የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩና የኩባንያዎቹ የዝግጅት ሥራዎች

የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎችም አሏቸው፡፡ ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚከፍልበትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል፡፡ በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች (Integrated Agro-Industry Parks)፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፡፡ ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ፡፡ መንግሥት አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እስካሁን ድረስ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ከባቱ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የ‹‹ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በሀገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ፓርኩ በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ሲሆን የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የማር፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡

የፓርኩ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በ271 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እስከ አንድ ሺ ሄክታር መሬት መሸፈን የሚችል ቀጣይ ዙር ግንባታ ሊከናወንለት እንደሚችል የፓርኩ የአዋጭነት ጥናት ያሳያል፡፡ በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው 148 ባለሀብቶችን ማስተናገድ ይችላል፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከ70 ሺ እስከ 100 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው እንዲሠሩ የፓርኩን ገፅታና አቅም ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ መርሃ ግብር በወርሃ ነሐሴ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱና በወቅቱም ከ40 በላይ ባለሀብቶች በፓርኩ ለመሰማራት ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጌታሁን አዱኛ እንደሚናገሩት፣ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ባከናወናቸው ተግባራት ፈቃድ የወሰዱ 29 ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ገብተው በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ባለሀብቶቹ የሚሰማሩባቸው የአግሮ-ፕሮሰሲንግ (ግብርና ማቀነባበር) ዘርፎች የማርና ሰም፣ የምግብ ዘይት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ (ቲማቲም፣ ድንች፣ ጭማቂ… )፣ የቡና፣ የአቮካዶ ዘይት፣ የስጋ፣ የወተት፣ የእንስሳት መኖ፣ የፓስታና ማካሮኒ፣ የሕፃናት ምግቦች ማምረትና ማቀነባበር ሥራዎች ናቸው፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አራት ባለሀብቶችን ወደ ፓርኩ ለማስገባት ታቅዶ ለሰባት ባለሀብቶች ፈቃድ መስጠት ተችሏል፡፡ ባለሀብቶቹ በምግብ ዘይት ምርት እንዲሁም በስጋ እና አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበር ዘርፎች የሚሰማሩ ናቸው፡፡ ፈቃድ ከተሰጣቸው ኩባንያዎች መካከል ‹‹ቲኬ ግሩፕ›› (TK Group) የተባለ ኩባንያ ሼድ ገንብቶ የማሽን ተከላ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ኩባንያው በምግብ ዘይት እና በእንስሳት መኖ ምርትና ማቀነባበር ሥራ ላይ የሚሰማራ ሲሆን፣ ለሥራውም ሁለት ነጥብ ስምንት ሄክታር መሬት ተረክቧል፡፡ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ምርት ማምረት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌሎቹ ድርጅቶች ደግሞ መሬት ተረክበው የባንክ ብድር ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም የባንክ ብድር ተፈቅዶላቸው ማሽን ማስገባት ጀምረዋል፡፡ ለአብነት ያህል መንግሥት ለናሙና ወደገነባቸው ስድስት ሼዶች ውስጥ ከገቡት አምራቾች መካከል ሁለቱ የብድር ፈቃድ ሂደቶችን አጠናቅቀው ማሽኖችን እያስገቡ ይገኛሉ። ወደ ፓርኩ ገብተው ሥራ ለመጀመር ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውንም አቶ ጌታሁን ይናገራሉ፡፡

የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ ‹‹ፓርኩ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች የተሟሉለት ነው፡፡ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች አሉት፡፡ ለሁሉም ፓርኮች የመብራት ሰብስቴሽኖችን የሚገነባው የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የሰብስቴሽን ግንባታ ስለዘገየብን ከ35 ሜጋዋት በላይ ኃይል ከአካባቢው በመሳብ ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች የዝግጅት ሥራዎቻቸውን እንዲቀጥሉ አድርገናል፡፡ በውሃ አቅርቦት ረገድ ደግሞ፣ በአካባቢው ያለው ውሃ ጨዋማ ነው፡፡ ውሃውን ለማጣራት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ከፓርኩ ከ50 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ በመጓዝ በጢዮ ወረዳ (አርሲ) አምስት የውሃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር ታቅዶ ሦስቱ እንዲቆፈሩ ተደርጓል፤ መስመር የመዘርጋት ሥራም ተጀምሮ ነበር፡፡ በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ሥራው እንዳይስተጓጎል ለተወሰነ ጊዜ ከባቱ ከተማ ወደ ፓርኩ ውሃ ለማስገባት ታቅዷል›› በማለት ይገልፃሉ፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፣ ከፓርኩ ጋር ትስስር ያላቸውና ግንባታቸው የተጠናቀቀ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት ያሉ ሲሆን፤ የማዕከላቱ ዋና ተግባር የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትና በብዛት ሰብስቦ ለፓርኩ አምራቾች ማቅረብ ነው፡፡ ወደ ፓርኩ የሚገቡት ባለሀብቶች ከሽግግር ማዕከላቱ ጋር በሚፈጥሩት ትስስር አርሶ አደሩን ጨምሮ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል። በሻሸመኔ፣ መቂ፣ ዶዶላ፣ ባሌ ሮቤ፣ ኢተያ እና ኦለንጪቲ ከሚገኙት ማዕከላት መካከል የሻሸመኔና የመቂ ማዕከላት የመሠረተ ልማት ግንባታዎቻቸው ጭምር ተጠናቀዋል፡፡ አራቱ ማዕከላት ደግሞ የሕንፃ ግንባታቸውን አጠናቀው መሠረተ ልማቶችን (ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ…) የማሟላት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት ማጠናቀቂያ የሁሉንም ማዕከላት ግንባታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ሥራዎች ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡

የፓርኩ ግንባታ ብዙ የሰው ኃይልና ግብዓት ይፈልግ እንደነበር አቶ ጌታሁን ጠቅሰው፣ በፓርኩ ግንባታ ወቅት በርካታ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ አምራቾች ሥራ ሲጀምሩ ደግሞ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለፓርኩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ያስረዳሉ፡፡

‹‹ፓርኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ ሲገነባ ያስገኛል ተብሎ የታሰበው ዋና ጥቅም የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትና በመጠን በመጨመር እንዲሁም የገበያ ዕድል በመፍጠር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡›› ያሉት አቶ ጌታሁን፤ አሁን ባለሀብቶች ገና ወደ ፓርኩ ለመግባት በዝግጅት ላይ በመሆናቸው ስለአርሶ አደሩ ሰፊ ተጠቃሚነት ለመናገር ጊዜው ገና ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀው ‹‹ቲኬ ግሩፕ›› ዘይት የሚያመርተው ከአኩሪ አተር መሆኑን ጠቅሰው፣ ለምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓት (አኩሪ አተር) እየሰበሰበ እንደሚገኝና በዚህም አኩሪ አተር አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ‹‹የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርውን ዘርፍ ለማሳደግ ታልሞ የተገነባ በመሆኑ የሚጠቀመው ግብዓት የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን ነው፡፡ በፓርኩ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አርሶ አደር ነው። የፓርኩ አምራቾች የሚጠቀሙት ጥሬ ዕቃ የአካባቢውን የግብርና ምርት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ግብርናውን በማዘመንና አምራችነቱን በመጨመር ለምግብና ለገበያ ከሚያውለው ምርት በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ትርፍ ምርት እንዲያመርት እየተሠራ ነው፡፡ በቀጣይ አምራቾች በማር፣ በስጋ፣ በዶሮ፣ በወተት፣ በጥራጥሬ፣ በዘይትና በሌሎች ዘርፎች ወደ ሥራ ሲገቡ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የአካባቢው ኅብረተሰብ የገበያ ዕድል እንዲያገኝም ያደርጋል›› በማለት ፓርኩ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ ያስረዳሉ፡፡

የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል፡፡ ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You