ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች ሀገር ናት። የወርቅ፣ የእምነበረድ፣ የድንጋይ ከሰል፣ እንደ ኦፓል ያሉ የከበሩ ድንጋዮች፣ የታንታለም ፣ የጂብሰም፣ የኖራ ድንጋይ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ ማዕድናት እምቅ ሀብቶች ይገኙባታል። እነዚህ የማዕድን ሀብቶች ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም ውስጥ የተለዩና የታወቁ ውስን ሀብቶች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ ሊቲየም ያሉ ማዕድናት ተገኝተዋል። እንደዚያም ሆኖ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ የማዕድን ሀብቶች ገና ጥናት ያልተካሄደባቸውና ያልታወቁ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በጥናት የተለዩትን የማዕድን ሀብቶች አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል በኩልም እንደ ወርቅና እምነበረድ፣ ጀብሰም ያሉትን ካልሆነ በቀር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትኩረት ተሰጥቶ በሌሎች ማዕድናት ላይ እንዳልተሰራ ይገለጻል። እንደ ወርቅ ያሉትን ማዕድናት የማልማቱ ሥራም በቴክኖሎጂ ብዙም ያልተደገፈና በባህላዊ መንገድ የሚከናወን ሆኖ ቆይቷል።
የማዕድን ሀብት የገቢ ምንጭ የሥራ እድል መፍጠሪያና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። መንግሥትም ይህን ታሳቢ በማድረግ በዘርፉ ላይ በስፋት እየሠራ ይገኛል። ባለፉት አምስት ዓመታት ይህን የሀገሪቱን እምቅ የማዕድን ሀብት በማጥናትና በማልማት ጥቅም ላይ በማዋል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተሠራ ነው። ማዕድን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ አቅድ የኢኮኖሚው ዋና ዋና ምሰሶዎች ተደርገው ከተያዙት አምስት ዘርፎች አንዱ ተደርጎ እየተሠራበት ነው።
የማዕድን ሚኒስቴር ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችሉ ሥራዎች በመሥራት፣ ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስፋትና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የገበያ ትስስር ለመፍጠር በርካታ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል። በየክልሎቹ የመንግሥት መዋቅሮችም እንዲሁ በየደረጃው የማዕድን ዘርፉ ራሱን ችሎ የተደራጀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የየክልሉን የማዕድን ሀብት በማስጠናትና በመለየት ወደ ልማት ለማስገባት እየሰሩ ናቸው።
ይህን ተከትሎም አበረታች ጅምሮች ስለመኖራቸው አመላካቾች አሉ። እንደ ወርቅ፣ ኦፓልና የድንጋይ ከሰል ማዕድናት ባሉባቸው ክልሎች በርካታ ዜጎች እየተደራጁ በልማቱ ተሰማርተዋል፤ ኩባንያዎችም ወደ ልማቱ እየገቡ ይገኛሉ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኤክስፖዎችን በማዘጋጀት የሀገሪቱን የማዕድን ሀብት በማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት እና ኢንቪስተሮችን በመሳብ የማዕድን ሀብቱን ማልማት የሚያስችል ሥራ እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ባለፈው ዓመት የተጀመረው ‹‹የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ›› አንዱ ማሳያ ነው። ኤክስፖው ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል።
የማዕድን ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ተስፋሁን የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖው የማዕድን ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት ታስቦ መዘጋጀቱን ይናገራሉ። የዘንድሮ ‹‹ ማይን ቴክስ›› በመባል የሚጠራው የዘንድሮ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የማዕድን ሀብቱን ማስተዋወቅ ነው ያሉት አቶ አወቀ፣ የማዕድን ዘርፉን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማሳየት ባለሀብቶችን (ኢንቨስተሮችን) መሳብም ሌላው አላማው መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹የማዕድን ሀብቱን በአግባቡ አልምተን ካልተጠቀምንበት ሀገሪቱ በርካታ የማዕድን ሀብት ያላት መሆኑ ብቻውን ዋጋ የለውም›› ያሉት አቶ አወቀ፤ ይህ ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ኤክስፖዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በዘንድሮው ኤክስፖ በዘርፉ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎችና ትላልቅ አቅም ያላቸው ድርጅቶች እንደሚገኙ ተናግረው፣ ኤክስፖው ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።
