መስከረም ሲታሰብ አዲስ ዓመትና አደይ አበባ፣ አዲስ ዓመትን ተከትሎ ደግሞ የመስቀል ወፍና የመስከረም ወር የተለየ መገለጫ አላቸው። ከሳምንት በፊት የሸኘነው የጥቅምት ወርም መገለጫው ብዙ ነው። ጥቅምት አጥንትን ሰርስሮ ከሚገባ ብርድና ቁር ባሻገር ‹‹የጥቅምት አበባ›› የሚል ማሞካሻውም የወቅቱ መገለጫ ነው። በእያንዳንዱ ቀናት የምናሳልፋቸው የህይወት ክስተቶች ከቀናት ጋር የተሳሰሩ ናቸው። በዚህ ቀን፣ አምና በዚህ ሰዓት እያልን የምናስታውሳቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።
ያጠናቀቅነው የጥቅምት ወር ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ዝነኛ የጥበብ ሰዎችን ያገኘችበት ወር ሆኖ እናገኘዋለን። እነዚህ ዝናቸው ከጥግ እስከ ጥግ የናኘ የጥበብ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ተጉዘው ሀገራቸውን ያስጠሩ በሥራዎቻቸውም በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ናቸው። የዛሬው የዝነኞች ገፃችንም ጥቅምት ያፈራቸውን ዝነኛ የኪነ ጥበብ ፍሬዎች ህይወትና ሥራዎቻቸው ከብዙ በጥቂቱ የምንመለከትበት ነው።
አፈወርቅ ተክሌ
ማንኛውም ሰው ሥራዎቻቸውን ሲመለከት ስለእሳቸውም ሆነ ኢትዮጵያ መልካም ነገር እንዲያስብ ተስፋ እንዲታየው ይፈልጋሉ። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ ዝናቸው በኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ አይደለም። ታላቁ ሠዓሊ ትውልዳቸው ከጣልያን ወረራ ሦስት ዓመት ቀደም ብሎ ነው። ይህ ጊዜ በአፈወርቅ ልጅነት ላይም ሆነ በቀሪው ህይወታቸው ላይ ትልቅ አሻራን አሳርፏል። ለዛም ይመስላል በሚሰሯቸው የሥዕል ሥራዎች ውስጥ ሰላም፣ ሀገርና ነጻነት ያላቸውን ቦታ በጉልህ የሚያሳዩት። ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ.ም ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ እና ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ በጥንታዊቷ ከተማ አንኮበር ተወለዱ ።
በልጅነታቸው የሰሙትን ማንኛውም ታሪክ ሆነ በክፍሉ ውስጥ የሚማሩትን ከደብተራቸው ጎን በሥዕል ለማስቀመጥ ይሞክራሉ። ታዲያ ከልጅነታቸው የጀመሩት በምናብና በውብ ነገር የተሞላው አዕምሯቸው እጃቸውን ሲመራው ባገኙት ብዕርም ሆነ እርሳስ እየሞነጫጨሩ የጥበብ እጃቸውን ፈተዋል። በሂደትም ራሳቸውን ፣ ህይወታቸውን፣ የሚወዷት ኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት በትልቅ ክብር በዓለም ፊት ከፍ አድርገው ያስቀመጡ ሠዓሊ ናቸው። ልዩ የሆነ ትኩረትና ውበት ለሥዕሎቻቸው ይሰጣሉ ።
በ16 ዓመታቸው የውጪ የትምህርት እድል ካገኙ ተማሪዎች መሀል አንዱ በመሆን ወደ እንግሊዝ አቀኑ። በጊዜው የተላኩት በማዕድን የትምህርት ዘርፍ እውቀት ሸምተው እንዲመለሱ ነበር። የእሳቸው ትኩረትና ጥሪያቸው ግን ከዚህ ዘርፍ እንዳልሆነ የተገነዘቡ። እናም በለንደን ሴንትራል ስኩል ኦፍ አርትስ ኤንድ ክራፍትስ ገብተው መማር ጀመሩ። በዚያ ትምህርት ቤት ባሳዩት ችሎታም በእውቁ ስሌድ ስኩል ኦፍ ፋይን አርት ትምህርት ቤት ገብተው የተሻለ እውቀት ለመሸመት አስቻላቸው። በዚህ ዝነኛ የስዕል ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር የበቁ የመጀመሪያው አፍሪካዊም ነበሩ።
