የጋምቤላ ክልልን የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድገው ፎኖተ ካርታ

የጋምቤላ ክልል ለግብርና ልማት ሥራ ሊውል የሚችል ለም አፈር፣ በቂ ዝናብ፣ የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት ባለቤት ነው፡፡ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ግብርናን በማስፋት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ይታመናል፤ በዚህም ምንም እንኳ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ባይውልም ሰፊ የመስኖ ልማት ለማካሄድ የኦልዌሮ ግድብ መገንባቱ ይታወቃል፡፡ በኢህዴግ ዘመን ደግሞ ምንም እንኳ ልማቱን ባያካሂዱም፣ በርካታ ባለሀብቶች ለግብርና ኢንቨስትመንት ወደ ክልሉ የገቡበት ሁኔታም እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የክልሉ መንግሥት ለግብርናው ሥራ ሊውል የሚችለውን እምቅ ሀብት የበለጠ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ይገኛል። በክልሉ የግብርና ሥራ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት በቅርቡ ይፋ ተደርጓል፡፡

የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናቱ የድርጊት መርሃ ግብሩን የጀመረ ሲሆን፤ ከተያዘው 2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል፤ በፍኖተ ካርታው መሠረት በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን ሕይወት መለወጥና የኤክስፖርት ምርቶችን ለማምረት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉአል አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ይፋ የተደረገው የግብርና ፍኖተ ካርታ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የዞን አመራሮች፣ ባለሀብቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተገኙበት የትውውቅና የተግበራ መርሃ ግብሩ አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ የክልሉን የግብርና ሥራ በማዘመን አርሶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘጋጀው ከዚህ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ በርካታ ውጤቶች ይጠበቃሉ፡፡

በፍኖተ ካርታው በክልሉ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ በሚችሉ የምርት ዓይነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ኡጁሉ፤ በተመረጡ የምርት ዓይነቶች የሚጀመረው ሥራም ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅና ውጤት የሚጠበቅበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች ምርቶች በመሄድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ኤክስፖርት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ከፍ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

ክልሉ ለግብርና ሥራ ምቹ እንደመሆኑ በፍኖተ ካርታው በዋናነት አስር የሚደርሱ ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በበጋ መስኖ እየለማ ያለው ስንዴ በፍኖተ ካርታ ከሚለሙ የሰብል ምርቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ከፍራፍሬ ማንጎና ሙዝ፣ ከእንስሳት ምርቶች ደግሞ የወተት ምርት፣ የዳልጋ ከብቶች፣ የዓሳ፣ የፍየል፣ የዶሮና ንብ እርባታ ትኩረት ይደረግባቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አጠቃላይ በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀምን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት በተለይም ለእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ አነስተኛና ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ተለይተው መቀመጣቸውን አቶ ኡጁሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለቱሪዝም መስህብ የሚሆኑ ፓርኮችም መለየታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ለመስኖ ሥራ የሚውሉ አራት ትላልቅ ወንዞች በክልሉ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የደን ውጤቶችም በስፋት ይገኛሉ ብለዋል። ክልሉ በማዕድን ሀብት እምቅ አቅም እንዳለው ተናግረው፣ በተለይም ወርቅ በአካባቢው በስፋት እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት፡፡

‹‹ለቀጣይ አምስት ዓመት ተግባራዊ የሚሆነው የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ወደ ሥራ የሚገባው በክልሉ የሚገኙትን እነዚህን እምቅ ሀብቶች መሠረት በማድረግ ነው›› ያሉት አቶ ኡጁሉ፤ ይህ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ በክልሉ በመደበኛው የግብርና ሥራ ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን የሚሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በአስሩ የምርት ዓይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ኤክስፖርትን ዓላማ በማድረግ የሚሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው መሠረት የአርሶ አደሩን ሕይወት በመለወጥ ረገድም ትልቅ ድርሻ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ኡጁሉ፤ በተለይም በክልሉ ያለውን ጎጂ ልማዳዊ አመለካከቶችን በማስወገድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ይላሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ የተለመደው መጠነኛ ምርት አምርቶ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮን መምራት ነው፡፡ በፍኖተ ካርታው ይህን ልማድ በማስቀረት ጠንካራ የሥራ ባህል እና የቁጠባ ባህልን ይፈጥራል። በዚህም አርሶ አደሩ ምርቱን በስፋት እንዲያመርትና ምርቱን ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ወደ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ይሆናል፡፡

