ከወዲሁ የተጀመረው የድብልቅ ፈተና ዝግጅት

ፈተና ዓይነቱ ብዙ እንደሆነ ሁሉ የአፈታተን ሁኔታውም ዘመኑን ተከትሎ እየበዛና እየተሻሻለ መጥቷል። ድሮ የነበረው የአፈታተን ሥርዓት አንድ ወጥ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ለቴክኖሎጂ እድገት ምስጋና ይግባውና የፈተና አማራጮች በዝተዋል። ዛሬ፣ የትም ሆኖ መማር እንደሚቻለው ሁሉ፣ የትም ሆኖ ፈተና መፈተን ይቻላል። የትም ሆኖ ተፈታኝ፣ የትም ሆኖ ፈታኝ መሆን ይቻላል። ከፈተና ጋር በተያያዘ ታዲያ የትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን አንድ መግለጫ አውጥቷል።

ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ የዘንድሮውን የ2016 ዓ∙ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚመለከት ሲሆን ፈተናው በግንቦት ወር የሚሰጥ መሆኑና የፈተናው አሰጣጥም ድብልቅ (ሀይብሪድ) እንደሆነ ገልጿል። የፈተናው ዝግጅት ከአሁኑ መጀመሩን የሚያመለክተው መግለጫው ድብልቅ ፈተና ማለትም ግማሹ ኦንላይን (የኢንተርኔት ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች)፤ የኢንተርኔት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ በነበረበት አካሄድ በወረቀት የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የፈተና አሰጣጥ አካሄድ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ፣ በመንግሥት በጀት፣ በትምህርት ቢሮዎች ላይ ጫናን እንደሚቀንስ የተነገረ ሲሆን፤ (የአፈታተን ሥርዓቱን በማዘመን) ምንም እንኳን ትምህርት ሚኒስቴር የመግዛት አቅም ባይኖረውም ለፈተናው የሚሆኑ ታብሌቶችን ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመነጋገር በፈተናው ወቅት በመወዋስ ፈተናው በድብልቅ እንደሚሰጥ መግለጫው አመልክቷል።

እንደ መግለጫ ከሆነ፣ የ2016 ዓ.ም ፈተና ድብልቅ በሆነ መንገድ እንዲሰጥ ከወዲሁ ዝግጅቶቹ እየተደረጉ ሲሆን የሶፍትዌር ሥራው ከወዲሁ ተጠናቋል። ምዝገባውንም በኦንላይን ሲሆን፣ ተፈታኞች በአካል ተገኝተው ፎቶ እንዲነሱ ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ ቁጥጥሩ ጠበቅ እያለ ይሄዳል።

የተሻሉ የፈተና አዘጋጆች፣ ፈተናዎች እንዳይሰረቁ የሳይበር ጥበቃ፣ የደህንነት ካሜራዎች፣ የተቋማት ትብብር (ኢንሳ፣ ፈተናዎች አገልግሎት)፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የፈተና ሕትመት ዝግጅት ከዚህ ቀደሙ በተሻለ መልኩ ጠንካራ ሥራ በጋራ እንደሚሰራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው ተናግሯል፡፡

የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ከወዲሁ እራሳቸውን ለመመዘኛ ፈተናው ብቁ እና ዝግጁ እያደረጉ መሄድ ያለባቸው ሲሆን፤ መምህራን፣ ወላጆች፣ መላው የትምህርት ማህበረሰብ ተማሪዎችን እያገዙ ለፈተናው እንዲዘጋጁ ማድረግ አለባቸው ሲልም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያሳሰበው።

በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው ባለፉት ሁለት ብሔራዊ ፈተናዎች ማለትም በ2014 እና 2015 ዓ.ም ከተፈተኑት አጠቃላይ ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዛ በላይ አምጥተው ያለፉት እጅግ ጥቂት መሆናቸው ከመገለፁም በላይ፤ በ2014 ፈተና 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ተፈትነው ያለፉት 30 ሺህ 034 ወይም 3 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፤ በ2015 ዓ.ም ፈተና 845 ሺህ 099 ተማሪዎች ተፈትነው ማለፍ የቻሉት 27 ሺህ 267 ወይም 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መሆናቸውም በመግለጫው ተመልክቷል።

በተለይ ፈተናው በየአካባቢው ካሉ ትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ወጥቶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተመዘገበው ውጤት ብዙሃኑን ያስደነገጠ፤ እንዲሁም፣ የትምህርት ሥርዓቱ ያለበትን አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ያመላከተ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በሂደት ይህ ሁሉ ችግር እየተቀረፈ፤ የተማሪዎች የመማር አቅም እየጎለበተ፤ በመሄድ የተሻለ ውጤት ላይ እንደሚደረስ ይጠበቃል። ይህ ይሆን ዘንድ ታዲያ ተፈታኝ ተማሪዎችን ከወዲሁ በማንቃት ለተሻለ ውጤት እንዲዘጋጁ ማድረግና የተመዘገበው “አስደንጋጭ” ውጤት እንዲለወጥ ማበረታታት ተገቢ መሆኑ ይታመናል፡፡