የያኔው ተማሪ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ሥዕልን ቅርጽና ኪነ-ህንጻን ተምረዋል። የሥዕል ሥራዎቻቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሥዕል ጥበብ በኢትዮጵያ እምብዛም ቦታ የሚሰጠው አልነበረም፤ በዚህ የተነሳም ሰለጠኑ በሚባሉ ሀገራት መርጠው በአንዱ እንዲኖሩ በየጊዜው ሀሳብ ይቀርብላቸው ነበር ። እሳቸው ግን ለትምህርት ከተመረጡ ጓደኞቻቸው ጋር ለመጓዝ ሲዘጋጁ በወቅቱ ንጉሰ ነገስት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያሏቸውን ያስታውሳሉ። “ጠንክራችሁ በመሥራት ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ።
ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ እንጂ አውሮፓ ውስጥ ስላሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች ወይም ስለመንገዶቻቸው ስፋት እንድትነግሩን አይደለም።” ነበር ያሏቸው። ይህም ባህር ማዶ የተላኩበትን አደራ አክብረው ሀገራቸውን ኢትዮጵያን መርጠው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጋቸዋል። በ1947 ዓ.ም የመጀመሪያቸው የሆነውን የሥዕል አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ንጉሱ በተገኙበት ሲያቀርቡ ሥራቸው እጅግ አስደናቂ የነበረ ቢሆንም በጊዜው ለሥዕል የነበረው አመለካከት እምብዛም በመሆኑ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
የሥዕል ሥራቸውን ለመግዛት ተስማምተው የወሰዱ በርካታ ሹማምንት ለወሰዱት ሥዕል አስፈላጊውን ክፍያ ከመክፈል ይልቅ መመለስን ምርጫቸው አድርገዋል። በዚህም አውደ-ርዕዩ የጠበቁትን ያህል ውጤታማ አልሆነም። ከመጀመሪያው የሥዕል አውደ ርዕያቸው ያገኙትን ገንዘብ ሰብስበው እንደገና ወደ አውሮፓ በመመለስ የመስታወት ላይ ሥዕልን ተማሩ፤ ስለ ኪነ-ህንጻም አጠኑ።
በ1958 ዓ.ም ዓለም አቀፍ እውቅናቸውን ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የመጀመሪያውን የሥነ-ጥበብ ሽልማት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተቀበሉ። በዚያው ዓመትም በሩሲያ ሞስኮ ታላቅ የሥዕል አውደ ርዕያቸውን አቀረቡ። በወቅቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመገኘትም የማይረሱ ንግግሮችን አድርገዋል። በ1959 ዓ.ም በአሜሪካ መንግሥት ግብዣ በዋሽንግተንና ኒውዮርክ የአንድ ሰው የሥዕል አውደ-ርዕይ አቀረቡ።
በ1964 ዓ.ም የሰው ልጆችን ወንድማማችነትና የሰላም ልዕልናን የሚመሰክረው ሥራቸውን በተለያዩ ሀገሮች አቀረቡ። በዚህ ሥራቸውም በ1971 ዓ.ም በአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል የወርቅ ሽልማት ክብርን አገኙ። በፈረንሳይ ሀገር ባቀረቡት የሥዕል ሥራም ተወዳዳሪዎቻቸው የነበሩትን የጃፓን፣ የፈረንሳይ እና የሜክሲኮ ሠዓሊዎችን በልጠው በአንደኝነት ከመሸለማቸው በላይ የቤናል የሎሬት ክብር ማዕረግን አገኙ።
እ.አ.አ በ2000 በዋሽንግተን ዲሲ በተጠራው 27ኛው ዎርልድ ሎሬት ኦፍ ዘ አሜሪካን ባዮሎጂካል ኢንስቲትዩት ጉባኤ የዓለም ሎሬት ክብርን ተቀዳጁ። እ.አ.አ በ2004 በአየርላንድ ደብሊን ላይ በተጠራው ጉባኤ ለሰው ልጆች ትምህርትና ጥበብ ለዓለም ባበረከቱት መልካም ተግባር የዳቪንቼ አልማዝ ሽልማትን ሲቀበሉ፤ በዚሁ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን የተባለ ተቋም ለዓለም ጥበብ እድገት ላበረከቱት መልካም ሥራ የጀግና ክብር ኒሻን ሸልሟቸዋል። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የዚህ ሁሉ ማዕረግና ክብር ባለቤት ሲሆኑ በሄዱበት ሁሉ ለሀገራቸው ተጨማሪ የክብርና የዝና ምንጭ ናቸው።
