የታዛው ስር ዋርካ …

ልጅነት ማርና ወተት …

ልጅነቷ እንደ እኩዮቿ ነው፡፡ ከሜዳ ከመስኩ፣ ስትሮጥ ትውላለች፡፡ በትንሽ ነገር ደስ ይላታል፡፡ ዕንባና ሳቅ አይለያትም፡፡ በየሰበቡ ታለቅሳለች፡፡ ይህ የሕጻንነቷ ጊዜ ለእሷ የተለየ ነው፡፡ ወላጆቿ በስስት ያይዋታል፡፡ ባልንጀሮቿ ለጨዋታ ይጠሯታል፡፡

ውዴ ለቤተሰቦቿ ልጅ ብቻ ነች፡፡ ማንም ጉዳት ድካሟን አይሻም፡፡ ሁሉም ስትወጣ ስትገባ በፍቅር እየሸኘ ይቀበላታል፡፡ እናት አባቷ የእሷን ዓለም ማየት ይሻሉ፡፡ ልጃቸው በወጉ ብትማር ደስ ይላቸዋል፡፡ በሆታና ዕልልታ ተድራ፣ በልጆቿ አያት ብታደርጋቸው ከልብ ይመኛሉ፡፡

አሁን ውዴ በዕድሜ ከፍ ብላለች፡፡ ልጅነቷን ተሰናብታ ለወላጆቿ አድራለች፡፡ የታዘዘችውን እየሠራች ቤተሰቡን እየደገፈች ነው፡፡ ወጣትነቷ ሊያብብ፣ ውበቷ ሊታይ ጀምሯል፡፡ እንዲህ ሲሆን ወላጆች ብዙ ያስባሉ። ጎረምሶች ያማትራሉ፤ ዝምድናን የሚሹ ዓይናቸውን ይጥላሉ፡፡

እንግዳዋ ወይዘሮ …

አንድ ቀን በእነ ውዴ መንደር አንዲት እንግዳ ከአዲስ አበባ መምጣታቸው ተሰማ፡፡ ሴትየዋ እንግዳ ቢሆኑም ጠጉረ ልውጥ አይደሉም፡፡ ተወልደው ያደጉት በእነ ውዴ አገር ‹‹ብቸና›› ውስጥ ነው፡፡ ኑሮና ሕይወት ቢያርቃቸውም አንዳንዴ ብቅ እያሉ ዘመድ ይጠይቃሉ።

ውዴ ስለ አዲስ አበባ ሲወራ ሰምታለች፡፡ ብዙዎች ወርቅ ይታፈስበታል፤ ብር ይቆጠርበታል ብለዋታል። ቤተሰቦቿ ለከተማው ያላቸው ስሜት የተለየ ነው። እንግዳዋን ጨምሮ በርካቶች ስፍራው ደርሰው ኑሮ እንደለወጣቸው ያውቃሉ።

አንድ ማለዳ በእነ ውዴ ቤት በርከት ያሉ ሰዎች ደርሰው በር አንኳኩ፡፡ እንዲገቡ ተፈቅዶ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ በአካባቢው አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ናቸው። ሳይቀመጡ በፊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የውዴ ወላጆች ‹‹ልጃችሁን ለልጃችን›› ተባሉ፡፡

ሰዎቹ በዚህ ብቻ ዝም አላሉም፡፡ ሀሳባቸውን ማብራራት፣ መተንተን ያዙ፡፡ ውዴ የታጨችው ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ለመጡት ወይዘሮ ልጅ ነው። ልጃቸው በሥራ ምክንያት ባገር የለም፡፡ እሱ በአካል ባይገኝም እንደወጉ ክብር እናት ሽማግሌዎች ልከው አስጠይቀዋል፡፡

