የምላስ ስፖርተኞች

የጤና ባለሙያዎች የምላስ ውጫዊ ክፍልን በመመልከት ብቻ በምላስ ላይ የሚኖር እብጠትን፣ የቀለም ለውጥን እና ነጠብጣብን በማጤን መላ ሰውነታችን ስላለበት የጤና ሁኔታ ፍንጭ ማግኘት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ምላስ ሲንቀሳቀስም በተመሳሳይ መልኩ የአእምሮን ጤንነት መጠቆሙ ነው፡፡ ለዚህም አይደል “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” የሚባለው፡፡ የምላስን ኃያልነት የሚገልፁ ብዙ ብሂሎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ስማቸውን የማላስታውሳቸው አንድ እውቅ ማሲንቆ ተጫዋች ድምጻዊ እንዲህ ተቀኝተዋል፡-

መቆየት ደግ ነው አየን ብዙ መላ ፤

እጅ ሳያቀብል በምላስ ሲበላ፡፡

ወጥ በከሰል በእንጨት እየተቀቀለ ፤

እንጀራ ባቋራጭ በምላስ በሰለ፡፡

ሐሙስ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ገጽ 10 እና 11 ላይ ሁለት የተለያዩ ጽሑፎችን ይዞ ወጥቷል፡፡ ሁለቱም ጽሑፎች ሙሉ ገጽ የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ ገጽ 10 ላይ ያለው ጽሑፍ 65 አራት ነጥቦችን ይዟል፡፡ ገጽ 11 ላይ የሚገኘው ጽሑፍ ግን ምንም ዓይነት አራት ነጥብ የለውም፡፡ በአራት ነጥብ መቋጨት የነበረባቸው በርካታ ዓረፍተ ነገሮች እንዲሁ የገጹ ሜዳ ላይ ተበትነዋል፡፡ ሁለቱ ጽሑፎች ባስመዘገቡት አራት ነጥብ ሲወዳዳሩ ገጽ 10 ገጽ 11ን 65 ለዜሮ ይመራዋል፡፡ አጋጣሚው መረጃው በሌለን እና በማናውቀው ጉዳይ ላይ በእርግጠኝነት የመናገር ድፍረታችንን እንዲሁም ንግግርን የማንዛዛት ልማዳችንን (አራት ነጥብን የሙጥኝ እንደምንለው እና ምን ያህል እንደምንሸሸው) ለማሳየት የሚያስችል ጥሩ ምሳሌ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

አብዛኞቻችን እያንዳንዱን ንግግራችንን በፍጹም እርግጠኝነት ለመቋጭት ያለን ድፍረት ለአራት ነጥብ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ንግግራችንን በ12 ቁጥር ሚስማር እየቸነከርን የአቋም መግለጫ የምናደርገውን ቤት ይቁጠረን፡፡ ሃሳብ “ነው” እና “ናቸው” በሚሉ ድምዳሚ ቃላት ብቻ ሳይሆን ይመስለኛል፤ አስባለሁ፤ እረዳለሁ፤ እገምታለሁ፤ እጠብቃለሁ በማለት አሊያም በጥያቄያዊ ዓረፍተ ነገርም ይገለጻል፡፡ እነዚህን ቃላት መጠቀም ትህትና የተመላ ግብረገባዊ አቀራረብ ከመሆኑ ባሻገር ድፍረት ከሚጭረው የአንደበት እሳት ይጠብቃል፡፡

አራት ነጥብ የናፈቀው የጋዜጣው ገጽ ደግሞ ንግግርን ቶሎ መቋጨት የማይሆንልንን ሰዎች ይወክላል፡፡ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ ዕድል አግኝተው መናገር የጀመሩ ሰዎች ማይክ እንዲለቁ መመኘት የታዳሚዎች ዘወትራዊ እጣ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾችም ያለውን ሁኔታ የታዘበ ሰው መሰል ትዝብት ይገበያል፡፡ በምላስ ወለምታ የምንመታው በዚህ ልማዳችን ሳይሆን አይቀርም፡፡

ንግግርን መግቢያ፣ ዋና አካል (ሐተታ) እና ማጠቃለያ በሚሉ ሶስት ክፍሎች ከፍሎ ማደራጀት ተገቢ እንደሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ መግቢያ አጠቃላይ ለንግግሩ ከተመደበው ጊዜ 10 በመቶ፣ ዋናው ንግግር 70 በመቶ ማጠቃለያው ደግሞ 20 በመቶ ሊመደብለት እንደሚገባ ይገለጻል። የኛ ንግግር ባህል ግን እንደ ኮንደሚኒየም ቤቶቻችን 10/90 አሊያም 20/80 ባስ ሲልም 40/60 ነው፡፡ አብዛኞቻችን መግባትና መውጣት እንጂ ማጠቃለል ብሎ ነገር የምናውቅ አይመስለኝም። ገባ ሲባል የሚወጣውን፤ ሀተታ ሲባል የሚፎትተውን፤ ቋጨ ሲባል የሚቀጥለውን ጆሮ ይቁጠረው።

