«በሕግ ያስቀጣል»ቃል ወይስ ተግባር?

ወቅቱ ክረምቱ አልፎ በጋው የገባበት፣ ፀሀይ ከልቧ ደምቃ የምትወጣበት ነው፡፡ እርግጥ ነው ጥቅምት ሲብት አንስቶ ‹‹አለሁ›› ማለት የጀመረው ቅዝቃዜ ሕዳር ጀምሮ ይበረታል፡፡ እንዲያም ሆኖ የበጋዋ ፀሀይ አኩርፋ አትውልም። ማለዳ በስሱ ታይታ እስከ ማምሻው ዘለቄታ አናት ስትበሳ ትውላለች፡፡

የበጋ ፀሀይን ነገር ማንሳቴ ያለምክንያት አይደለም። ፀሀይን ስናነሳ ከበጋው መከተል ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙትን እውነታዎች አንዘነጋም፡፡ መቼም ሰሞኑን የከተማችንን የጽዳት ገጽታ ላስተዋለ ከማዘን አልፎ እስከማፈር መድረሱ አይቀርም። ይህ አይነቱ አጋጣሚ በባሰ ቁጥር የፀሀይዋ አብሮ ማበር ጉዳዩን ያባብሳል፡፡

የቆሻሻ ክፋትና ጉዳት ክረምት ከበጋ ብለው አይመርጡትም፡፡ እንዲህ ይማረጥ ከተባለ ግን የቆሻሻ መጥፎነት በበጋ ወቅት ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ሰሞኑን በመንግስት ደረጃ ግልጽ እንደሆነው ጉንፋን መሰል በሽታ ህብረተሰቡን እያጠቃው ነው፡፡ ይህ ህመም ሰዎች በመዘናጋት ችላ ይበሉት እንጂ ውጤቱ የዋዛ አይመስልም።

እንደሚታወቀው ለእንዲህ አይነቱ ችግር አንዱ መንስኤ የቆሻሻ አወጋገዳችን ክፍተት ነው፡፡ ችግሩ ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም ፡፡ ለችግሮች እንደመፍትሄዎች ተቀምጠዋል የሚባሉ ደንብና መመሪያዎች ስም ብቻ የመሆናቸው እውነት እንጂ፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ናት፡፡ የስሟን ግዝፈት ያህልም በቆሻሻዋ ክፋት ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ይህ እውነት እንዳለ ሆኖ በዚህ ችግር ዙሪያ እንደ ህግ የሚቀመጡ ጉዳዮች አለመተግበራቸው አሳዛኝም፣ አስገራሚም ያደርገዋል፡፡

‹‹ወዳጆቼ!›› ልብ ብላችሁ ከሆነ በየግድግዳው፣ በየቆርቆሮውና በተገኘው ጥጋጥግ ሁሉ ‹‹ቆሻሻ መጣል በህግ ያስቀጣል›› የሚል የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ ደምቆ ይታያል፡፡ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ህግ መቅረጹ አይከፋም፡፡ የማይተገበርን ጉዳይ ህጋዊ ሰውነት አሸክሞ ቃል ብቻ ማድረግ ግን ፈጽሞ አያስጨበጭብም፡፡

ይህን ሀሳብ ደፍሮ ለመናገር ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹በህግ ያስቀጣል›› የሚሉ ጽሁፎች በተለጠፉባቸው ስፍራዎች ተጠቃሚዎች በኩራት ቆሻሻ መጣልን ህጋዊ ያደርጋሉ፡፡ በግልጽ፣ በገሀድ መጸዳዳትን ይተገብራሉ፡፡ ጉዳዩ እንደተባለው በህግ የሚያስጠይቅ፣ የሚያስቀጣ ከሆነ ስለምን አይጠየቁም፣ እንዴትስ አይቀጡም ?

‹‹በህግ ያስቀጣል›› የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ከጀመርን አይቀር ሌሎች ትዝብቶችን መቃኘቱ አይከፋም፡፡ ሲጋራ በዓለማችን ገዳይ ከሚባሉ ጎጂ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በቀላሉ ከሚያውከው ጭስና ሽታው በዘለለ የሚያስከትላቸው መልከ ብዙ የጤና ችግሮች በእጅጉ የከፉ ናቸው፡፡ ይህ እውነታ በግልጽ በመታወቁ የሲጋራን ተጠቃሚነት ሊያሳጥሩ የሚችሉ አንዳንድ ርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ርምጃዎች አንዱና ዋነኛው ህብረተሰቡ በሚገኝባቸው ስፍራዎች ሁሉ ‹‹ሲጋራ ማጨስ በህግ ያስቀጣል›› የሚለው መመሪያ ነው፡፡

ይህ መመሪያ ህግ ነው ተብሎ በወጣ ሰሞን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ተግባራዊ የማድረግ ሩጫው ፈጣን ነበር ፡፡ በወቅቱ መታዘብ ለቻለ ሲጋራ የያዙ ሰዎች ከተከለከሉት ስፍራዎች ፈቀቅ ብለው ይጠቀሙ ነበር፡፡ ለምን ከተባለ ‹‹በህግ ያስቀጣል›› የሚለውን ትዕዛዝ , በማክበር፡፡