አቶ አወቀ እንዳሉት፤ የዘንድሮው ‹‹የማይን ቴክስ/ የማዕድንና ቴክኖሎጂ›› ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ ‹‹የማዕድን ሀብታችንን የነገ ተስፋችን›› በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል። በባለፈው ዓመት የተካሄደው ‹‹ማይን ቴክስ ኤክስፖ›› ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ እንደመሆኑ መጠን በዝግጅትም ሆነ በአቀራራብ ክፍተቶች ነበሩበት። ከዚህ በተገኘው ልምድና ተሞክሮ መሠረት የዘንድሮውን ኤክስፖ በተለየ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ኤክስፖ የፓናል ውይይቶች እንዳልተካሄዱ አቶ አወቀ ጠቅሰው፣ የዘንድሮው ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ከኤክስፖው ጎን ለጎን ሦስት ያህል የፓናል ውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱበት ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በፓናል ውይይት መድረኮቹ በማዕድን ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ምንድናቸው? ዘርፉ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ተግዳሮቶችስ አሉ? ተስፋዎቹስ ምንድናቸው? የማዕድን ዘርፉን እንዴት ማልማት ይቻላል? በሚሉት ጉዳዩች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ይደረጋሉ። በምክክር መድረኩም የዘርፉ ምሁራን፣ ኩባንያዎች፣ የመንግሥት አካላትና በየደረጃው ያሉ በዘርፉ ይመለከተናል የሚሉ ተዋናዮች ይሳተፋሉ።
በኤክስፖው ላይ የሚሳተፉት አካላት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ማዕድን የሚያመርቱ ኩባንያዎች፣ አነስተኛ አምራቾች እና ማንኛቸውንም ማዕድን በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ይሳተፋሉ። ሌሎች ማዕድን አምርተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ፣ ከአምራቾች ማዕድን እየተቀበሉ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እንዲሁም የማዕድን ተጠቃሚዎች (ጌጣጌጥ ማዕድናትም ሆነ ሌሎች ማዕድናት ምርቶችን የሚጠቀሙ አካላት/፣ በማዕድን ዘርፉ ያሉ ትላልቅ ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡና የሚያመርቱ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ምሁራን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳና፣ ከኖርዌይ እና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በኤክስፖው እንደሚሳተፉም አቶ አወቀ አስታውቀዋል። ከአፍሪካም ታንዛንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካን የመሳሳሉ ሀገራት የሚሳተፉበትና ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያካፈልቡት እንደሚሆን ተናግረዋል። ከ80 በላይ የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በኤክስፖው ላይ ቦታ ይዘው ራሳቸውን እንደሚያስተዋወቁ ጠቅሰው፣ ሌሎች በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በባለፈው ዓመት የተካሄደው ኤክስፖ ካሉበት ክፍተቶች አንዱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ማሳተፍ አለመቻሉ አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አወቀ፤ በዘንድሮው ኤክስፖ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና ኩባንያዎችን በተሻለ መልኩ ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይገልጻሉ። በኤክስፖው ላይ የኢንዱስትሪ፣ የኃይል ምንጭ፣ የጌጣጌጥ፣ የብረትና ብረት ነክ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ማዕድናት የዘርፉ ማሽነሪዎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል ሲሉም አብራርተዋል።
በአምናው ኤክስፖ አምራችና ገዥ የገበያ ትስስር የፈጠሩበት እንደነበር አስታወሰው፤ ዘንድሮም የማዕድን ዘርፉን ተደራሽነት ከማስፋት ባሻገር የተሻለ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል። የዘንድሮው ኤክስፖ ለየት የሚደርገው የፓናል ውይይት እንዲኖር መደረጉና ዓለም አቀፍ ተቋማት በስፋት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባሻገር ከመጀመሪያ በተገኘው ተሞክሮ በዝግጅትም ሆነ በአቀራረብ የተሻለ ኤክስፖ እንዲሆን ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አመላክተዋል።