በዓለማችን ረጅም ንግግር በማድረግ ሪከርድ የያዙት የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ናቸው። መቼም ከእኛ መካከል ይህን ሪከርድ አልፎ ሂያጅ የሚጠፋ አይመስለኝም፡፡ የዘርፉ ጠበብቶች እንደሚገልጹት ከመናገራችን በፊት የምንናገረው ለምንድን ነው ? መረጃ ለማስተላለፍ ወይስ ታሪክ ለመንገር ? ለማሳመን ወይስ ለማዝናናት ? በቅድሚያ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ ቀጥሎ የሚከተለው ምን እንናገራልን የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የምንናገረው ነገር መረጃ ፣ ታሪክ ፣ ማስረጃ ወይስ አዝናኝ ጉዳይ ነው ? እነዚህ ጥያቄዎችም መልስ ማግኘት አለባቸው።

በየመድረኩና በየአጋጣሚው ሁሉ መናገር ደግሞ ግድ አይደለም፡፡ አንዱ መናጢ ደሃ እጮኛው ቤተሰብ ጋር ሽማግሌ ይልካል፡፡ በቤተሰቦቿ ወገን የተቀመጡ ሽማግሌዎች “ለመሆኑ ምን አለው?” ብለው ሲጠይቁ የወንዱ ወገን ሽማግሌዎች “ሌላ የማጨት አማራጭ” ብለው መለሱላቸው፡፡ ምን ለማለት ነው… ሰው ሃሳቡን የመግለጽ ብቻ ሳይሆን ዝም የማለት ምርጫም አለው፡፡

 ዘመናችን የሚፈልገው ንግግር አርቃቂዎችንና በቃላት ተራቃቂዎችን ሳይሆን የተግባር ሰዎችን ነው፡፡ በወሬና ቃል በመግባት ተወዳዳሪ ለማይገኝለት፣ በተግባር ግን ዜሮ ለሆነ ልጃቸው “የምላስ ስፖርተኛ” የሚል ቅጽል ስም ያወጡ እናት አውቃለሁ፡፡ ማህበረሰባችን አያሌ የምላስ ስፖርተኞች አቅፏል። የሚሰለጥንባትና እናሰልጥንህ የሚሉት እነሱ ናቸው፡፡ አንዲት የተግባር ቅንጣት ሳናይ በንግግር ብቻ የምንጠግብ ብዙዎች ነን፡፡ ፈጣሪ ይመስገን የምላስ ስፖርተኞችን አደብ ግዙ ያለ ከያኒ አላጣንም፡፡ እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ እንዲሁም የዜማና ግጥም ደራሲ ኤሊያስ መልካ በድምጻዊ ኢዮብ መኮንን አንደበት እንደሚከተለው ይህን ማህበረሰባዊ ህጻጻችንን ኮንኖታል፡፡