በክልሉ አርሶ አደር ያልተለመደውን የሥራና የቁጠባ ባህል በማለማመድ በተለይም በተመረጡ አስር የምርት ዓይነቶች ላይ የሚደረገው ርብርብ አርሶ አደሩን ወደ ባለሀብትነት ማምጣት የሚያስችል እንደሆነ አቶ ኡጁሉ ጠቁመዋል፡፡ ከገቢው ቆጥቦ የግብርና ሥራውን በማስፋት ቀስ በቀስ ወደ ባለሀብትነት እንዲሸጋገር የማድረግ ልምድ እንዲያዳብር ይጠቅማል፡፡

እያንዳንዱ አርሶ አደር ምርቱ ምን ያህል እንደሆነ በማጥናት በቀጣይ ከራሱ የምግብ ፍጆታ ባለፈ ወደ ገበያ ማውጣት የሚያስችለውን ምርት ማምረት እንዲችል በዕቅድ ተይዞ የሚሰራ መሆኑ በፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከተ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፤ ይህም የአርሶ አደሩን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሩ ከባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት የኤክስፖርት ምርቶችን በስፋት እንዲያመርቱ ርብርብ ይደረጋል፡፡ ለዚህም በክልሉ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ 766 የሚደርሱ ባለሃብቶች እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ባለሃብቶች ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር በመፍጠር የሚሠሩ ሲሆን፤ ይህም ለክልሉ አርሶ አደር ሕይወት መሻሻልና ለግብርና ሥራው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ባለሀብቱ ከአርሶ አደሩ ጋር በሚፈጥረው ትስስር ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል ያሉት አቶ ኡጁሉ፤ አንድ ባለሀብት በሚሰራበት አካባቢ ላይ አንድ ቀበሌ አርሶ አደሮችን መለወጥ አለበት ብለዋል፡፡ ይህ እንደ አቅጣጫ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በአቅራቢያቸው የሚገኙ ቀበሌዎችን በማገዝ የአርሶ አደሩን ሕይወት ከግብርና ፍኖተ ካርታው ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ማድረግ አንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡

እንደ አቶ ኡጁሉ ማብራሪያ፤ በክልሉ አርሶ አደሩ ባለው አነስተኛ የእርሻ መሬት በስፋት የሚያመርተው በቆሎና ማሽላ ነው፤ አርሶ አደሩ ለእነዚህ ምርቶች ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ቢሆንም፣ ግሪሳ ወፍ የሚያስችግርበት ሁኔታ በመኖሩ በተለይም ማሽላ የማምረት ፍላጎቱ ቀንሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች ሰፋፊ በሆኑ የእርሻ መሬት ላይ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ ማሾና የመሳሰሉት እያመረቱ ናቸው፡፡ አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ ከፊል አርብቶ አደር እንደመሆኑ ለእንስሳት እርባታም ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይቻላል፡፡ በክልሉ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ይገኛል፡፡ 19 የሚደርሱ የዓሳ ዝርያዎችም አሉ፤ ዓሳ በክረምት ወቅት በብዛት ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመኸር የእርሻ ሥራ ማለፉን ጠቅሰው፣ በክልሉ የወንዞች ሙላት እየቀነሰ ሲሄድ የሚሰራው የግብርና ሥራ ውሃ ሸሽ ሥራ እንደሆነ አቶ ኡጁሉ ተናግረዋል፡፡ በውሃ ሸሽ የግብርና ሥራ 37 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአየር መዛባት ምክንያት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ በውሃ ሸሽ እርሻ በዘር የሸፈነው መሬት እየተበላሸ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ውሃ ሸሽ ግብርና ወንዞች ሞልተው ሲቀንሱ አርሶ አደሩ እርጥበቱን ተከትሎ የሚዘራበት የእርሻ ሥራ እንደሆነ አቶ ኡጁሉ ገልጸው፤ በዚህ መልኩ የተዘራው ዘር ከተሰበሰበ በኋላም የመስኖ እርሻ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኡጁሉ፤ ዝናቡ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በበጋ መስኖ ለማልማት የታቀደውን ሥራም እያስተጓጎለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በመስኖ የእርሻ ሥራ 6ሺ500 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ በዚህም ስንዴን ጨምሮ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝና የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሥራሥር ልማት ለማካሄድ ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ዝናቡ ቆም ሲል በየካቲትና መጋቢት አካባቢ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል፡፡

