በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር የተሳተፉ ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ርምጃ ተወሰደባቸው

አዲስ አበባ፡- በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር የተሳተፉ ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የተለያየ ርምጃ መወሰዱን የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት፤ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር የተሳተፉ ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ እንዲጠየቁና በአስገዳጅ ሁኔታ ከሀገር እንዲወጡ አድርጓል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሕገወጥ የማዕድን ማውጣትና ንግድ ተሠማርተው የነበሩ ከ100 በላይ የቻይና፣ የአፍሪካ ሀገራትና ከተለያዩ አህጉራት የመጡ ዜጎች ላይ ምርመራ በማድረግ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከተቋቋመበት 2015 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመግታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይም ከቻይና ሀገር የመጡ ሕገወጥ ግለሰቦች በቤንሻጉል ጉሙዝ፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስረድተዋል።

ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ወደ ክልሎች በማቅናት የዘርፉን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ጥረት ተደርጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለውጭ ምንዛሪ ዕድገት ትልቅ አቅም የሆነውን የወርቅ ማዕድን በቤንሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በጋምቤላ ክልሎች በስፋት የሚገኝ እንደመሆኑ ግብረኃይሉ በወርቅ ማዕድን ስፍራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከውጤት አንጻርም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ጋምቤላ ክልል ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ዕድገት ያሳየ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልልም ሰፊ የወርቅና የሌሎች ማዕድናት ክምችት መኖሩን ተከትሎ የማልማት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፤ ግብረ ኃይሉ በትግራይ ክልል እንዲሠማራ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አቶ ሚሊዮን እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመከላከል ከብሔራዊ ባንክ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል፡፡

የማዕድን ዘርፍ ለቀጣይ 10 ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ እንደመሆኑ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ዘርፉን የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የማዕድን ዘርፍ አሠራር በማጥናት ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ በመመልከት የፌደራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅር በጋራ ተቀናጅተው እንዲሠሩ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

የማዕድን ምርት ከሚገኝበት ስፍራ ወደ ባንክ ለመውሰድ ያለውን ርቀት ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ በቅርበት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን አቅም እንዲያጠናክር በትብብር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በማዕድን ዘርፉ ያለውን ሕገወጥነት ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም የቁጥጥር ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You