ሁኔታው ድንገቴ ቢሆንም እናት አባት አላንገራገሩም። ለደንቡ ጥቂት መክረው ጋብቻውን በደስታ ተቀበሉ፡፡ ሴትዬዋ ከአዲስ አበባ መምጣታቸው የቤተሰቡን ስሜት ገዝቷል፡፡ ሙሽራው ውጭ አገር ነው መባሉ ኩራት ሆኖ ሁሉም በይሁንታ ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ውዴ በእሷ ላይ የተመከረውን ሰምታለች፡፡ ጉዳዩ ቢያስደግጣትም አልተቃወመችም፡፡ ካለችበት የተሻለ ዓለም እንደሚቆያት ስታስብ ነገዋን ናፈቀች፡፡ ወርቅ በሚታፈስባት፣ ብር በሚቆጠርባት ከተማ ምቹ ትዳር መያዝን አልጠላችም፡፡ ኑሮው ከብቸና መብለጡን ያመኑ ሁሉ በጋብቻው ተስማሙ፡፡ ዕድለኛነቷ ያስቀናቸው፣ ዕጣ ፈንታዋ የገረማቸው ባልንጀሮቿ እሷን መሆን ተመኙ፡፡

ስንብት …

አሁን ትንሽዋ ውዴ ወላጆቿን ልትተው፣ አገር ቀዬውን ልትርቅ ነው፡፡ እናት አባት ቆመው ባይድሯትም በዓይን ላላዩት፣ ባገር ለሌለው አማታቸው ሰጥተዋታል። በቃ! ከዚህ በኋላ ውዴ የባሏን እናት እጅ ይዛለች፡፡ ወላጆቿን፣ ጓደኞቿን ተሰናብታለች፡፡ ‹‹አይዞሽ በርቺ፣ ልመጂ›› ያሏትን አመስግና ካገር ቀየው ርቃለች፡፡

ውዴና አማቷ አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡ እናት የልጃቸውን ሚስት ይዘው ቤታቸው ሊገቡ መንገድ ላይ ናቸው፡፡ እሷ የገጠር ልጅ ነች፡፡ ስለከተማ ሕይወትና ድምቀት አታውቅም፡፡ እግሯ ከመኪናው ወርዶ ሀገሩን ከማየቷ ተገርማለች፡፡ ግርግሩ ፣ የሰዉ ብዛት፣ የመኪናው ፍጥነት ∙ ∙ ∙ አስደንቋታል፡፡

ሁሉን አልፈው ከታሰበው ሰፈር ሲገቡ ወይዘሮዋ እግራቸው ወደ አንድ መንደር አቀና፡፡ ደማቅና ብዙ ነዋሪ ያለበት ነው፡፡ አላፊ አግዳሚው የሚተያይ አይመስልም። ሁሉም በራሱ ዓለም ከላይ እታች ይሮጣል፡፡ ውዴ ወይዘሮዋን እየተከተለች ነው፡፡

አማትና ምራት ጥቂት ተራምደው ከአንድ ግቢ ደረሱ። ውዴ ባልዋ ባገር እንደሌለ ብታውቅም እንደ ሙሽራ ‹‹ዕልል›› ቢባልላት ተመኘች፡፡ እንዳሰበችው አልሆነም። ሴትዬዋ መለስ ያለውን በር ገፋ አድርገው እግራቸውን አስቀደሙ፡፡ ግራ እንደገባት ተከተለቻቸው። ከጠባቧ ክፍል አንድ ባለ ሁለት ክራንቾች ጎልማሳ ተቀምጧል፡፡

ሰውዬውና አማቷ ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳሙ፡፡ ውዴ የያዘችውን ጓዝ አስቀምጣ ከአንድ ጥግ አረፍ አለች። ጥቂት ቆይቶ ሰውዬውና ውዴ ለትውውቅ እጃቸው ተጨባበጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ወይዘሮዋ አልዘገዩም፡፡ ለውዴ የወደፊት ባሏ፣ የትዳር አጋሯ ይህ ሰው መሆኑን እቅጩን ነገሯት፡፡

ሙሽሪት ልመጂ …

ውዴ በሰማችው እውነት ክው ብላ ደንግጣለች። ውጭ ሀገር ነው ተብላ በእምነት የተዳረችለት ባሏ ይህ ሰው መሆኑን ባወቀች ጊዜ አንገቷን ደፋች፡፡ አሁን ‹‹ከፋኝ፣ ተቀየምኩ›› የምትልበት ጊዜ አይደለም፡፡ አገር አታውቅም፣ ዘመድ ወዳጅ የላትም፡፡ ጨነቃት፣ ግራገባት፣ አሳልፈው በሰጧት ወላጆቿ ድርጊት ከልብ አዘነች። ዕድሏን አማረረች፡፡ ያለማቋረጥ ስታለቅስ ዕንባዋን ያበሰላት አልነበረም፡፡

