መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ የዘርፉን መሠረተ ልማቶች በመገንባት ላይ ይገኛል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ ግንባታቸውም በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተጠናቀቀም ነው፡፡ በአዲስ አበባ በገበታ ለሸገር የተገነቡት የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይና የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክቶች ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ፤ ፕሮጀክቶቹ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
መንግሥት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ደግሞ በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል፡፡ የኮይሻ አካል የሆነው የሀለላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገ ሲሆን፣ የወንጪና የጎርጎራ ፕሮጀክቶችም ግንባታቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በገበታ ለትውልድ ደግሞ የሌሎች ተመሳሳይ በርካታ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተጀመረ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሎቹ እየተተገበሩ ያሉት እነዚህ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት መከናወናቸው፣ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና ጥራት መገንባት እንደሚቻል ያመላከቱና በኢንቨስተሮች ፍላጎት ላይ በጎ ተፅእኖ የፈጠሩ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ሃሳብ አፍላቂነት ትግበራ ላይ ከሚገኙት “የገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው “የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም” ግንባታ ሂደትም የዚህ ማሳያ መሆን ይችላል።
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ፣ “የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ‹‹ወንጪ›› እና “ደንዲ” በመባል የሚታወቁ ሁለት ሃይቆችን ያማከለ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ መሆኑን ይናገራሉ። የመጀመሪያው ዙር የመሠረተ ልማት ግንባታም “ወንጪ” ላይ ልዩ ትኩረቱን አድርጎ ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰዋል። ይህ ፕሮጀክት ሲጀመር በ10 ዓመት ውስጥ በሶስት ዙር እንዲጠናቀቅ ታስቦ ነው፡፡ አሁን ግንባታው መጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰው “የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም” መሠረተ ልማት ግንባታ በመጀመሪያው ዙር ላይ የተያዘ መሆኑን ይገልፃሉ።
የወንጪና ደንዲ አካባቢዎች ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት (መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት) የሌለባቸው ቦታዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ እነዚህን ዋና ዋና ጉዳዮች ማሟላት፣ የቴሌኮም የኔትወርክ ጥራቱን ማሳደግ እንዲሁም ለጎብኚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሎጆችን ለመሥራት በማቀድ ፕሮጀክቱ መጀመሩን ያመለክታሉ። በዚህም ሁሉም የመሠረተ ልማት እቅዶች ተተግብረው ግንባታቸው ከ90 እና 95 በመቶ በላይ መድረሱንና ለምረቃት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
“በመጀመሪያው ዙር የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ግንባታ ሁሉም እቅዶች ተተግብረው የመጨረሻው ማጠናቀቂያ ደረጃ ላይ ተደርሷል” የሚሉት ማኔጀሩ፤ በመንገድ ግንባታው ከአምቦ ወደ ወንጪ የሚወስደው፣ የወንጪ ዙሪያው፣ ወደ ሐይቁ የሚወስደው፣ ወንጪን ከደንዲ የሚያገናኘው እና የመሮጫ መም (ትራክ) የሚይዘው መንገድ ግንባታ ከ98 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ይገልፃሉ። ሌላው ደካማ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎትን ለማሻሻል በተከናወነው ተግባርም የአካባቢውን የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደ 4ጂ ደረጃ ከፍ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ይገልፃሉ።
አቶ ብርሃኑ እንደሚገልፁት፣ በመጀመሪያው ዙር የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ግንባታ ከተያዙት ውስጥ የመጠጥ ውሃ ግንባታና ዝርጋታ አንዱ ነው፡፡ በአካባቢው የጉድጓድ ቁፋሮ ተካሂዶ ውሃው ወጥቷል፤ የሥርጭት መስመር ዝርጋታው እየተካሄደ ነው። ይህም ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በሚፈለገው መልኩ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሌላው የመሠረተ ልማት ግንባታ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መሆኑን በማንሳትም፣ በዚህም ረገድ ከወሊሶ ከሚመጣው የኤሌክትሪክ መስመር ኤሌክትሪክ ኃይል በመጥለፍ ለሎጅ፣ ለመንገድ እና ለሁሉም የወንጪ አካባቢ የኃይል ፍላጎቶች ለማድረስ የመጨረሻ ደረጃ የዝርጋታ ሥራ እየተከናወነ ነው ይላሉ።
