ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በታላላቅ ተጋባዦች ደምቆ ነገ ይካሄዳል

ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ስሟ በመልካም የሚጠራበት፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የምትደምቅበት፣ በሯጮቹ ሃገር አትሌቲክስ ባህላዊ ስፖርት መሆኑ የሚመሰከርበት፣ ኢትዮጵያዊያንና የሌሎች ሃገራት አትሌቶች ለማሸነፍ የሚፋለሙበት፣ በርካቶች ተሳታፊ ለመሆን የሚጓጉለት ተናፋቂው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነገ ለ23ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ስፖርት፣ ቱሪዝም፣ ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት፣ ዲፕሎማሲ ወዘተ በአንድ በሚታዩበት በዚህ መድረክ 45ሺ ሯጮች ይሳተፉበታል፡፡

ዛሬ ደግሞ 3ሺ500 ህጻናት የሚካፈሉበትና ‹‹ክትባት ለሁሉም›› የሚል መሪ ሃሳብ ያለው የህጻናት ሩጫ ይካሄዳል፡፡ በዘንድሮ ሩጫ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ተሳታፊ ለመሆን ከተመዘገቡት ውስጥም ከ130 በላይ የሚሆኑት ከ15 ሃገራት የተወጣጡ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ 500 (200ሴት እና 300 ወንድ) የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሚካፈሉበት በዚህ ውድድር ላይም እጅግ በርካታ ዝነኛ አትሌቶችን ባፈራው ግሎባል ስፖርት ኮሚዩኒኬሽን ስር የሚሰለጥኑ ዩጋንዳዊያን እንዲሁም ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የተወጣጡ አትሌቶች ተካፋይ ይሆኑበታል፡፡

ባለፉት ዓመታት ታዋቂ ከሆኑ አትሌቶችና የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ባሻገር የጥበብ ሰዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተው ውድድሮችን አስጀምረዋል። እነዚህ የክብር እንግዶችም የጎረቤት ሃገር ኬንያን ጨምሮ የእንግሊዝና ሌሎች ሃገራት ድንቅ ብቃታቸውን ያስመሰከሩና ከኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጋርም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ፉክክር በማድረግ የሚታወቁ ጭምር ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ በክብር እንግድነት ደቡብ አፍሪካዊቷ አንጋፋ አትሌት ኤለና ሜየር እንዲሁም ታዋቂው የአትሌቲክስ ውድድር ኮሜንታተር ቲም ሃቺንግስ በምስራቅ አፍሪካዊቷ የአትሌቶች ሃገር ተገኝተዋል፡፡ አንጋፋዋ አትሌት ባለፉት ዓመታት ቀንደኛ ተፎካካሪዎቿን ስታገኝ፤ የቀድሞው አትሌትና ለ33 ዓመታት የአትሌቲክስ ጋዜጠኛ የሆነው ቲም ድላቸውን የተረከላቸውን አትሌቶች እንዲሁም ልምምድ የሚያደርጉባቸውን ስፍራዎች የመመልከት እድል አግኝተዋል፡፡

ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ በእርግጥም ውድድሩን አሁን ካለበት እንዲደርስ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ ይታመናል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ህሊና ንጉሴ፤ በየዓመቱ ጥሪ ከሚደረግላቸው እንግዶች ባለፈ እነሱን ተከትለው የሚመጡ በርካታ አካላት እንደመኖራቸው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ለውድድሩ ሽፋን እንደሚሰጠው ትገልጻለች፡፡ ይኸውም የውድድሩን ደረጃ የሚጨምር ሲሆን በተጋባዥ እንግዶች አማካይነትም ውድድሩ ምን ይመስላል የሚለው ለዓለም ይታያል። እንግዶቹ ምንም እንኳን በሙያቸው ታላላቅ ስራን የሰሩና በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ግብዣው ሲቀርብላቸው ሌላ መርሃ ግብር ከሌላቸው በቀር ምላሻቸው አወንታዊ ነው፡፡ በተለይ ጥሪው የሚቀርብላቸው በጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በኩል መሆኑ እሱን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ምላሻቸው ቀና ነው፡፡

እንግዶቹ ሩጫውን ከተመለከቱና ተሳታፊ ከሆኑ በኋላም ወደሃገራቸው ሲመለሱ በቀጣይ ሌሎች ከመጋበዝ አኳያ ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ባለፈ ስለ ኢትዮጵያ የታዘቡትን ለሌሎች በመናገርም መልካም ገጽታን ይገነባሉ፡፡ ለዚህ መንገድ የሚከፍተውም የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድሩ ባለፈ የሚያዘጋጅላቸው የጉብኝት እንዲሁም ባህላዊ እሴቶችን የሚመለከቱበት መርሃ ግብር እንደሆነ ዳይሬክተሯ ታስረዳለች፡፡ ከተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችንና አምሳደሮችንም በመጋበዝ በጋራ ይሰራል። ይኸውም የስፖርት ዲፕሎማሲ እንዲሁም የስፖርት ቱሪዝምን የሚያሰፋ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 23 ዓመታት ሳቆራረጥ በተመሳሳይ የመወዳደሪያ ወቅት እየተካሄደና እያደገ የመጣ ውድድር መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም በሩጫው ላይ ከሚሳተፈው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ባለፈ በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘቱ ለዲፕሎማሲው ሰፊ ሚናን ይጫወታል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሌሎች ዓለማት ከሚካሄዱ ህዝባዊ ሩጫዎች የተለየና የራሱ የሆነ መልክ ያለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው የስፖርታዊና የመዝናኛ መድረክ ነው፡፡ ይኸውም በየጊዜው በሃገር ውስጥና በውጪ ያለውን ተሳታፊ በይበልጥ በመሳብ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ነገ አዲስ አበባ ላይ ከሚደረገው ሩጫ ባለፈ 200 የሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ የሩጫ ውድድር በተመሳሳይ ሰዓት ለንደን ላይም ይካሄዳል፡፡ ይህ ሁኔታ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የ‹‹ቨርቹዋል ሩጫ›› በሚል መተግበሪያ የተጀመረ መሆኑ የምታስታውሰው ዳሬክተሯ በሂደት እያደገ ሊመጣ ችሏል፡፡ ለንደን ላይ ከሚደረገው ሩጫ ባለፈም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚሮጡና የተለያየ ዜግነት ያላቸው 130 የሚሆኑ ሯጮችም በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መተግበሪያ አማካይነት 10ኪሎ ሜትር ይሮጣሉ፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016

Recommended For You