ከሠሯቸው የሥዕል ሥራዎች መካካል በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን በመስታወት ላይ የሠሩት አስደናቂ ሥዕልና በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች የሚገኙት ሥራዎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው። መጀመሪያ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመስታወት ላይ ሥዕል ሥራ የተሰጠው ለአንድ ጣልያናዊ ሠዓሊ ነበር። የዚያን ጊዜው ወጣቱ ሰዓሊ አፈወርቅ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሱ በመቅረብ ሥራውን ኢትዮጵያዊ ሊሠራው ሲችል እንዴት ለአውሮፓዊ ተሰጠ ብለው ጠየቁ። ግርማዊነታቸውም አርክቴክቱን ጠርተው ጠየቁት የባለሙያው መልስ የነበረው “ይህንን ሥራ ሊሰራ የሚችል አፍሪካዊ የለም” የሚል ነበር ።
ንጉሱም ወጣቱን ሠዓሊ ጠርተው ይህንን ሥራ ሊሰራው ይችል እንደሆነ ጠየቁት፤ ያለምንም ማመንታት የተማረው እሱን እንደሆነ እና እንደሚሰራው በሙሉ ርግጠኝነት ተናገረ። ህንጻውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ የቀረው ስድስት ወር በመሆኑ አርክቴክቱ “ጊዜ የለንም” ሲል ተቃወመ። በችሎታው የተማመነው ሠዓሊ ግን ከበቂ በላይ ነው ሲል አሳመነ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በመላው አፍሪካ ውድድር እንዲደረግ አዘዙ። የያኔው ወጣት ሠዓሊ የኋላው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ከ17 ዳኞች የ14ቱን ድምጽ በማግኘት ያንን የመስታወት ላይ ጥበብ የአፍሪካን ትናንት ዛሬና ነገን እንዲያሳይ አድርገው በብሩሻቸው አሰፈሩ።
በሕይወት ዘመናቸው ከ97 በላይ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችና ሽልማቶችን አግኝተዋል። የታላላቅ መሪዎችን ምስል ቀርጸው አስቀምጠዋል። በኢትዮጵያ የባህል ሚኒስቴር የሥነ-ጥበብ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል። በዓለም የኪነጥበብ መድረክ ላይ ከ50 ዓመታት በላይ እንደ ብርቅ ኮከብ ሲታዩ የነበሩት ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ሚያዝያ ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በሕይወታቸውም በሞታቸውም ሀገርን ያልረሱት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ መኖሪያቸው የነበረውን “ቪላ አልፋ” ጨምሮ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ለሀገራቸው ተናዘው አርፈዋል።
አስቴር አወቀ
ስለ ፍቅር የተዜሙ ዜማዎች ሲነሱ የሷም ስም አብሮ በትልቁ ይወሳል። ወደ ሙዚቃው ዓለም ከተቀላቀለችበት ጊዜ አንስቶ አሁንም ድረስ የድምጿ ውበት አልተለወጠም። በሥራዎቿ በጊዜ ሂደት ያልተቀየሩ አድናቂዎችንም ለማፍራት ችላለች። ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለች ወደ ሙዚቃው የገባችው አስቴር አወቀ፤ዛሬም ድረስ በተወዳጅነቷ ለመዝለቅ በቅታለች። በሙዚቃዎቿ ስለ ሀገር፣ፍቅር፣ሀዘን፣ደስታ እንዲሁም ስለ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አቀንቅናለች። ለዚህ ሥራዋም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግን ተቃድጅታለች።
