በዓለም አትሌቲክስ የተለያየ ደረጃ የተሰጣቸው ከ5 ኪሎ ሜትር እስከ ማራቶን ድረስ በርካታ የጎዳና ላይ ውድድሮች በሳምንቱ መጨረሻ ተካሂደዋል:: ከነዚህ መካከል በ2023 የቤይሩት ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፈዋል::በሴቶች ሙሉጎጃም ብርሃን በወንዶች ደግሞ ጋዲሳ ጣፋ የውድድሩ አሸናፊዎች ናቸው::
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመድረኩ በርካታ ጊዜ መንገስ የቻሉ ሲሆን አሁንም የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር ጭምር ማሸነፋቸውን ቀጥሎበታል:: በወንዶች አትሌት ጋዲሳ ጣፋ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ሲያሸንፍ 42 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ 2፡10፡34 ሰዓት ፈጅቶበታል:: አትሌቱ በ5 እና 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድሮችና የአንድ ማይልና የ10 ማይል የጎዳና ውድድሮች በመሮጥ የሚታወቅ ሲሆን ፈጣን ሰዓቶችም አሉት:: ከዚህ ቀደም በቤይሩት ማራቶን የቦታው ፈጣን ሰዓት ተመዝግቦ የነበረው እአአ በ2018 በረጅም ርቀት ሯጩ ሞሮካዊ አትሌት ሞሃመድ ኤል አራብይ ሲሆን ሰዓቱም 2፡10፡41 ነው:: ኢትዮጵያዊው አትሌት ጋዲሳም 7 ሰከንዶችን በማሻሻል የቦታውን ፈጣን ሰዓት የግሉ ማድረግ ችሏል:: በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የመድረኩን የመጀመሪያ ድላቸውን ያስመዘገቡት እአአ በ2004 ሲሆን አትሌት እሼቱ በቀለ የመጀመሪያው ባለድል ነበር:: በዚህ ውድድር ቀደም ሲል ጋዲሳን ጨምሮ 8 ወንድ አትሌቶች ድል ሲቀናቸው ጋዲሳ ከሁሉም ወንድ አትሌቶች የተሻለ ውጤትን በማስመዝገብ ያሸነፈ አትሌት መሆን ችሏል:: አትሌት ጋዲሳ አንደኛ ደረጃን በመያዝ የወርቅ ሜዳለያ ተሸላሚ በሆነበት ውድድር አትሌት ጎጃም በላይነህ እሱን ተከትሎ በመግባት የብር ሜዳለያ ተሸላሚ መሆን ችሏል::
በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ደግሞ አትሌት ሙሉጎጃም ብርሃን ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ የቦታውን ክብረወሰን በእጇ በማስገበት አሸንፋለች:: አትሌቷ ውድድሩን በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ 2፡27፡48 የሆነ ሰዓት ፈጅቶባታል:: ይህም ቀደም ሲል የቦታው ፈጣን ሰዓት ሆኖ በትውልደ ኬንያዊቷ የባህሬን አትሌት ኢኡኒሴ ቹምባ እጅ የነበረውን ክብረወሰን እንድትረከብ አስችሏታል:: ባህሬናዊቷ አትሌት የቦታውን ክብረወሰን እአአ በ2017 2፡28፡38 ሰዓት ይዛ መቆየት ችላ ነበር:: አትሌት ሙሉጎጃም የቀድሞውን ሰዓት ከ1 ደቂቃ በላይ በማሻሻል ለ6 ዓመት ተይዞ የቆየውን የውድድሩን ክብረወሰን በእጇ ባስገባችበት ፉክክር አትሌት ጌጤ ዱከለ ሁለተኛና የብር ሜዳለያ አሸናፊ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች:: አትሌት አስመሬ በየነ ደግሞ ውድድሯን በሦስተኝነት አጠናቀ ነሐሳ ሜዳሊያውን ወስዳለች:: በቤይሩት ማራቶን ሙሉጎጃምን ጨምሮ አስር ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቀደም የነገሡ ሲሆን የመጀመሪያው ድል እአአ በ2007 በአትሌት አዳነች በየነ አማካኝነት ሊመዘገብ ችሏል::
በመድረኩ በሁለቱም ጾታዎች ላሸነፉ አትሌቶች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን 1ኛ ደረጃን በመያዝ ላሸነፉ አትሌቶች 3 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ለፈጸሙ 2 ሺ የአሜሪካን ዶላር እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ላጠናቀቁ አትሌቶች 1 ሺ አሜሪካን ዶላር በሽልማት መልክ ማግኘት ችለዋል::
ሌላው በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደው የቦስተን ግማሽ ማራቶን ሲሆን ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ማሸነፍ ችለዋል:: አትሌቶቹ እጅግ ቀዝቃዛማ አየርን አስተናግዷል በተባለው ውድድር አረንጓዴ ጎርፍን በመሥራት ባሸነፉበት የቦስተን ግማሽ ማራቶን አትሌት ፎይተን ተስፋዬ በቀዳሚነት ጨርሳለች:: አትሌቷ የ21 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 1፡08፡46 ሲሆን፣ አትሌቷ በመካከለኛና በረጅም ረቀቶች የግሏን ፈጣን ሰዓቶች ማስመዝገብ ችላለች:: ይህ የመጀመሪያው የግማሽ ማራቶን ድሏ ሆኖም ሊመዘገብ ችሏል:: አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ውድድሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀች ሲሆን ውድድሩን ለመጨረስ 1፡09፡00 የሆነ ሰዓትን ፈጅታለች:: አትሌት ፅጌ ገብረ ሰላማ ውድድሩን ሦስተኛ ሆና ስታጠናቀቅ 1፡09፡06 የሆነ ሰዓትን አስመዝግባለች:: መስታወት ፍቅሩ አምስተኛ፣ ቡዜ ዲሪባ ስድስተኛ እና አትሌት በየኑ ደገፋ አስረኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል::
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች 150 ሺ ዶላር የሚበረከትላቸው ሲሆን ውድድሩን በሁለተኝነት የሚያጠናቅቁ አትሌቶች 75 ሺ ዶላር ሲያገኙ ሦስተኛ በመሆን የሚያጠናቅቁ ደግሞ 40 ዶላርን የሚሸለሙ ይሆናል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም