የሉሲዎቹ ተተኪዎች በወሳኝ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምዕራፍ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ለመሥራት ተቃርቧል:: እ.አ.አ በ2024 በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 11ኛው የፊፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት የሉሲዎቹ ተተኪዎች የማሊ አቻቸውን በደርሶ መልስ ጨዋታ 6 ለምንም ማሸነፍ ችለዋል::

የሉሲዎቹ ተተኪዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ ኅዳር 1/2016 ከሜዳቸው ውጪ ባማኮ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ንግሥት በቀለ በ57ኛው ደቂቃ እና እሙሽ ዳንኤል በ68ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ከትናንት በስቲያ ደግሞ የመልሱን ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም አከናውነው 4ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል:: በጨዋታው የሉሲዎቹ ተተኪዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በ35ኛውና በ45ኛው ደቂቃ በእሙሽ ዳንኤል አማካኝነት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች እየመራ ለእረፍት ወጥቷል። ከእረፍት መልስም ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴት ብሔራዊ ቡድን መዓድን ሳህሉ በ66ኛው ደቂቃ እንዲሁም መሳይ ተመስገን በ69ኛው ደቂቃ ጎሎችን አስቆጥረው በፍፁም የበላይነት ማሸነፍ ችለዋል::

በሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ቡድን ልዩነት ፈጣሪ የሆነችው አጥቂዋ እሙሽ ዳንዔል ከስፖርት ቤተሰቡ ሙገሳን አግኝታለች:: ከሐዋሳ ወጣት ቡድን የተገኘችው እሙሽ ለኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ተሰልፋ በመጫወት ባለፉት አራት ዓመታት ለሀገሯ በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር ችላለች:: ለኢትዮጵያ በተለያዩ የዕድሜ እርከን ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ እና ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በርካታ ጎሎችን እያስቆጠረች የምትገኘው እሙሽ ማሊ ላይ በሁለት ጨዋታ ሦስት ግብ ያስቆጠረች ሲሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 13 ከፍ አድርጋለች::

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ማሊን በድምር ውጤት 6 ለ 0 ማሸነፉን ተከትሎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የ180 ደቂቃ ፍልሚያ ብቻ ቀርቶታል:: በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሞሮኮ ጋር ጥር 3 ቀን 2016 የሚያከናውኑም ይሆናል። ሞሮኮን በደርሶ መልስ ጨዋታ ካሸነፉም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሎምቢያ በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።

ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ መጨረሻው ዙር ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በሰጡት አስተያየት፣ «የዛሬውን ጨዋታ ብዙ ትኩረት አድርገንበት ነው የመጣነው። ከሜዳ ውጪ አሸንፈን ብንመጣም በሜዳችን ጥሩ መሥራት እንዳለብን ተነጋግረን ከተጫዋቾቻችን ጋር ብዙ ሥራዎችን ስንሠራ ነበር። ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ብዬ አስባለሁ።» ብለዋል::

ስለ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ሞሮኮ ሲናገሩም «ሞሮኮ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። የሞሮኮን ጠንካራ እና ደካማ ጎንም ለማወቅ እንደ ሀገር ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል። ከዚህ በፊት እንደምንዘጋጀው ለቀጣዩ ጨዋታም ተገቢውን ዝግጅት በትኩረት እናደርጋለን።» በማለት ተናግረዋል::

በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 16 ሀገራት የሚካፈሉ ሲሆን ከኮሎምቢያ ውጪ ያሉትን ቀሪ 15 ተሳታፊ ሀገራት ለመለየት በስድስት አህጉራት የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ። አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት ሀገራት የማሳተፍ ኮታ እንዳላት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) አስታውቋል። በውድድሩ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ 35 የአፍሪካ ሀገራት እየተሳተፉ ነው። የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ በአራት ዙሮች እንደሚከናወን የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2016

Recommended For You