ከዕለት የዕለት እንቅስቃሴችን አናየው አንታዘበው የለም። መቼም እግርና መንገድ፣ ዓይንና አስተውሎት ከተገናኙ ብዙ ማየትና መገምገም ብርቅ አይሆንም። ሀገራችንን በመሰሉ ኢኮኖሚያቸው ቀጭጯል በሚባሉ ሥፍራዎች የበረከቱ ችግሮችን ማስተዋል ተለምዷል።
ችግሮች የምንላቸው አንዳንድ ጉዳዮች ከአቅም በላይ የሚባሉ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሲያጋጥሙ ሁኔታዎች መላና መፍትሔ እስኪያገኙ ከመጠበቅ ሌላ ምርጫ አይኖርም። አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸው በግዴለሽነት የሚባክኑ የሀገር ሀብትና ንብረቶች እንዳይሆኑ ሆነው ማስተዋላችን ያሳዝናል።
እነዚህ ሀብቶች አስቀድመው ሲታሰቡ በርካታ ችግሮችን ይፈታሉ፣ ጎዶሎዎችን ይሞላሉ ተብሎ ነው። እውነታው እንዲህ ቢሆንም ተግባር ላይ ጥቅማቸው ሳይታይና ሳይፈተሸ ያለአንዳች አገልግሎት ባክነው ሊቀሩ ይችላሉ።
ለዛሬው ትዝብቴ አንድ ጉዳይን ልጠቁም። የከተማችንን ቀላል ባቡርና የአገልግሎቱን ነገር። መቼም በባቡር ትራንስፖርት እኛ ኢትዮጵያውያን አንታማም። ፈጥነን በማስገባቱ ግንባር ቀደሞች ነን። ዘመናዊነት እግሩን ሰዶ ዓለም በወጉ ሳይሰለጥን ባቡር ይሉትን ጭሱን እያንቧለቅን፣ ድምፁን እያምቧረቅን ሀገር አቋርጠንበታል።
እናም ባቡሩ ለእኛ ብርቃችን ፣ ድንቃችን አልነበረም። የዛሬን አያድርገውና የስልጣኔው መንገድ እኮ ጓዙን ይዞ ሃሳቡን ቋጥሮ ያለፈው በእኛው ሀዲድ ነበር። ‹‹ነበር›› እንዲህ ቀላል ሊሆን የዛኔ በነጻነታችንና የስልጣኔ ፍጥነታችን የማይደነቁ አቻ አፍሪካ ሀገራት አልነበሩም።
አንዳንዶች እጃቸውን በአፋቸው እስኪጭኑ ‹‹አጀብ›› ብለዋል። ዓይናቸው ደም መስሎ እስኪቀላም በቅናት ያረሩ አልታጡም። ውሎ አድሮ ግን ፍጥነታችን ቀዘቀዘ። ርምጃችን የኋልዮሽ ሆኖም ስልጣኔያችን ተዋጠ። ማደግ መመንደግ በሚገባን ጊዜ ታሪካችንን ሌላ ታሪክ ዋጠው። ዕድገታችን ዳዴ ማለት ያዘ።
ወዳጆቼ የተነሳሁበትን ጉዳይ አልዘነጋሁም። መነሻዬ የከተማችን የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በመዲናችን ፈጣን የባቡር ትራንስፖርት ሲጀመር ‹‹እሰይ›› ብለን ተደሰትን። ብንደሰት ደግሞ አይፈረድብንም። እኛ እኮ እንደባቡሩ ስያሜ ችግሮቻችን ቀላል የሚባሉ አይደሉም።
የበረከተው የከተማችን ነዋሪ በትራንስፖርት ችግር ዕለት በዕለት ይንገላታል። በየቀኑ በሚጨምረው የገንዘብ ታሪፍ ይሳቀቃል። እናም ደስ ቢለን አይፈረድም። የዚህኛው የከተማ ባቡር ደስታ ደግሞ እጥፍ ድርብ ነው። በተመቹ ወንበሮች በተስፋፉ ቦታዎች ተጠቃሚው እንዳሻው ይሆናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበርና።