“በዚህኛው ዙር አንድ ደረጃውን የጠበቀ ኢኮ ሎጅ በወንጪ ፕሮጀክት እየሰራን ነው” የሚሉት የመሠረተ ልማት ፕሮጄክት ማኔጀሩ፤ የዚህ ሎጅ ግንባታም ከ92 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ጠቁመዋል። በሂደቱ የቀሩት የማጣሪያ፣ የእቃ ማስገባትና መሰል አነስተኛ ሥራዎች መሆናቸውንም ይገልፃሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አብዛኛው የኢኮ ቱሪዝም ግንባታው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የወንጪ አካባቢ አርሶ አደሮችን ከቦታው ከማንሳት ይልቅ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚል 13 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተውላቸዋል። እነዚህ አርሶ አደሮች ኑሯቸው ከማህበረሰብ አቀፍ ሎጁ ጋር የተሳሰረ እንዲሆንና የዚያም ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይህ ፕሮጀክት የእቅዱ አካል አድርጓቸዋል። በሂደቱም ሁሉም አርሶ አደሮች የወተት ላሞች ተሰጥቷቸዋል። የእርሻ መሬታቸውንም ወደ ኢኮ- ግብርና ቀይረው ለቱሪዝም ፕሮጀክቱ አቅራቢ በሚሆኑበት መንገድ እንዲተሳሰሩ ተደርጓል፡፡ የተገነቡትን ቤቶችም በዚህ ሳምንት ለአርሶ አደሮቹ የማስረከብ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡
የኮንትራክትሮች አፈፃፀም
በመጀመሪያው ዙር እየተተገበረ ባለው የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ግንባታ ላይ በርካታ ኮንትራክተሮችና ንዑስ ኮንትራክተሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በመንገድ እና ሌሎች መሰል የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የተሳተፉት የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች አፈፃፀም ውጤታማ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ።
የመንገድ ግንባታው በሀገር ውስጥ ኮንትራክተር 48 ኪሎ ሜትር እንደተሰራ በመግለፅም የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ ስድስት የሚደርሱ ንዑስ ኮንትራክተሮችን በመቅጠር እንደተሳተፈና ውጤታማ ሥራ እንደተሰራ ይገልፃሉ። የወንጪ አካባቢ ዝናባማና የአፈሩም ሁኔታ ምቹ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ግንባታ ጊዜው ሲፈቅድ ብቻ እየተሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ ግን ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፣ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ አፈር መቆረጡንና አስቸጋሪ የአየር ንብረትን በመቋቋም እንደተተገበረ ይናገራሉ።
በመንገድ ግንባታው ላይ ከተሳተፉት ኮንትራክተሮች መካከል የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ አንዱ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ብርሃኑ፣ ወደ ሎጁ የሚወስደውን 10 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ይገልፃሉ። የዚህ ግንባታ ሂደትም ተመሳሳይ የአየር ፀባይና የመልከዓ ምድር አስቸጋሪነት ማጋጠሙን ጠቅሰው፣ ቀንና ሌሊት ለ18 ሰዓታት በመሥራት የተሻለ አፈፃፀም እንደታየ ይገልፃሉ።
የሎጅ ግንባታውን የጣሊያን ኮንስትራክሽን ኩባንያ እንደያዘው የሚናገሩት ማኔጀሩ፤ ኩባንያው ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ሆኖታል ብለዋል። ከሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች በተለየ ሥራውን የተቀበለው ዘግይቶ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ወደ ማጠናቀቂያው ደረጃ መድረሱን ይናገራሉ። የወንጪ አካባቢ ቀዝቃዛማ የአየር ንብረት ያለው፣ ዝናብ የሚጥልበት እና ከፍተኛ መልከዓ ምድር ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀንና ሌሊት በሙሉ ጊዜ ሥራው እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ግንባታው በአሁኑ ወቅት የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
የንድፍ ሥራ
