ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ23ኛ ጊዜ በድምቀት ተካሄደ

ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎችን በማወዳደር ተወዳጅነትን ያተረፈው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትናንት ለ23ኛ ጊዜ በድምቀት ተከናውኗል። ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የጎረቤት ሀገራት አትሌቶችን፣ ኤምባሲዎችንና የውጭ ሀገር ዜጎችን እንዲሁም ሌሎች 45ሺ ተሳታፊዎች እንደወትሮው ሁሉ የ 10 ኪሎ ሜትር ውድድሩን አድምቀውታል። መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው የ 10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ በበርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ሽፋን አግኝቷል።

‹‹ክትባት ለሁሉም ህጻናት›› በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደውን ይህን ውድድር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስጀምረዋል። በኦሊምፒክና ሌሎች ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በረጅም ርቀት የተደጋጋሚ ክብር ባለቤቷ ደቡብ አፍሪካዊት የቀድሞ አትሌት ኤላና ሜየር እንዲሁም ታዋቂው የአትሌቲክስ ጋዜጠኛ ቲም ሃቺንግስ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን በተለያዩ ውድድሮች ማስጠራት የቻሉ አንጋፋና ወጣት አትሌቶችም በመድረኩ ተሳታፊዎች ሆነዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ በርካታ የኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች በዚህ መድረክ የተገኙ ሲሆን በርካታ አርቲስቶችና ስመጥር ሰዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ። 500 የሚሆኑ አትሌቶች (በሴት 200 እንዲሁም በወንድ 300) በሁለቱም ጾታዎች የተለያዩ ክለቦችን ወክለው እንዲሁም በግላቸው ተሳትፈዋል። ደመናማ የአየር ሁኔታ በነበረው ውድድር ወጣትና ልምድ ያላቸው አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። በውጤቱም በወንዶች የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌት የሆነው ወጣቱ አትሌት ቢንያም መሃሪ አሸናፊ ሆኗል። በግሉ የተሳተፈው ዘነበ አየለ እና የኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ አትሌቱ ጂራታ ሌሊሳ ደግሞ ተከትለውት ገብተዋል።

በሴቶች በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮቹ አትሌቶች መልክናት ውዱ እና ተኪና አማረ አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቁ ሌላኛዋ አትሌት መገርቱ አለሙ ከኤሊት አትሌትስ ሁለተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። የአሸናፊዎቹ አትሌቶችም የዋንጫ ሽልማትን ጨምሮ የ200 ሺ፣ 100 ሺ እና 50ሺ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል። ከሩጫው በኋላም በወንዶች አሸናፊ የሆነው ወጣቱ አትሌት ቢንያም፤ በውድድሩ እንዲሁም በአሸናፊነቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል። የአጭር ጊዜ ልምምድ በማድረግ ወደ ውድድር በመግባት የነበረውን ፈታኝ ፉክክር አልፎ አሸናፊ እንደሆነም ባለድሉ አትሌት ተናግሯል። አትሌቱ ልምምዱን በአዲስ አበባ ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተካሄደው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ተሳታፊ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሎ ነበር። በቀጣይም ከሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ ሀገር በምትወከልባቸው ውድድሮች ተሳትፎ ስሟን በኩራት ለማስጠራት አቅዶ በመሥራት ላይ መሆኑንም ጠቁሟል።

አምና በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችው አትሌት መልክናት ውዱ ዘንድሮ ድል ቀንቷታል። በዓመቱ ዳይመንድ ሊግን ጨምሮ በበርካታ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበረችው መልክናት የአየር ሁኔታው ሩጫውን ከባድ ቢያደርገውም ፈተናውን ተቋቁማ አሸናፊ ልትሆን እንደቻለች ተናግራለች። ከዚህ በኋላም ትኩረቷን በቀጣይ ውድድሮች ላይ በማድረግ ውጤታማ የመሆን ጥረቷን እንደምትቀጥል አብራርታለች።

ጀግናው አትሌትና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ሩጫው በየዓመቱ እያደገ 23ኛው ላይ ሲደርስ በ45ሺ ተሳታፊዎች መካሄዱን ገልጿል። የውድድሩን ጥራት በመጨመርም ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ለማሳደግ እንደተቻለ የተናገረው ኃይሌ፣ ይህንንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎዳና ላይ ሩጫ አዘጋጆች መለኪያ 98 ከመቶ ውጤት የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁሟል። በዚህ ውድድር ተሳታፊ የሆኑ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ተፈላጊ ናቸው፤ በመሆኑም በርካታ ማናጀሮች ተገኝተው ይመለከታሉ። ይህም የሆነው ከአዲስ አበባ የቦታ አቀማመጥ አኳያ በሩጫው መሳተፍ ጥንካሬን ስለሚጠይቅ ነው። በመሆኑም በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሚያገኙትን ሽልማት በ30 ከመቶ ማሳደጉን አንጋፋው አትሌት ያስረዳል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር እየሸፈነ ላለፉት 23 ዓመታት የተካሄደ ውድድር ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ግን ከዚህ ያለፈ እንዲሆን እየታሰበ መሆኑን ኃይሌ ይጠቁማል። የዓለም አትሌቲክስ ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱን (ሀገር አቋራጭ፣ የወጣቶች ቻምፒዮና፣…) ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አክሏል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You