ይህ ብቻ አይደለም የቀላል ባቡሩ በረከት ለአካል ጉዳተኞች አጠቃቀም ምቹና አስፈላጊ መሆኑ ተነግሯል። ከዚሁ ተያይዞ ለአቅመ ደካማዎችና ለነፍሰጡሮች ጭምር ግልጋሎት የሚሰጥ አሳንስር(ሊፍት) መገጠሙ ለችግሮች ‹‹እፎይታ›› ነው። የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ከባቡሩ አጠቃቀም ጋር የተሳለጠ እንዲሆን የታሰበው ደግሞ በጥናት ነው። ጥናቱ መሠረቱን ጥሎ በአካል ቢታይ ብዙኃኑን አስገርሞ አስደስቷል።
እነሆ ! የባቡሩ ትራንስፖርት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጠሩ። ባቡሮቻችን ሥራ የጀመሩ ሰሞን ቃላቸውን አከበሩ፤ በተያዘላቸው ደቂቃ ከች እያሉም ተጠቃሚውን አስደሰቱት። ከታክሲ ከአውቶቡሱ ሲጋፋ የቆየ ሁሉ በከተማው ባቡር በሰዓቱ አሰበበት ይደርስ ያዘ።
የባቡሩ ጉዞው ቀጠለ። እያደርም የተጠቃሚው ቁጥር አየለ። ከወንበር አልፎ ጢቅ ብሎ የሚሞላው ባቡራችን ሥራውን አላቆመም። ባዶ ሆዱን ተጉዞ የማያውቀው አገልጋይ በየደቂቃው ዕልፍ እየሞላበት ፣ ጫን እየተነፈሰ ብዙኃንን ጠቀመ። እንደ አጀማመሩ ግን አልቀጠለም።
ባቡሩ እንደጀመረ ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ተብለው የተሰሩትን የመጓጓዣ ሊፍቶች ዓይኖች ናፈቁ። በተለይ ጉዞውን ሽተው አጠገቡ መድረሻ አቅም ያጡ ወገኖች የሥራውን መጀመር በጉጉት ጠበቁ። በዓይን እንጂ በተግባር ካልተገለጠው ሊፍት ጋር መተያየት ብቻ ሆነ። ቀናት አልፈው ሳምንታትና ወራት ተተኩ። ዓመታት እንደዋዛ ነጐዱ። ብዙ ገንዘብ የወጣበት፣ ለስንት የተጠበቀው የባቡር አሳንሰር በዝምታ ጊዚያትን ቆጠረ።
ይህን ታላቅ የሀገር ሀብት ዛሬ ላይ ላስተዋለው ገጽታው ተለውጧል። ሥራ ያለመጀመሩ እንዳለ ሆኖ በየቀኑ የሚጣልበት ቆሻሻ ምንነቱን አዘንግቷል። ይህን እውነታ ለሚያይ ‹‹ሀገራችን ድሃ ናት፣ ችግር አለባት›› የሚለው ወሬ አይገባውም። በእጃችን ያለንን ሀብት በወጉ ሳንጠቀም ሌላ ርዳታና ብድር ፍለጋ መዋተታችንም ጉዳዩን ከአሳዛኝ በላይ ያደርገዋል። ለነገሩ በርካታ የሕክምና ማሽኖችም እንደተሸፈኑ በአቧራ መዋጣቸውን ሰምተናል።
ዛሬ ላይ የከተማው ባቡር ትራንስፖርት አረፍ እያለም ቢሆን ጉዞውን ይዞታል። የጅማሬውን ያህል በፍጥነቱ ባይቀጥልም ባለው አቅም እየተንከላወሰ በርካቶችን እያገለገለ ነው። በጣም አስገራሚው ጉዳይ ግን ሁሌም ስለአካል ጉዳተኞች የሚነገረው ትርክት ነው።
ተደጋግሞ እንደሚባለው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታትን የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን ፈርማ ተቀብላለች። ይህ ዕውቅና ሲሰጥ ደግሞ ለነዚህ ወገኖች ከቃል ያለፈ ድርጊት በተግባር እንዲተረጎም ታስቦ ነው። ይህ እውነታ ግን በአብዛኛው በእግሩ ቆሞ ሲራመድ ታይቶ አያውቅም። ይባስ ብሎ ጫፍ የደረሰ ጅማሬ እንዲህ ባክኖ ይቀራል።