ዝናብ በሌለባቸው አካባቢዎች የበጋ መስኖ ሥራው መጀመሩን ጠቅሰው፣ ከበጋ መስኖ ልማት 827 ሺ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡ በውሃ ሸሽ ከተመረተው ምርትም እንዲሁ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ኡጁሉ ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂ ለምርትና ምርታማነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ኡጁሉ፤ መንግሥት ለክልሉ ትራክተሮችን ማቅረቡንም አስታውቀዋል። በቅርቡም ለመስኖ ሥራ አገልግሎት የሚውሉ 16 የሚደርሱ ትራክተሮችን ለማቅረብ መንግሥት ቃል መግባቱን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ የአቅም ውስንነት እንዳለበት አመልክተው፣ አሁን ያለው የሜካናይዜሽን አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት የሚያደርጉትን ይህን መሰሉን ድጋፍና ክትትል አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ኡጁሉ እንደገለጹት፤ በክልሉ በድህረ ምርት ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ክፍተቶች አሉ። አርሶ አደሩ የደከመበትን አዝመራ መሰብሰብ እንዳይችል ችግሮች እየገጠሙት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ምርቱ ሲባክንና አርሶ አደሩም ለፍቶ መና ሲቀር ይስተዋላል፡፡

ለአብነትም በአካባቢው አትንኩኝ የሚባል አረም ስለመኖሩ ገልጸው፤ አረሙ አርሶ አደሩ ምርቱን ማሳ ውስጥ ገብቶ ለመሰብሰብ አያስችለውም ብለዋል። በዚህ ምክንያት አብዛኛው ምርት ማሳው ላይ በስብሶ እንደሚቀርም ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ የበቆሎ፣ የሩዝና የማሽላ መፈልፈያ በአጠቃላይ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊና የግድ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ የገባው የጋምቤላ ክልል የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ በጥናቱ መሠረት ተግባራዊ ሆኖ የተፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ አመራሩን ጨምሮ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል፣ ባለሙያዎችና ማህበረሰቡ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ ኡጁሉ፤ በተለይም አመራሩ የግብርና ኤክስቴንሽኖችንን በማጠናከር የክልሉ ሕዝብ ወደ ሥራ እንዲገባ በመቀስቀስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የልማት ቡድን ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ግብርናን ለማዘመን በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት፤ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናቱን ወደ ተግባር የመቀየርና የአርሶና የከፊል አርብቶ አደሩን ሕይወት በመለወጥ ሥራ ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡

በክልሉ ለግብርና ልማት ሊውል የሚችለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት በመለወጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ክልሉ ለግብርና ልማት አመቺ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያለው ቢሆንም፤ ሕዝቡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ሥራ የሚተዳደር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አካባቢው የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ አልቻለም። በመሆኑም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ተጠቅሞ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የግብርና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግሥትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ስለመሆኑ የጠቀሱት ሚኒስቴሩ፤ በግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮች ታግዞ እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ለሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። የፍኖተ ካርታው አካል የሆነው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን በሚደረገው ርብርብም እንዲሁ አመራሩ፣ ሕዝቡና የዘርፉ ተዋንያኖች በሙሉ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You