
አዲስ አበባ፡- የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ የምርት መዳረሻ ሀገራትን የማስፋፋትና የምርቶችን ጥራት የመጨመር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
12ኛው ዓለምአቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ “ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ፋላጎቷ አስተማማኝ ምንጭ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት፤ የግብርናና የተለያዩ ምርቶች ወጪ ንግዱን ገቢ ለማሳደግ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ መዳረሻዎችን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የግብርናና የተለያዩ ምርቶች በብዛት የሚላኩባቸው ሀገራት ውስጥ ናቸው ያሉት አቶ ገብረመስቀል፤ የገበያ አማራጮችን በማስፋት በእስያና የአረብ ሀገራት እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን ምርቶች የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ምቹ የንግድ ሥራ ፖሊሲ በማውጣት ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ መላክ የምትችለውን የምርት መጠን ወደተለያዩ ሀገራት በማቅረብ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግና ያሉትን የምርት መዳረሻ ሀገራት የማጠናከር፣ የምርቶችን ጥራት የመጨመር፣ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅርበት የመስራት እንዲሁም አዳዲስ የምርት መዳረሻ ሀገራትንና የንግድ አጋሮችን የመሳብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዋና ዋናዎቹ ምርቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምርቶቹን በጥራትና በብዛት በማምረት ወደተለያዩ መዳረሻ ሀገራት ተልከው ሀገሪቱ ማግኘት የሚጠበቅባትን ገቢ እንድታገኝ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ገበያ በሚቀርቡት ምርቶች ላይ ተወዳዳሪ መሆን ይጠይቃል ያሉት አቶ ገብረመስቀል፤ በዚህም የምርትን ጥራትና አቅርቦት የመጨመር እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩትን የፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ ገዥዎች፣ የምርምር ተቋማትና የልማት አጋሮች ችግሮችን በጋራ በመፍታት የዘርፉን ትስስር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህም የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤው ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ጉባኤው የሀገር ውስጥ ላኪዎች፣ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች እና የዓለም አቀፍ ገዢ ኩባንያዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው የንግድ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና አዳዲስ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ሀገሪቱ ለወጪ ንግዱ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግና ለሀገር ገጽታ ግንባታም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ወጪ ንግዱ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች 571 ነጥብ 44 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ ሊቀመንበር ሲሳይ አስማረ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች የዓለምአቀፉን፣ የአፍሪካንና የኢትዮጵያን ንግድ በተመለከተ የተለያዩ ጽሁፎች ይቀርባሉ፡፡ በዚህም በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት ፍላጎት፣ የዋጋ አዝማሚያዎች እና አጠቃላይ የንግዱን ሁኔታ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች የተሟላ መረጃ ያገኙበታል ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ፣ የሀገር ውስጥ ላኪዎች፣ ዓለም አቀፍ ገዥዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮችና የዘርፉ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም