የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ይካሄዳል

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይከናወናል። የፊታችን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማሰናዳት ዝግጅቷን አጠናክራ እንደቀጠለች የተጠቆመ ሲሆን፣ እንግዶቿን በአግባቡ አስተናግዳ ለመሸኘት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጥ ምረት ዝግጅት እየተደ ረገም ይገኛል።

የአፍሪካ ቦክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በዱባይ እንደሚደረግ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ የቦታ ለውጥ ለማድረግ ተገዷል። መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ‹‹በአፍሪካ እንጂ በሌላ አህጉር መሆን አይገባውም›› የሚል መከራከሪያ በመቅረቡ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳራዘመና የቦታ ለውጥ እንዳደረገ ታውቋል።

ከቦታ ምርጫ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውዝግብ ሲያስተናግድ የቆየው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በመጨረሻም በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ተወስኗል። ጉባዔውን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟት እንደነበረ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በዱባይ ማድረግ የተፈለገበት ምክንያት የዓለም አቀፍ ቦክስ ፌዴሬሽን መስከረም 28 ቀን በዱባይ ለማድረግ ማቀዱን ተከትሎ እንደሆነና ከወጪ ቁጠባ አንፃር ታስቦ እንደነበር ተገልጿል። ሆኖም የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን የመተዳደሪያ ደንቡን አንቀጽ 17.7 በመጥቀስ ‹‹የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ምርጫ በአፍሪካ ብቻ መሆን ይገባዋል›› በሚል በጻፈው ደብዳቤ መሠረት በዱባይ ሊደረግ የነበረው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሊሰረዝ ችሏል።

ምርጫው በአፍሪካ መከናወን እንዳለበት ከተወሰነ በኋላ፣ ኢትዮጵያ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማስተናገድ ጥያቄ በማቅረቧ የአባላቱን ድጋፍ ማግኘቷን ተከትሎ ዕድሉ ተሰጥቷታል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ጉባዔውን ማስተናገዷ ቅሬታ የፈጠረባቸው የአፍሪካ አገሮች መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ መድረክ ስፖርት ለመምራት ዕጩ ፕሬዚዳንት ማቅረቧን ተከትሎ ለማሸነፍ ዕድል ይሰጣታል የሚል ጥርጣሬ መኖሩ እንደነበረ ተጠቁሟል። ተናግረዋል። በሌላ በኩል ምርጫውን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግቦች ካስነሱ ጉዳዮች መካከል የምርጫውና የዕጩዎች ውክልና ሲሆን፣ 30 ሀገሮች ለምርጫ በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ትችት ሰንዝረዋል። ይህም የሆነው ዕጩ ሆነው ከቀረቡት መካከል የተለያዩ የሙስና ክስ የቀረበባቸውና በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን የታገዱ መኖራቸውን ተከትሎ ነው።

በሙስና ቅሌት ስማቸው ከተጠቀሰው መካከል የካሜሮኑ ዕጩ በርትራንድ ሜንዱጋ ይገኙበታል። እ.ኤ.አ. ከ2022 የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽንን ለመምራት የተመረጡት ካሜሮናዊው በርትራንድ የግል ፍላጎታቸውን ያንፀባርቃሉ የሚል ክስ የተነሳባቸው ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በላይ መምራት ሳይችሉ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ቦክስ ፌዴሬሽን ውስጥ ያላቸው ውክልናን ተነጥቀዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዘንድሮም ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አባል አገሮች ተቃውሞ እየደረሰባቸው ነው። ሌላው በምርጫው ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት የዑጋንዳ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሞሰስ ሙሐንጊ ሲሆኑ፣ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብን በመጣሳቸው፣ እንዲሁም በሀገራቸው የሕግ ጥላ ሥር ውለው ክስ የቀረበበቸው ናቸው። ሆኖም ከተለያዩ ሀገሮች ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ቅሬታ በማስነሳቱ እስከ ቅርብ ጊዜ በምርጫ ውስጥ እንደሚሳተፉ ቢታወቅም፣ በመጨረሻ ራሳቸውን አግልለዋል።

የምርጫ ሒደቱን ተከትሎ ውስብስብ ሒደትን ማለፋቸውን የሚያነሱት ኢትዮጵያዊው ዕጩ፣ በምርጫው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ቀዳሚ ናቸው። ኅዳር 8 ቀን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሚከናወነው ምርጫ የካሜሮኑ ዕጩ በርትራንድ ሜንዱጋ እንዲሁም የሞሮኮ ሞሐመድ ቦድር ይገኙበታል።

ኢትዮጵያን የወከሉት አቶ ኢያሱ ምርጫውን ማሸነፍ ከቻሉ በአፍሪካ መድረክ ስፖርቱን በመምራት ከቀድሞ የካፍ ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በመቀጠል ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ ይሆናሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You