አሁን ላይ ግን በብዙ ቦታዎች ግዴለሽነቱ ተመልሷል ማለት ያስደፍራል፡፡ አንዳንዶች ‹‹ሲጋራ ማጨስ በህግ ያስቀጣል›› የሚለውን ማስታወቂያ ተደግፈው ሲጋራቸውን ሲያቦኑ ታዛቢ እንጂ ጠያቂ የላቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጭምር እያዩ የማለፋቸውን ጉዳይ ልብ ይሏል፡፡ ‹‹በህግ ያስቀጣል የሚለው›› እውነት መባከኑም እንዲሁ።

‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› እንዲሉ አንዱ ጉዳይ ሲነሳ ሌላውን መምዘዙ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ‹‹በህግ ያስቀጣል›› የሚለው ጉዳይ መባከኑን የሚያሳይ ሌላ ጉዳይ ላንሳ፡፡ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ትኬቶች ላይ ያለውን ‹‹በህግ ያስቀጣል›› ይሉትን የማሳሰቢያ ጽሁፍ ፡፡

በየጊዜው እየጨመረ ከሚታየው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ጋር ተየይዞ በርከት ያሉ አማራጮች መኖራቸው ይታወቃል።ከእነዚህ አማራጮች መሀል የባቡር፣ የአውቶቡስና የሸገር ትራንሰፖርት አገልግሎቶች ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

በእነዚህ የትራንስፖርት መጠቀሚያዎች ተገቢው ሂደት ይኖር ዘንድ ትኬቶች በስርዓት ተዘጋጅተው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ተሳፋሪው በቆረጠው ትኬት መሰረትም በወጉ እንዲጠቀም ይሆናል፡፡ እንዲህ ማድረጉ የነበረና አሁንም ያለ ስርዓት ነው፡፡ ሁሌም ትኬቶችን ስናስብ ደግሞ ‹‹ትኬት ሳይዙ መጓዝ በህግ ያስቀጣል›› ይሉትን ቀጭን ትዕዛዝ መሰል መመሪያ አንረሳውም፡፡

ይህ እንደ ህግ በትኬቱ ላይ የተነቀሰው ቃል ከትኬቱና ከተሳፋሪው ጋር ለዓመታት የቀጠለ ነው። የህጉ ተግባራዊነት ግን በገሀድ ታይቶ አያውቅም፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት በተለይ በከተማ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በነጻ የመሄድ ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡

እንዲህ ለመሆኑ ባቡሩ በተመደበለት የደቂቃ ቆይታ መድረስ አለመቻሉና ተሳፋሪው ያለቅጥ መብዛቱ ሰበብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አሁንም በትራንስፖርቱ ሂደት ‹‹ትኬት ሳይዙ መጓዝ በህግ ያስቀጣል›› ይሉት ብሂል ከቃል ያለማለፉ ከልብ ያስተዛዝባል፡፡

መቼም ይህ ‹‹በህግ ያስቀጣል›› ይሉት አባባል አይገባበት ቦታ የለም፡፡ ‹‹በህግ ያስቀጣል›› የሚለውን የቃል ብክነት ካነሳን አይቀር ሌላውን ትዝብቴን ላክል። የድምጽ ብክለትንና ተቀምጠዋል የሚባሉ የህግ አግባቦችን ፡፡

አንዳንዶች በተለያዩ አካባቢዎች የሚያካሂዷቸው የንግድና ስራ ምርጫዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእነዚህ ምርጫዎቻቸው ሲንቀሳቀሱ ስራዎቹን መተዳዳሪያቸው በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ሁሉም ናቸው ባይባልም ብዙ ጊዜ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ከግልጋሎቶቻው ጎን ለጎን ሞቅ ባለ ሙዚቃ ታዳሚዎቻቸውን ማዝናናት ይሻሉ፡፡

ይህን ደማቅ ሙዚቃ ሲጠቀሙ ግን በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች ነፃነት ቁብ ሰጥቷቸው አይደለም፡፡ ባሻቸው ጊዜና ሰዓት ከጣራ በላይ የሚለቁት ሙዚቃ በሚመለከታቸው አካላት ‹‹የድምጽ ብክለት›› የሚል ስም ተችሮት በርካቶችን ሲያውክ ይስተዋላል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ነዋሪዎች በሚገኙበት ሰፈር የሚከፈቱ የብረታብረት፣ የእንጨት መሰንጠቂያዎች፣ የብሎኬት ማምረቻዎችና ሌሎችም ቀን ከሌት ሳይለዩ ማሽኖቻቸውን ያስጮሀሉ፡፡ የእነሱ ስራ የእንጀራና የገቢ ጉዳይ ቢሆንም ስለሌሎች መረበሽና ሰላም ማጣት ማንም ትኩረት የሚሰጠው አይሆንም ፡፡

ይህ አይነቱን እውነታ ይመርመር ከተባለ ግን የተጠቀሱት ድርጊቶች በሙሉ ‹‹በህግ ያስጠይቃሉ›› የሚባሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ይባል እንጂ ህጎቹ ህጋዊ መሰረት ይዘው በተግባር ሲተረጎሙ አይስተዋልም። በእኔ ዕምነትና እሳቤ ግን ህግ ይሉትን ታላቅ ጉዳይ ላይተገብሩ በቃል ብቻ ማስቀረቱ ከብክነትና ኪሳራ በላይ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ‹‹በህግ ያስቀጣል፣ ያስጠይቃል›› ይሉት አባባል በራሱ ህግ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ‹‹አበቃሁ››!

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You