የባለፈው ዓመት ኤክስፖ የተካሄደው ለሦስት ቀናት መሆኑ በራሱ የማዕድን ዘርፉን በደንብ ለማስተዋወቅ አልተቻለም ያሉት አቶ አወቀ፤ የብዙዎች አስተያየት የነበረው ቀኑ አጠረ፣ ሰፋ ቢደረግ የሚል እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ኤክስፖው ዘንድሮ ሰፋ ተደርጎ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንዳሉት፤ ዘንድሮ በሚካሄዱት ሦስት የፓናል ውይይቶች የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው የሚንሸራሸሩ ይሆናል። በመጀመሪያው መድረክ የኢትዮጵያ የማዕድን ኢንቨስትመንት አማራጮች ምንድናቸው፣ የማዕድን ሀብትን በመፈለግ ዙሪያ ያሉ ሥራዎችና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በኢትዮጵያም ሆነ እንደ አፍሪካ ምን ይመስላሉ የሚሉት ይታያሉ። በሁለተኛው መድረክ በዘርፉ ፖሊሲዎች ዙሪያ የዓለም አቀፍ፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች ምን ይመስላሉ? በሚሉት ላይም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ዘርፉን ለማነቃቃትና ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ውይይት ይካሄዳል። በሦስተኛው መድረክ የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ምንድነው? የሚለው የሚፈተሸበት ይሆናል።
ይህ ኤክስፖ ለዘርፉ በርካታ እድሎች ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል የሚሉት አቶ አወቀ፤ አንደኛው በማዕድን ኢንቨስትመንት ያሉ እድሎችን ማስተዋወቅና ኢንቪስተር መሳብ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለተኛው ደግሞ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሳየው ከማዕድን ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት አቶ አወቀ፣ አሁን ያለው ተሞክሮ የሚያሳየው ጥሩ ጅምር እንዳለ ነው ይላሉ።
አንድ ባለሀብት ኤክስፖው ላይ ለመሳተፍ ሲመጣ ዶላር ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ኤክስፖው በከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የበኩሉን መነቃቃት ከመፍጠር ባሻገር በተለይ አገልግሎት ሰጪዎች ሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ይህ ተጠቃሚነት እያደገ ሲሄድ ቱሪዝሙን በማሳደግና ገቢ በማመንጨት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የዘንድሮው ኤክስፖ በተሻለ መንገድ እንዲዘጋጅና የተሳካ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኤክስፖው ትኩረት ሰጥተው እንዲሳተፉና እንዲጎበኙ ማድረግ ያስፈልጋል። የዘርፉን መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ቴክኖሎጂዎችንና ሁሉንም የዘርፉን እንቅስቃሴዎችና እምቅ አቅሞች ቀረብ ብለው እንዲረዱና እንዲያወቁ ለማድረግ የሁሉም አካላት ቅንጅትና የጋራ ተሳትፎ ያስፈልጋል። ጉዳዩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቻውን አይሰራውም። ክልሎች፣ የጸጥታ አካላትና ሌሎች በዘርፉ የሚሳተፉ በርካታ አካላት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው።
የማዕድን ዘርፉ በሚገባ ቢሰራበት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ገቢ የሚያስገኝ ነው ያሉት አቶ አወቀ፤ አሁን እየተሰራ ያለው እንዳለ ሆኖ ወደፊት በዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ምን መሠራት ይኖርበታል የሚለው በመድረኩ ተነስቶ እንደሚዳሰስም ገልጸዋል። ኤክስፖውም ሆነ የፓናል ውይይቶቹ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶች ታይተው በቀጣይ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚያስችሉ ጠቁመው፤ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ወሳኝና ጥቅሙ ብዙ እንደሆነ አመላክተዋል።
‹‹በሀገራችን የማዕድን ዘርፍ ገና ያልተነካና ያልተጠቀምንበት፣ ብዙ ያልተሰራበት ሀብት ክምችት ያለበት ነው›› የሚሉት አቶ አወቀ፤ ኤክስፖው የተሳካ እንዲሆን ሚዲያው የማዕድን ሀብቱን በማስተዋወቅ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል። በዘርፉ የሚሰሩ የመንግሥት አካላትም ሆኑ የግል ዘርፉ እና ሌሎች የሚመለከተው በየደረጃው ያሉ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ሁሉም በቅንጅትና በትብብር በመሥራት ዘርፉን ማነቃቃትና ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
‹‹የማዕድን ዘርፉ ገና ያልተነካ ሀብት ነው፤ በደንብ ማስተዋወቅ አለብን፤ ካስተዋወቅነውና ካለማነው ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠርና የብዙዎችን ሕይወት መቀየር የሚችል ሀብት ነው፤ ወደፊትም ገቢ ከማስገኘት በተጨማሪ ሌላ የቱሪዝም ንቅናቄ መፍጠር የሚችል ሀብት ነው›› ያሉት አቶ አወቀ፤ ሁሉም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ያገባኛል፤ ይመለከተኛል በማለት በቅንጅት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የመጀመሪያው ‹‹የማይን ቴክስ/ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ›› በ2015ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደ መሆኑ ይታወሳል። የዘንድሮ ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ ‹‹የማዕድን ሀብታችንን የነገ ተስፋችን›› በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2016