በታብሌት (የእጅ ስልኮች) ፈተና መፈተን ከተለመደው የወረቀት ፈተና ተጨማሪ እውቀት ይፈልጋል፤ የተለየ ክህሎት ይጠይቃል። በተጨማሪም፣ ጉዳዩ የሶፍትዌር (ወይም፣ አፕሊኬሽን) ነውና የሚሆነው የሶፍትዌር ወይም አፕሊኬሽን አጠቃቀምን ብልሃትንም ይጠይቃል። ይሁን እንጂ፣ ትምህርት ሚኒስቴር “ዝግጅቴን ከወዲሁ ጀምሬያለሁ” ሲል እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ክህሎቶችን በተፈታኝ ተማሪዎች ዘንድ ማስረፅንም ያካትታል ተብሎ ይታሰባልና ጉዳዩ ብዙም የሚያስጨንቅ አይሆንም።

በየትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ መንገድ ተፈታኝ ተማሪዎቻቸውን የማብቃት ሥራዎች ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተፈታኝ ተማሪዎችም ለፈተናው ብዙም በማይጠቅሙ ማህበራዊ ድረገፆች ላይ ጊዜያቸውን ከማጥፋት ተቆጥበው ሙሉ ትኩረታቸውን ጥናትና ዝግጅታቸው ላይ ያደርጋሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሏል።

ወደሃይብሪድ/ድብልቅ/ ፈተናው ሲመጣ ደግሞ በተለይ ዓለማችን አሁን ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ ለተመለከተ ቴክኖሎጂ ምን ያህል እንደተቆጣጠረን በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ዛሬ፣ ከተራ ማህበራዊ ግንኙነት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ መንግሥታዊ ተግባራት ድረስ ያለ ቴክኖሎጂ የሚከናወን ነገር የለም። እዚህ ሆኖ አውሮፓ ፈተና መፈተን፣ እዚህ ሆኖ አሜሪካን ሀገር ከሚገኝ ተቋም ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረግ ምንም አዲስ ነገር የለውም። በመሆኑም፣ ፈተናን በታብሌት መፈተን ችግሮችን ያቀልላቸዋል እንጂ የሚፈጥረው መሰናክል የለም። ምናልባት እኛን የሚያስወቅሰን ነገር ቢኖር ከቴክኖሎጂው መዘግየታችን ነው።

ሌላው፣ የፈተናው ጉዳይ ሲሆን፣ በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው በነባሩ አሰራር መሠረት በወረቀትና በታብሌት በሚፈተኑት መካከል ከፈተናው አኳያ ምንም ዓይነት የይዘትም ሆነ የቅርፅ ልዩነት አይኖርም፤ ልዩነት አለ ከተባለ ያው የተገለፀው አፈታተኑ ድብልቅ (ሀይብሪድ) መሆኑ ብቻ ነውና በዚህ በኩል ማንንም የሚያሳስብ ምንም ነገር የለም።

ከፈረሱ አፍ እንዲሉ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት የመፈተኛ ታብሌቶቹ በተቋሙ አቅም የሚሟሉ ሳይሆኑ የባለ ድርሻ አካላትን፣ የባለ ሀብቶችን ወዘተ ትብብርና እገዛ የሚጠይቁ ናቸው። ከዚህ አኳያ እነዚህ አካላት ፈተናው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና በአግባቡ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ትምህርት ሚኒስቴርም (በባለፉት ፈተናዎች እንደታየው) የማስተባበር ችግር ይኖርበታል ተብሎ ስለማይታሰብ የድብልቅ ፈተና ፕሮግራሙ በሚጠበቀው መልኩ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል።

ሌላው የመፈተኛ ጣቢያዎችና ፈታኞች ጉዳይ ሲሆን፣ ሁሉም ቴክኖሎጂውን ማእከል ባደረገና ቴክኖሎጂው የደረሰበትን እድገት ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ፈታኞችም ቢሆኑ ከተፈታኞቹ ያልተናነሰ የቴክኖሎጂ እውቀት እንደሚያስፈልጋቸው ጥርጥር የለም። ያ ካልሆነ ክፍተት መፈጠሩ የሚቀር አይሆንምና ከወዲሁ መፍትሔን ይሻል።

