፋሶ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ ካሳረፈ በኋላ ግን ዋልያዎቹ መፍረክረክ ጀምረዋል::

የመጀመሪያውን ግብ ያስተናገዱትም ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ ሲነገር እንደነበረው የቆመ ኳስ በመከላከል ረገድ ሊቀርፉት ባልቻሉት ችግር ነበር:: ያምሆኖ ዋልያዎቹ አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ዳግም ሌላ ስህተት ሰርተው 78ኛው ደቂቃ ላይ በርትራንድ ትራኦሬ ባስቆጠራት ፍፁም ቅጣት ምት 2ለ0 መመራት ችለዋል:: ይህም የቡድኑን በራስ መተማመን እያወረደው ሄዶ ዳግም በሌላ ስህተት ዳንጎ ኦታትራ 90ኛው ደቂቃ ለቡርኪናፋሶ 3ኛ ግብ ሊያስቆጥር ችሏል::

ቡርኪናፋሶ ማሸነፏን ተከትሎ ነጥቧን አራት በማድረስ የምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። ዋልያዎቹ በበኩላቸው በአንድ ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በቀጣይ የምድቡን ሶስተኛ እና አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከጊኒ ቢሳኦ እና ጅቡቲ ጋር በመጪው ሰኔ የሚያደርጉም ይሆናል::

አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ልምድ ያላቸውና ወጣት ተጫዋቾችን ያሰባጠረ ቡድን በአጭር ጊዜ ዝግጅት ለመስራት ጥረት ቢያደርጉም በሁለቱ ጨዋታዎች ስብስባቸው ይህ ነው የሚባል ቅርፅ ማሳየት አልቻለም:: ይህም በሁለቱ ጨዋታዎች ካስመዘገቡት ውጤት ጋር ተዳምሮ የዋልያዎቹን የዓለም ዋንጫ ጅማሬ ተስፋ ያልታየበት አድርጎታል::

ዋልያዎቹ አጥቂው አቡበከር ናስርና አማካኙ ሽመልስ በቀለን የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ማጣታቸው እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ያሉ ስታዲየሞች በቂ መሠረተ ልማቶችን አላሟሉም በሚል በመታገዳቸው ከሁለት ዓመታት በላይ በሜዳቸው መጫወት አለመቻላቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩ አይካድም::

ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ሁለቱን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ቀላል ከሆኑ ቡድኖች ጋር እንደማከናወኑ በሜዳው ተጫውቶ ቢሆን ምናልባትም የተሻለ ነጥብ የመሰብሰብ እድል ይኖረው እንደነበረም ብዙዎች ተቆጭተዋል። ያምሆኖ በሁለቱ ማጣሪያዎች ዋልያዎቹ እንደ ቡድን ከተከላካይ እስከ አማካኝ፣ ከአማካኝ እስከ አጥቂ የነበሩባቸው ክፍተቶች በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጉዞ ተስፋ የሚፈነጥቁ አይደሉም::

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አንድ ተደልድሏል። በዚሁ ምድብ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቡርኪናፋሶ፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ጊኒ-ቢሳው እና ሴራሊዮን ተደልድለዋል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ያለችው ግብጽ በአንድ መቶ ፐርሰን የማሸነፍ ጉዞ ላይ ትገኛለች:: ፈርኦኖቹ ከቀናት በፊት በምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከሴራሊዮን ጋር በማድረግ ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በመጀመሪያው ማጣሪያም ጅቡቲን 6ለ0 ያሸነፉ ሲሆን ይህም በስድስት ነጥብ ምድቡን እንዲመሩ አስችሏቸዋል።

ፊፋ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራትን ያወዳድራል። የተሳታፊዎች ኮታ መጨመሩን ተከትሎም የአፍሪካም የዓለም ዋንጫ ተሳታፊዎች ኮታ ከአምስት ወደ ዘጠኝ ማሳደጉ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ሀገራት በአዲስ አይነት የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። የአፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ምድቦች ተደልድለው የማጣሪያ ጉዞውን የጀመሩ ሲሆን እያንዳንዱ ምድብ ላይ ስድስት ሀገራት ይገኛሉ። እያንዳንዱ ሀገር በምድቡ በአጠቃላይ አስራ ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን አከናውኖ በሚሰበስበው ነጥብ መሰረት ከዘጠኙ ምድብ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀ ዘጠኝ ሀገር በቀጥታ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።

ከዘጠኙ ምድብ ምርጥ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ አራት ሀገራት ደግሞ እርስበርስ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከተለዩ በኋላ አሸናፊ የሆነው አንድ ሀገር ፊፋ እንደ አዲስ በዘረጋው ኢንተር ኮንፌዴሬሽን ጨዋታ ተሳታፊ ይሆናል። በዚህም በተመሳሳይ መንገድ ከሌሎች አህጉራት ማጣሪያ ከተለዩ ሀገራት ጋር ተጫውቶ ማለፍ ከቻለ አፍሪካ በዓለም ዋንጫው አስረኛ ተሳታፊ ሀገር የማግኘት እድል ይኖራታል።

የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ እንዲያስተናግዱ ተመርጠዋል። ሶስቱ ሀገራት በ16 ከተሞች ትልቁን ውድድር እንደሚያካሂዱ ይታወቃል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016

Recommended For You