ተጠራርተን ከየቤቱ ቃልን መርጠን መሻማቱ፤

ለመናገር መጎምጀቱ ለኛስ ነው ወይ መድኃኒቱ፤

ለምን አደንቃለሁ ጥሩ ቃል መራጩን፤

በምላሱ ስለት የምናብ ቆራጩን፡፡

ሁላችን ከሆንን የቋንቋዋ ፈላስፋ፤

በተግባር መስካሪ እማኝ እንዳይጠፋ፤

አንድም ሳይጨበጥ ሳይዳሰስ እንኳን፤

ጀግና ልንባል ነው ቃልን ካሰካካን፡፡

አስተዋልኩኝ ብሎ የምሩን ቢነግረኝ፤

አላጨበጭብም መደሃኒት ካልሰጠኝ፤

ለፈለፈው እንጂ መች አጣሁት እኔ፤

አይራቀቅበኝ እድናለሁ ያኔ፡፡

እዚህ አንድ ቦታ ያነበብኳትን ጨዋታ ጣል ባደርግ ጥሩ ይሆናል፡፡ አንድ ወጣት አጠገቡ ለነበሩ ሰዎች በጨዋታ መልክ እንዲህ ሲል ጥያቄን አቀረበ “በአንድ መሬት ላይ በተጋደመ ትልቅ ግንድ ላይ ሶስት እንቁራሪቶች በመደዳ ቆመው ነበር፡፡ አንደኛዋ እንቁራሪት ቆመው ከነበረበት ግንድ ላይ ለመዝለል ወሰነች፡፡ ስንት እንቁራሪቶች ቀሩ?” ይህንን ጥያቄ የሰሙት በሙሉ መልሳቸው፣ “ሁለት” የሚል ነበር፡፡ ሰውየውም መልሳቸው ትክክል እንዳልሆነ ገለጸላቸው፡፡ “አንዷ እንቁራሪት የመዝለል ውሳኔ አደረገች እንጂ አልዘለለችም፡፡ ስለዚህ አሁንም የቀሩት ሶስት እንቁራሪቶች ናቸው” ነበር ማብራሪያው፡፡

“አያችሁ”፣ አለ በመቀጠልም፣ “ይህ የሚያመለክተው ውሳኔን ከተግባር ጋር የማምታታት ዝንባሌያችንን ነው፡፡ አንድ ውሳኔ ወደተግባር እስኪለወጥ ድረስ ከውሳኔው በፊት ከነበርንበት ሁኔታና ደረጃ ትንሽም እልፍ አያደርገንም፡፡” አብዛኛውን ጊዜ አንድን ነገር ለማድረግ ከወሰንን በኋላ ልክ እንዳደረገ ሰው ኑሯችንን እንቀጥላለን። ውሳኔ ግን ያው ውሳኔ እንጂ ተግባር ማለት አይደለም።

የምላስ ስፖርተኞች ይወስናሉ እንጂ ተግባሩ ላይ የሉበትም። እነዚህ አካላት በክፋት መስመር ሲሰለፉ የሚያስከትሉት ጥፋት ማጣፊያ የለውም፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው በለው… ቁረጠው… ፍለጠው እያሉ ጥላቻን በመስበክና ወንድምን በወንድም ላይ ማስነሳት እሳት የሚያስነሱት የምላስ ስፖርተኞች ናቸው፡፡ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ “ፍካታ ናፋቂዎች” በተሰኘ የግጥም ስብስቦችን በያዘ መጽሐፉ፣ የምላስ ስፖርተኞችን ሚና በሦስት መስመር ስንኖች እንደሚከተለው ምጸታዊ በሆነ መንገድ ገልጾታል፡፡

ከገለባ ፍም ሸጉጠው፣

ኡፍ ብለው አቀጣጥለው፣

እሳት ሲያጠፉ እንዲያ ነው፡፡

በእውቀቱ ስዩም በበኩሉ በአንድ ግጥሙ የምላስ ስፖርተኞችን እንደሚከተለው በሁለት መስመር በግሩም ሁኔታ ገልጿቸዋል፡፡

ለጀግናው ሐውልት ስሩ ፣ ጀብደኛውን ሸልሙት

እኔን ተዉኝ ፣ አንሶላዬ ውስጥ ልሙት፡፡

የምላስ ስፖርተኞች ያነሳሳሉ፤ ይገፋፋሉ፤ ያሳምጻሉ፤ ያፋጃሉ እንጂ ሜዳው ላይ መገኘት የማይፈልጉ አንሶላ ውስጥ ሟቾች ናቸው፡፡ እንደ ማህበረሰብ እንዴት በምላሳውያን መዳፍ ውስጥ ተገኘን ብዬ ስጠይቅ ነሐሴ 25 ቀን 1592 የተወለደው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ ከ500 ዓመታት በፊት የወረወረውን ሃሳብ እቀልባለሁ፡፡

ዘርዓ ያዕቆብ “ሰዎች ሁሉ ሐሰትን እንጂ እውነትን የማያስተውሉት ለምንድነው? (ምክንያቱ) የሰው ተፈጥሯው ደካማና ስልቹ ስለሆነ መሰለኝ። ሰው እውነትን ይወዳል፤ አጥብቆም ያፈቅራታል። የተፈጥሮን ስውር ነገሮች ማወቅ ይፈልጋል። ግን ነገሩ አስቸጋሪ ነው፤ ያለ ትልቅ ጥረትና ትዕግሥት አይገኝም፤ ሰሎሞን እንዳለው፥ ከፀሐይ በታች ስለተፈጠረው ሁሉ ልቤን ለምርመራና በጥበብ ለመፈተን ሰጠሁ፤ ምክንያቱም ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ድካምን ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ሰዎች መመራመርን አይፈልጉም፤ ከአባቶቻቸው የሰሙትን ያለምርምር ማመንን ይመርጣሉ እንጂ” ይላል።

 ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You