ከላይ፣ “ድብልቅ ፈተና ማለት ግማሹ ኦንላይን (የኢንተርኔት ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች)፤ የኢንተርኔት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ በነበረበት አካሄድ በወረቀት” ይሆናል ተብሏል። በዚህ መሠረት እነማን በነባሩ፣ እነማን ደግሞ በኦንላይን ፈተናውን እንደሚወስዱ ይታወቃል ማለት ነው። ቢያንስ በግርድፉም ቢሆን አካባቢዎቹን መለየት ይቻላል ማለት ነው። እዚህ ጋር ግን አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ያለ ሲሆን እሱም “∙ ∙ ∙ ችግር ባለባቸው” የሚለው ችግር ሳይሆን “ኢንተርኔት ባልተዳረሰባቸው” በሚለው ቢብራራ የተሻለ ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ “ችግር” የሚለው እዚህ፣ አዲስ አበባም ኢንተርኔት ሁሌም ችግር ነውና።

ቀደም ሲል “አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” በሚለው መሠረት ሲሰራባቸው የቆዩትን አሰራሮች በስር ነቀል ደረጃ እየለወጠ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚናገረው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ይህ የድብልቅ አፈታተን ስርአትም የዚያው አካል መሆኑን እየተናገረ ይገኛል። ባፍጢሙ ተደፍቶ የነበረውን የትምህርት ጥራት በሁለት እግሩ ለማቆም እየወሰዳቸው ካሉ ርምጃዎችም አንዱ ይኸው መሆኑን በማስረዳት ላይ ነው። በመሆኑም፣ ልክ ለትምህርት ተደራሽነት ብቻ ሲሰጥ ከነበረው ትኩረት እኩል ለጥራቱም መሰጠት ጀምሯል ማለት ይቻላልና ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ የተፈታኞች ውጤት እንደሚጠበቅ ይገመታል፡፡

ሌላው ይህ የድብልቅ ፈተና ፕሮግራም ይዞት ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ አቢይ ጉዳይ ቢኖር ተማሪዎች በራሳቸው የመተማመንና ፈተናውን በራሳቸው አቅም የመሥራት ብቃትን ነው። አዎ፣ ከዚህ በፊት በነበረ እጅግ አሳፋሪና ኢ-ሙያዊ አሰራር ምክንያት ተማሪዎችን አንዱን ካንዱ፣ ሰነፉን ከጎበዙ ሁሉ መለየት እስኪያቅት ድረስ ነገሮች ተደበላልቀው እንደነበር ይታወሳል።

በዚሁ መደበላለቅ ምክንያትም ተማሪዎች፣ በተለይም ተፈታኝ ተማሪዎች ነገር ዓለሙን እርግፍ አድርገው በመተው ሁሉ ነገራቸውን ኩረጃ ላይ አሳርፈው “እፎይ” ያሉበት ዘመን ነበር። ዩኒቨርሲቲዎች እምባ አውጥተው እስኪያለቅሱ ድረስ ስሙን ሁሉ የማይጽፍ ተማሪ እየተመደበላቸው ወደ “ሀሁ ∙ ∙ ∙” ማስቆጠር ደረጃ ወርደው እንደነበር ራሳቸው ሲናገሩ ያልሰማ ቢኖር ጥቂት ነው። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ሪፎርም ከሆነ በሂደት እነዚህ ሁሉ ችግሮች እየተፈቱ በመሄድ ላይ ናቸው። ትግሉ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም፣ ሁሉም ሰው የሚተባበር ከሆነ ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

ተፈታኝ ተማሪዎች በሚገባ ተዘጋጅተው ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ እሚቀጥለው የትምህርት እርከን (ፕሮግራም) መሻገር አለባቸው እየተባለ ነው። ትክክል ነው። ነገር ግን፣ ከዘንድሮ የ 2015ዓ.ም ተፈታኞችና ያጋጠሟቸው እድሎች አኳያ አንድ የታየ ልዩ አጋጣሚ ቢኖር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 1000 ተማሪዎች በመጀመሪያ ምርጫቸው በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የመመደባቸው ጉዳይ ነው።

አዎ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ፣ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 1000 ተማሪዎች የመጀመሪያ ምርጫቸው በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርገዋል። ይህ ተማሪዎቹ እራሳቸው ለራሳቸው ያስገኙት ድርብ ድል በመሆኑ ከመደሰትም አልፈው ሊኮሩ ይገባል። የዘንድሮ ተፈታኞችም ይህንን ልዩ እድል ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህ ልዩ እድልና አጋጣሚ ከእጃቸው እንዳያመልጥ በማሰብ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው በመሥራት ስኬታቸውን ድርብ ድርብርብ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃልና ዓመቱ ልዩ ነው ማለት ይቻላል።

የዘንድሮውን ውጤት ተከትሎ፣ በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ አማካኝነት “የዘንድሮው ውጤት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በቁጥርም በውጤትም የተሻለ” መሆኑ (“አስደንጋጭነቱ” እንዳለ ሆኖ) እንደተነገረው ሁሉ፤ በሚቀጥለው ዓመትም የዚሁ ዓይነት (“አስደንጋጭ” የሚለው በነጭ ተሰርዞ) አዲስ ዜና እንደሚነገር ተስፋችን ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You