ሰሞኑን በሥራ መውጫ ሰዓት አንዲት በዊልቸር የምትንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ከእይታዬ ገባች። ይህች ሴት የትራንስፖርት ተጠቃሚ በመሆኗ አውቶቡሶች በመጡ ቁጥር ዓይኗ ይንከራተታል። በርካቶች በሚተራመሱበት የአራት ኪሎ ጎዳና ነገሬ ያላት አልነበረም። ሸገር አልያም አውቶቡስ ብቅ ሲል እርስ በርስ የሚጋፋው ይበረክታል።
የአካል ጉዳተኛዋ ፍላጎት ሸገር አውቶቡሶች የመግቢያ በራቸውን ዝቅ አድርገው እንዲያስገቧት ነው። ወደ ውስጥ ስትዘልቅ ለእነሱ ተብሎ በተዘጋጀ መቀመጫ አረፍ ትላለች። ሀቁ እንዲህ ቢሆንም አጠገቧ የሚደርሱት ሸገር አውቶቡሶች ይህን ማድረግ አልፈቀዱም። ከእሷ ይልቅ ተጋፍተው ለሚገቡት ተሳፋሪዎች ቅድሚያ ሰጥተው ገለል አደረጓት።
ተስፋ ያልቆረጠችው ሴት ሙከራዋ ቀጠለ። ማንነቷን እያሳየች፣ ከፊት ከኋላ እየዞረች በተማጽኖ ተማለደች። አብዛኞቹ መብቷን አክብረው ሊያግዟት አልፈቀዱም። አይተው እንዳላይዋት ጥለዋት ሄዱ። በመጨረሻ አንዱ ልበ ቀና ሾፌር ደርሶ እስኪያሳፍራት በእንግልት መቆየቷን ብዙዎች አስተውለናል። ይህ እንግዲህ በአግባቡ የተዘጋጀን መገልገያ ካለመጠቀም ባለፈ በግልጽ መብት መጋፋትን ያመላክታል።
ይህ ዓይነቱን እውነታ በጋራ መኖሪያ ቤቶችም እያስተዋልነው ነው። አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በርካታ አካል ጉዳተኞች የጋራ መኖሪያዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ዕሙን ነው። ህንጻዎቹ ደግሞ በአሰራር ባህሪያቸው ከመሬት አልፈው በከፍታ ደረጃዎች የተዋቀሩ ናቸው። ይህ ዓይነቱ ግንባታ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ፈተና መሆኑ አይቀሬ ይሆናል ።
ለነዚህ ወገኖች በቀላሉ ዕልባት ለመስጠት የታችኛውን ወለል እንዲጠቀሙት ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው። አሁን ላይ ግን ከፍታቸው ከአራተኛ ፎቅ የዘለለ የሚሉ የጋራ መኖሪያዎች ተበራክተዋል። እነዚህ ቤቶች ከአስር በላይ ወለል አላቸውና ጫፍ ለመድረስ የመወጣጫ ሊፍት ተገጥሞላቸዋል።
ለነዋሪው አለመንገላታት ሲባል የሊፍቶቹ መገጠም እሰዬው ነው። ዕቃዎችን እስከ አስራ አምስተኛ ፎቅ ለማጓጓዝ፣ በየዕለቱም በእግር ወጥቶ ለመውረድ በእጅጉ ይቸግራልና ። አሁንም ግን ችግሩ የባቡሩን ዓይነት አጋጣሚ ያስታውሰናል።
ለነዚህ ቤቶች ላይ ለሊፍት ተብሎ የተገጠመው ቦታ በአግባቡ ተዘጋጅቷል። ስፍራው ቦታውን ከማስታወስ የዘለለ ግን ጥቅም ላይ አልዋለም። በነዚህ የጋራ መኖሪያዎች ላይ የተዘጋጁት የሊፍት ቦታዎች ገሚሶቹ በቆርቆሮ ታሽገው ገሚሶቹ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ሆነዋል። እውን እኛ ድሆች ብቻ ነን ? ይህ ዓይነቱ የግዴለሽነት መዘናጋትስ የት ያደርሰን ይሆን?
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016