የክብር ዶክተር አርቲስት አስቴር አወቀ የተወለደችው በጥቅምት ወር ላይ ሲሆን፤የትውልድ ቀዬዋም ከጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ነው። ትንሽ ልጅ በነበረችበት ወቅት የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩት አባቷ በሥራ ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወሩ አጋጣሚውን ተከትሎ እሷም ወደ አዲስ አበባ ገባች። ሙዚቃ የልጅነት ሕልሟ ቢሆንም ቤተሰቦቿ ግን በምርጫዋ በፍጹም ደስተኛ አነበሩም። በወቅቱ አብዝታ ታደምጣቸው የነበሩት የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰና የብዙነሽ በቀለ የሙዚቃ ሥራዎች ወደ ሙዚቃ እንድትሳብ አድርገዋታል። በ13 ዓመቷ ወደ ብሄራዊ ቲያትር አቅንታ በቲያትር ቤቱ በድምጻዊነትና ተወዛዋዥነት ለመቀላቀል ስትወዳደር የተጫወተችው የብዙነሽ በቀለን ሙዚቃ ነበር ። በብሄራዊ ቲያትር ቤት ተቀጥራ ሥትሰራ ከቆየች በኋላም ከሸበሌ፣ከአይቤክስ ፣ ከሮሃ እና ከሆቴል ደ አፍሪክ ባንዶች ጋር በመጣመር የሙዚቃ ሥራዎቿን ማቅረቧን ቀጠለች።
የሶልዋ ንግስት መጠሪያዋ ነው። በሥራዎቿም ሆነ በአለሷ በቃለመጠይቆቿም ጭምር ሀገሯን የምታስተዋውቅ እና ያላትን ፍቅር የምትገልጽ ድምጻዊት ናት። በሙዚቃ ሕይወቷም የእርሷን አርአያነት የተከተሉ ብዙ ሙዚቀኞችን ማፍራት ችላለች። ድምጻዊት ብጽዓት ስዩምና እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ቃለ-መጠይቆች፤ቀደም ሲል የእርሷን ሙዚቃዎች ያቀነቅኑ እንደነበር ተናግረዋል።
እስከዛሬ በነበራት የሙዚቃ ቆይታዋ 26 አልበሞችንና ከ250 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ለአድማጭ ጆሮ አድርሳለች። ከእነዚህም መካከል “ካቡ” የተሰኘው የሙዙቃ ሥራዋ በጊዜው፤በኮሌጅ የሙዚክ ሠንጠረዥ ላይ ለወራት በአንደኝነት ለመቀመጥ ችሏል። ለየት ባለው የአዘፋፈን ስልቷ በታይምና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መጽሄቶች ላይ በጊዜው መነጋገሪያ እስከመሆን ደርሳለች። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋርም ለመስራትም ችላለች፡
የራሷ ብቻ የሆኑ በርካታ መለያዎች ባለቤት የሆነችው አስቴር አወቀ፤መድረክ ላይ የሙዚቃ ሥራዎቿን የምታቀርብባቸውን ልብሶች እራሷ ዲዛይን ማድረጓ አንደኛው መለያዋ ነው። “ካቡ”፣ “ሶባ”፣ “ጨጨሆ” እና “ጨዋ” የተሰኙት አልበሞቿ ካበረከተቻቸው የሙዚቃ ሥራዎቿ መሃከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ሙዚቃን ከጀመረችበት የለጋ እድሜዋ አንስታ ረዥም ጊዜን በመድረክ ብታሳልፍም፤ ነገር ግን አሁንም ድረስ ሰዎች ፊት የመቅረብና የመቆም ፍርሀት አለባት። ነገሩ እንዲህ ቢሆንም መድረክ ላይ ወጥታ ገና ማዜም ስትጀምር እሷና ፍርሃት ይሰነባበታሉ። ሁሉንም ነገር ትረሳዋለች።
አስቴር አወቀ ከድምጻዊነቷ ባሻገር የግጥምና ዜማ ደራሲም ናት። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በበጎ ፈቃደኝነት ትሳተፋለች። በአንድ ወቅትም የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሰደር ነበረች።
እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)
በወርሃ ጥቅምት የተወለደችው ሌላኛዋ ተወዳጅና የምንግዜም ተናፋቂዋ ሙዚቀኛ፤እጅጋየሁ ሽባባው ናት። ከዋና መጠሪያ ስሟ በላይ ‘ጂጂ’ መታወቂያዋ ነው። በጥቅምት 11 ከቻግኒ ተወልዳ ብቅ ያለች የሙዚቃ ኮከብ ናት። ጨዋታና ህብረት ባለበት ቤት ውስጥ ያደገች ናትና ፍቅር መገለጫዋ ነው። የሀገራችን የሙዚቃ ሀያሲያን፤ጂጂ ሀገሯን የምትመለከትበት የተለየ ዓይን አላት ይሏታል። ባለቅኔዋ ሲሉ የሚጠሯትም ጥቂት አይደሉም። በተለያዩ ጊዜያት ሥራዎቿ በባለሙያዎች ተተንትነዋል። ጂጂ ትንቢትን የምትናገርና ታሪክን አጉልታ የምታሳይ ድንቅ ዜመኛ ናት።
“ጉራማይሌ”፣ “ናፈቀኝ” ስለ ሀገር ውበት ስለቤተሰብፍቅርና ናፍቆት ወዲህ ደግሞ ስለ ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ “አድዋ”፣ “የበረሀው ሲሳይ” እያለች ስታዜም ከከተማ ይልቅ ባለ ዋሽንት ባለሀገር የሚናፍቃት ሙዚቀኛ ብቻ ሳትሆን ባለታሪክም ጭምር ናት። የሙዚቃ ሥራዎቿን ስትጽፍም ታሪክን የመንገር ያህል አድርጋ እንደምታስባቸው ትናገራለች።
እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) ከሀገር የወጣችው ገና ታዳጊ ወጣት ሳለች ነበር። ለስደት በከተመችበት ኬንያ፤የራሷን ባንድ አቋቁማ የሙዚቃ ሥራዋን ስትጀምር፤የዚያኔም ገና ልጅ ነበረች። በሀገር ውስጥ እምብዛም በማትታወቅበት ሰዓት ከሀገር ርቃ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር መስራት ጀመረች። ረጅም ጊዜዋን ከሀገር ርቃ ታሳልፍ እንጂ አብዛኞቹ የሙዚቃ ሥራዎቿ በኢትዮጵያ ካሉት የሙዚቃ ስልቶች የተለዩ አይደሉም። የመጀመሪያ አልበሟ የሆነውን “ፀሀይ” ከመውጣቱ በፊት በተለያዩ ባለሙያዎች እንዲገመገም አድርጋ ነበር።
ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካን አቅንታ ተከታታይ የሙዚቃ ሥራዎቿን ማቅረብ ቀጠለች። “አንድ ኢትዮጵያ” የተሰኘው አልበሟ በስፋት የታወቀችበት የሙዚቃ ሥራዋ ሲሆን፤የራሷ የሆነውን “ጂጂ” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ ስልትና አቀራረብ ይዛ ብቅ ያለችበትም ጭምር ነው። ይህ አልበም በብዙኃኑ የተደመጠና የተወደደላት የሙዚቃ ሥራ ነበር ። ሙዚቃ ለእርሷ ከሙዚቃነት ባለፈ ታሪክን የምታወሳበትም ጭምር ነው። በግሏ ከሠራቻቸው ሰባት የሙዚቃ አልበሞች በተጨማሪ፤ከሌሎች ድምጻውያን ጋር በመሆን በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ሠርታለች። ከዚህም ባሻገር ለፊልም ማጀቢያ የሚሆን የሙዚቃ ሥራ ለመሥራትም ችላለች።
በሥራዎቿ የሀገሯን ታሪክና ባህል የምትገልጸውና አሁንም ብዙ በመሥራት ላይ እንዳለች የምትናገረው ድምፃዊቷ፤በ2015 ዓ.ም ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የክብርት ዶክትሬት ማዕረግን አግኝታለች። ወርሃ ጥቅምት፤በዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ካነሳናቸው ኮከብ ዝነኞች በተጨማሪ፤ድምፃዊ እዮብ መኮንን እንዲሁም ታላቁ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ይህቺን ምድር የተቀላቀሉባት ወር ናት።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2016