
አዲስ አበባ፡– በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሎተሪ ሽያጭና ዕድል ጨዋታዎች 329 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም ገልጿል፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሎተሪ ሽያጭና ዕድል ጨዋታዎች 329 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ገቢው የእቅዱን 85 ነጥብ 67 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ59 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ፡፡
ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 247 ነጥብ 3 ሚሊዮኑ የተጣራ ትርፍ መሆኑን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ111 ሚሊዮን ብር ወይም የ55 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተገኘው ውጤት ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካት በሚችልበት ቁመና ላይ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ የሚያገኘው አጠቃላይ ገቢና ትርፍ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ የከተሞች መስፋፋት፣ ሕዝቡ ተቋሙ ላይ ያለው አመኔታ ከፍተኛ መሆንና የመግዛት ፍላጎት እያደገ መምጣት እንዲሁም አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው የቅስቀሳ ሥራዎች ለውጤቱ መገኘት በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ዕጣዎች ከወጡ በኋላ ሐሰተኛ ትኬት አሠርተው ሽልማት ለማግኘት የሚሞክሩና በተለይ ፈጣን ሎተሪዎች ላይ ሐሰተኛ ቁጥሮችን ለጥፈው ዕድለኛ መሆናቸውን በመግለጽ ለማውጣት የተቸገሩ በማስመሰል ኅብረተሰቡን የሚያታልሉ መኖራቸውን አስታውሰው፤ አንድ አሸናፊ ያሸነፈበትን ዕጣ ቁጥር ይዞ ሲቀርብ አስተዳደሩ ክፍያ የሚፈጽመው የትኬቱን ትክክለኛነት ከአታሚው ድርጅት አረጋግጦ ነው ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡም ገንዘቡን በአጭበርባሪዎች እንዳይበላ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የዕድል ጨዋታን የማከናወን ሕጋዊ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በገበያዎች አካባቢ ከሚደረጉ የዕድል ጨዋታዎች እስከ ትልልቅ ተቋማት የሚሳተፉባቸው የዕድል ጨዋታዎች ይከናወናሉ፡፡ ይህን ሕገወጥ ተግባር ለመከላከል አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አደረጃጀቱን የማስተካከልና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ቴዎድሮስ፤ በቀጣይነትም ከወረቀት ሎተሪ ባለፈ ዲጂታል ሎተሪዎችን በተጠናከረ መልኩ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ ይሠራል ብለዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም