የዓለም አትሌቲክስ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የውድድር ዘመን የላቀ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን አወዳድሮ ከሳምንታት በኋላ ይሸልማል፡፡ ይህ ክብር በአትሌቲክስ ቤተሰቡ እንዲሁም ስፖርቱን በሚመራው የበላይ አካል ምርጫ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ እንደመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ በመሆኑም በምርጫው መካተት እንዲሁም ከመጨረሻዎቹ እጩዎች መካከል ለመካተት የተሻለ ብቃት ማሳየት ወሳኝ ነው፡፡
ላለፉት ሳምንታት በማሕበራዊ ድረገጾች ድምጽ ሲሰጣቸው ከቆዩ አትሌቶች መካከል ብልጫ ያገኙትን አምስት አትሌቶች የዓለም አትሌቲክስ አሳውቋል። አምስቱ አትሌቶች ከተለያዩ ሃገራት የተወጣጡ እና በተለያዩ ርቀቶችና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ሁለቱ ግን አፍሪካን በመወከል ከኢትዮጵያ እና ኬንያ የተገኙ ናቸው፡፡ ሁለት እጩዎች የነበሯት ኢትዮጵያ በበኩሏ በአንድ አትሌት እስከመጨረሻው የምትፎካከር መሆናን አረጋግጣለች፡፡ በመጪው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ሞናኮ ላይ በሚካሄደው ስነስርዓት በሚደረገው የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት ይፋ እስኪሆንም አጓጊነቱ ቀጥሏል፡፡
በመጨረሻው የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ አምስት አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊቷ የማራቶን ጀግና አትሌት ትዕግስት አሰፋ የዓመቱ ምርጥ አትሌት የመሆን ዕድሏ እየሰፋና ሚዛን እየደፋ መጥቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አትሌቶች በቀላሉ በማይዳፈሩትና ሮጠው ለመጨረስም ከፍተኛ ጽናትና ብቃትን በሚጠይቀው ማራቶን የድርብ ክብር ባለቤት በመሆኗ ነው፡፡
ባለፈው መስከረም ወር በተካሄደው የበርሊን ማራቶን በሴቶች የዓለም ክብረወሰን የሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው ትዕግስት አሰፋ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች አንዷ መሆኗን የዓለም አትሌቲክስ ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል፡፡ ትዕግስት ከሰበረችው የማይደፈር የማራቶን ክብረወሰን ባለፈ አስደናቂው ያለፈ ታሪኳ ትኩረት በመሳብ በመላው ዓለም እጅግ አነጋጋሪ አድርጓታል፡፡ በመላው ዓለም ያሉ አትሌቶችን በተለይም ሴቶችን ልታበረታና ልታነቃቃ የምትችል እንደመሆኗ በስፖርት ቤተሰቡ በተሰጣት ድምጽ ላይ የዓለም አትሌቲክስ ባለሙያዎች ይሁንታም ተጨምሮበት ለዓመታት ከኢትዮጵያ የራቀውን ክብር እንደምታስመልስም ይጠበቃል፡፡
በ400 እና 800 ሜትር አትሌቲክስን የጀመረችው ትዕግስት ሃገሯን በመወከል ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለች አትሌት ናት፡፡ ፊቷን ወደማራቶን ካዞረች በኋላ ግን እአአ ከ2014 አንስቶ ከተረከዝ ጅማት ሕመም ጋር ጠንካራ ትግል ስታደርግ ነው የቆየችው፡፡ ይኸው ጉዳቷ እየጠነከረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም የሕክምና ባለሙያዎች ሩጫን እንድታቆም ቢነግሯትም ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ወደ ውድድር ተመልሳ ነበር። ከሕመሙ ሙሉ ለሙሉ ማገገም አለመቻሏም እአአ በ2019 የቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶንን እንዳጠናቀቀች በድጋፍ ወደ ሕክምና ስፍራ እስከመሄድም አድርሷታል። በወቅቱ በክራንች እየታገዘች በሄደችባቸው የአውሮፓ የሕክምና ማዕከላትም በተመሳሳይ ሩጫን እንድታቆም ቢነገራትም የጽናት ተምሳሌት የሆነችው አትሌት ግን ከሕመሟ አገግማ ወደ ቀድሞ አቋሟ ለመመለስ ሳትሰለች በመስራት በጎዳና ላይ ሩጫዎች ወደ አትሌቲክስ ሕይወቷ ለመመለስ ችላለች፡፡
ከረጅም ጊዜ የሕክምና ክትትል በኋላ የመጀመሪያ ማራቶኗን በሳውዲ አረቢያ ያደረገችው አትሌቷ በወቅቱ ያስመዘገበችው 2:34:01 የሆነ ሰዓት ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ በዚሁ የበርሊን ማራቶን 2:15:37 በሆነ ሰዓት በመሮጥ የውድድሩን ክብረወሰን እንዲሁም የዓለም ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላ ነበር፡፡ አትሌቷ የገባችበት ሰዓት ቀድሞ ከነበራት 19 ደቂቃዎችን ያሻሻለችበት መሆኑ በርቀቱ ያላትን የወደፊት ተስፋ በግልጽ ያመላከተ ነበር፡፡ ከዓመት በኋላ ዳግም በሮጠችበት የበርሊን ማራቶንም ከነበራት ሰዓት ወደ 4 ደቂቃ በማሻሻል 2:11:53 በሆነ ሰዓት ነበር የዓለም ክብረወሰኑን ከእጇ ያስገባችው፡፡
የአትሌቷን ጥንካሬ የሚያጎላውም በርቀቱ አስቀድሞ ከተያዘው ክብረወሰን በ3 ደቂቃዎች ቀድማ መግባቷ ሲሆን፤ እንደወንዶች ፈጣን ሰዓት በቶሎ በማይመዘገብበት የሴቶች ማራቶን ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች መግባት ይቻላል የሚለውንም ያስመሰከረ ሆኗል፡፡ በመሆኑም የአትሌቷ ታሪክ ቀያሪ ድል እንዲሁም በቀላሉ በማይደፈረው ማራቶን የዓለም ቁጥር አንዷ አትሌት መሆኗ በምርጫው ብልጫ እንደሚያስገኝላት ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በዚህ ምርጫ በእጩነት ብትካተትም ያገኘችው ድምጽ ግን ከመጨረሻዎቹ አምስት አትሌቶች መካከል አንዷ እንድትሆን አላስቻላትም፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም