ለዘላቂ ሰላም የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች ሚና

በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች 75 በመቶዎቹ በሃይማኖት ተጽዕኖ ሥር እንደ ሆኑ እና በከፍተኛ ሁኔታ ከሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ጥናቶች ያመላክታሉ። በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ከጠቅላላው ሕዝብ 99 በመቶ የሚሆነው አማኝ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖቱን አክባሪ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ፣ ለእምነቱ ቀናዒና ተገዥ መሆኑን ከኛ አልፎ ዓለም ይመሰክርለታል።

ይህ ሃይማኖተኛና ፈርያ እግዚአብሔር ያለው ሰፊው የሀገሪቱ ህዝብ በአንድም ሆነ በሌላ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በሚከተለው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ተጽዕኖ ሥር ያለ ነው። የሃይማኖት ተቋማትና አባቶቹ የሚሉትን የሚሰማ፣ ሰምቶም የሚፈጽም ነው። ይህ ደግሞ በራሱ ለማኅበራዊ አንድነት እና ለሰላም ግንባታ የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ የማይኖረው ነው፡፡

በተለይም የሃይማኖት አባቶች ልዩነቶችን በንግግርና በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር የሚኖራቸው ጠቀሜታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። በሃይማኖታዊ አባታዊ ተግሳጽና ምክራቸውም በዳይ እንዲክስ፣ ተበዳይ ደግሞ እንባው እንዲታበስ በማድረግ ይቅር በመባባል ሰላምን ለማጽናት የሚኖራቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ዛሬ በሀገራችን በተዛቡ ንዑስ ትርክቶች፣ በጽንፈኛ እና አክራሪ አስተሳሰቦች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ፤ ከዚህም ባለፈ ሀገራዊ ሰለምና አንድነትን በጸና መሰረት ላይ ለማዋቀር በሚደረገው አሁነኛ ጥረት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸው ድርሻ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

በቀደሙት ዘመናት የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች በትንሹም በትልቁም ሰላም እና ዕርቅ እንዲጸና መሰረት ነበሩ፡፡ በሀገራት ደረጃም የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን የሃይማኖት አባቶች ሰላምን በማውረድ ረገድ የነበራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡

እንደ ሀገራችን ሃይማኖት፣ ባህልና ወግ ደግሞ ባል ከሚስት፣ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ በጥቅሉ አንድ ሰው ከሌላው በተለያየ ምክንያት ቢቀያየም የዕርቀ ሰላሙን ሥራ የሚከውኑት የሃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ “በእርቅ ደም እንዲደርቅ” ቄሱ ታቦትን ከዙፋኑ ይዞ ወጥቶ ይገዝታል፣ ሼህ በዱዋው ያስማማል፤ ያስታርቃል።

በሀገራችን ትናንትም ሆነ ዛሬ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ጠብ እና ጦርነቶች ሲካሄዱ ኖረዋል። ሀገሪቱ ከገባችበት የግጭት አዙሪት ለመውጣት ደግሞ፤ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ምዕመናቸውን ስለ ሰላም ከማስተማር ባለፈ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው፡፡

በመሆኑም በሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩ ግጭቶች እንደ ሀገር በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ያደረሱት ኪሳራና ውድመት ዛሬ ላይ እንዳይደገም የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች የሚጠበቅባቸውን መንፈሳዊና ሞራላዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል። ለዚህም እራሳቸውን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

የተለያዩ ሃይማኖቶች አስተምህሮና ዶግማ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ስለ ሰላም ያላቸው አስተምህሮ ተመሳሳይ በመሆኑ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰለም እንዲሰፍን በጋራ ሊመክሩና ሊሠሩ ይገባል። ግጭት ውስጥ ያሉ አካላትን ወደ ሰላም ጎዳና እንዲመጡ ሳይታክቱ ማስተማር ለአስተምህሮው ተፈጻሚነትም በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ተቋማቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ከፍተኛ ተቀባይነት አኳያ፤ በሰላማዊ መንገድ በድርድርና በውይይት አለመግባባቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ይችላሉ። በአንጻሩ ሰላማዊ መንገድን አልቀበልም ያለን አካል በማውገዝ እና ምዕመኑ ከሰላም ውጪ ያሉ ሃሳቦችን እንዳይገዛና እንዳይከተል በማስተማርና በመስበክ የጦርነት ነጋዴዎችንና በሰው ሕይወት የሚቆምሩ ነፍሰ በላዎችን እራቁታቸውን ማስቀረት ይችላሉ።

የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ዘላቂነት ካለው የሰላም አስተምሮ ባለፈም ፤ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ ሊጮኹ፣ ሊመክሩ፣ ሊያስተምሩ፣ ሊዘክሩ፣ ሊገስጹ … ይገባል። ይህም ሀገርን ከትርምስና ከውድመት፤ ንጹሃንን ከሰቀቅንና ከሞት ይታደጋል። እነሱም ከወቀሳና ከታሪካዊ ተጠያቂነት ይድናሉ። ለሰላም ዘብ በመቆምም ለሰላም የሚሰጡትን ዋጋ በተጨባጭ ያመላክታሉ።

ስለ ሰላም መምከር፣ አብዝቶ መሥራት፣ የሰላም መታጣት የሚያመጣውን ችግር በግልጽ ማስረዳት፣ ከደረሱብን የሰላም እጦት ሰው እንዲማርና ከሰላም ጎን አጥብቆ እንዲቆም ማድረግ ፤የጥላቻን ዘር በመዝራት የሚፈጸመውን አክራሪነት ለሀገር ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ መሆኑን ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። ይህም የሰላም ሐዋሪያ ስለመሆናቸው ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ሰላም ማኅበራዊ ዕሴት ነው። ሚዛናዊ የሆነ መስተጋብርን ይፈልጋል፡፡ የደካሞች ሰላም ሲከበር በማኅበረሰቡ ውስጥ የኃያላኑም ሰላም እንደሚከበር ለሰፊው ምዕምን ማስተማር ያስፈልጋል። በማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አንዳንዴም የተቃረኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና ያልተጣጣሙ ፍላጎቶች የተነሣ የፖለቲካ ትግል ይፈጠራል፡፡ ትግሉ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ፣ከማህበረሰቡ ባሕል፣ እምነትና ግብረ- ገብነትን ተከትሎ ሊሆን እንደሚገባም ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ያሉ አካሄዶችን በግልጽ በማውገዝ፣ የተበደለ እንዲካስ፣ የበደለ ይቅር እንዲልና ሁሉም ወደ ሰላም ጎዳና እንዲመጣ በማድረግ ዘላቂ ሰላም በሀገሪቱ እንዲሰፍን የማይተካ ሚናቸውን ከመቸውም በላይ ዛሬ ላይ በቁርጠኝነት ሊወጡ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነትን አስከፊነትና አውዳሚነት ለኢትዮጵያ ህዝብ መናገር “ለቀባሪ” እንደማርዳት ይቆጠራል።

ስለዚህ ምዕመኑ የሃይማኖት አባቶችን የሰላም ጥሪ ጀሮ ሰጥቶ ሊያደምጥና ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል። የሚከተለውንም እምነት ለይስሙላ ሳይሆን በተግባር ሊኖረው ይገባል። ወንድምን ከወንድሙ ለማስተራረድ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ የጦርነት ነጋዴዎችን “ጆሮ ዳባ” በማለት እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባል እላለሁ። ሰላም ለሀገራችን ይሁን!

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016

Recommended For You