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም አጠቃላይ ይዘትና ገፅታ ለቱሪዝም መስህብ እንዲመጥን የንድፍ ሥራ ተተግብሯል። ፅንሰ ሃሳቡ በኤም ኤች (MH) ኢንጂነሪንግ ቢሰራም አጠቃላይ የንድፍ ሥራው በጣሊያን ኩባንያው “ሳሊኒ” ድጋፍ በጣሊያን ሀገር በሌላ ኩባንያ መሠራቱን የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ማኔጀሩ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከመንገድ ግንባታው ጋር በተያያዘም የሀገር ውስጥ የንድፍ ሥራ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የኦሮሚያ ቢፕ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና፣ ጂኤንድ ዋይ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተሳትፈዋል፡፡ በሎጅ ግንባታው ደግሞ የጣሊያን ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በአርሶ አደር ቤቶች ግንባታ እንዲሁም በሌሎች የግንባታ ሂደቶች ላይም የሀገር ውስጥ አማካሪዎች በንድፍ (ዲዛይን) ሥራው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህ ሂደትም ውጤታማ አፈፃፀም መታየቱን ጠቅሰው፣ የአካባቢውን ባህል እና የኑሮ ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ ለመሥራት እድሉ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ትግበራ
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም በሶስት ደረጃዎች የሚተገበርና በጥቅሉ አስር ዓመታትን የሚወስድ ፕሮጀክት ነው። አሁን ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ እየተዘጋጀ የሚገኘው “የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም” ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር እንዲጠናቀቅ የታቀደ ነው። ቀሪ ሁለት ዙሮች እንደሚኖሩና ግንባታው እንደሚቀጥልም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ማኔጀሩ አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ ይናገራሉ።
“ከስሙ መረዳት እንደምንችለው ፕሮጀክቱ ወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ነው” የሚሉት ማኔጀሩ፤ እየተተገበሩ የቆዩት በወንጪ፣ በደንዲ እና በሁለቱም መካከል ላይ የሚለሙና የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን በዝርዝር ጠቁመዋል።
በሁለተኛው ዘር የሚከናወኑት በደንዲ የሚሰሩ ልማቶች ሲሆኑ፣ አሁን አንዳንድ ሥራዎች ተጀምረዋል። በዚህም በአካባቢው አንድ ሎጅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ይህም የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ይገልፃሉ። የሁለተኛው ዙር አካል የሆኑት ሌሎች ሥራዎች ደግሞ በግል ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች የሚሰሩት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነርሱም በወንጪ የሚሰሩ ሎጆችን እንደሚያካትቱ ጠቁመዋል።
ወንጪንና ደንዲን በሚያገናኘው 13 ኪሎ ሜትር መንገድ መካከል ላይ የተወሰነ ቦታ መኖሩን የሚናገሩት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ማኔጀሩ፤ በዚያ ስፍራ ላይ ግዙፍ የስብሰባ ማዕከላት (convention center)፤ የአትሌቲክስ መንደር፣ የውሃና የመዝናኛ ፓርኮች፣ የጎልፍ ስፖርት መንደር፣ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ለመሥራት መታቀዱን አብራርተዋል። የዚህ ዲዛይን እና ዋና ፕላን ተጠናቆ ለባለሃብቶች ጥሪ የማድረግ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ሁለቱ ሐይቆች መስህብ ያላቸው ናቸው” የሚሉት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ማኔጀሩ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ጫና መፍጠርና በግንባታ ማጨናነቅ ተገቢ አለመሆኑ እንደታመነበት ይናገራሉ። በዚህ መሠረትም በወንጪና በደንዲ መካከል ያለውን ቦታ በመለየት ከላይ ለተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማዋል መታሰቡን ያስረዳሉ። ሥራዎቹም በሁለተኛና ሶስተኛ ዙር በሚሰሩት የልማት ሥራዎች ውስጥ መካተታቸውንም ይገልፃሉ።
እንደ መውጫ
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም በስፔን ማድሪድ ተካሂዶ በነበረው በ24ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ይታወሳል። የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም እንደ ሀገር እየተሰሩ ካሉ ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚሰራ የተነገረው ፕሮጀክቱ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመጠናቀቅ የቀሩት ጥቂት ጊዜያት መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአካባቢውን ነዋሪ “ጥያቄ የመለሰ” ፕሮጀክት ስለመሆኑ ማህበረሰብ በተለያየ አጋጣሚ ሲናገር ተደምጧል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሊጠናቀቅ ጫፍ መድረሱና የሁለተኛና ሶስተኛው ሥራ በሂደት ላይ መሆኑንም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም የቱሪዝም መስህብ ስፍራ ተጨማሪ ሃብት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016