እነሆ! ቀን አልፎ ቀን ተተካ፡፡ አሁን የትናንትናዋ ትንሽ ልጅ ‹‹ወይዘሮ›› መባል ይዛለች፡፡ ውዴ ከአባወራዋ ጋር ሕይወት ብትጀምርም ኑሮ አልተመቻትም፡፡ በየቀኑ የሆነባትን እያሰበች ትተክዛለች፡፡ የወላጆቿ ድርጊት ያናድዳታል፡፡ የእሷ አምኖ መቀበል ያበሽቃታል፡፡ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታዋን እያሰበች በሀሳብ ትነጉዳለች፡፡

አካል ጉዳተኛ ባሏ ልበ ክፉ አይደለም፡፡ የትዳር አጋር በማግኘቱ ከልቡ ተደስቷል፡፡ ባጋጠመው አደጋ በክራንች መጠቀም ከጀመረ ጥቂት ሰንብቷል። ጉዳተኛ በመሆኑ እንደ በፊቱ ሠርቶ አይገባም። ውዴ ይህን ሁሉ አምና ተቀብላለች፡፡ በአካል ጉዳቱ አልናቀችውም፡፡ የወላጆቿን ድርጊት ግን በዋዛ ይቅር ማለት አልተቻላትም፡፡ ዘመድና አገር አታውቅም፡፡ ልጅነቷን እየከፈለች ነው፡፡

ውዴ በማታውቀው ዕቅድ ብትጠለፍም ዝላ መውደቅን አልመረጠችም፡፡ ሁኔታዎች ቢያደክሟትም እየተንገዳገደች ቆማለች፡፡ አንዳንዴ ለውስጧ ‹‹ዕድሌ ነው›› ስትል ትነግረዋለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ራስዋን ከኑሮ አላምዳ፣ ሕይወትን መቀበል አላቃታትም፡፡

ቀናት እየገፉ፣ ወራት እየተተኩ ነው፡፡ የውዴን ልጅነት የሚያዩ ያዝኑላታል፡፡ ጥንካሬዋን ያስተዋሉ ያደንቋታል፡፡ ትንሽዋ ልጅ ሆዷ እየገፋ ሰውነቷ እየጨመረ ነው፡፡ ርጉዝ መሆኗን አውቃለች፡፡ ይህ እውነት የትም እንዳትሄድ አስሯታል፡፡

ባል አልባው መልስ…

ከቀናት በአንዱ ብቸና ካሉት የውዴ ቤተሰቦች ድንገቴ ጥሪ ደረሰ፡፡ አያቷ በትልቅ ድግስ የልጅ ልጃቸውን መልስ ሊጠሩ ተዘጋጅተዋል፡፡ ጥሪው የደረሳት ውዴ ጭንቅ ያዛት፡፡ ከዚህ ቀድሞ ባሏ ውጭ አገር መሆኑ ተሰምቷል፡፡ አሁን አብረው መኖራቸው በመታወቁ ለእሷ ክብር ሲባል ድግስ ተዘጋጅቷል፡፡

ውዴ የቤተሰቦቿን ሀሳብ አልገፋችም። አክብረው ስለጠሯት ደስ ብሏታል፡፡ ባሏን ይዛ ከጥሪው ለመገኘት ግን አቅም አጥታለች፡፡ ብዙ የተወራለት፣ ባሏን ‹‹ይህ ነው›› ብላ መውሰድ አልሆነላትም፡፡ ከጥሪው መቅረት አልቻለችም። ለእሷም፣ ለቤተሰቦቿም ስትል በደሏን ሁሉ ረሳች፡፡ ባሏን በቤቱ ትታ ከአማቷ ጋር በድግሱ ተገኘች፡፡

ስፍራው ሲደርሱ ትልቅ ዳስ ተጥሎ በርካታ ታዳሚ ተገኝቷል፡፡ ጭፈራው፣ ዕልልታው በበዛበት ድግስ አገሬው የውዴን ባል ለማየት ተሸቀዳደመ፡፡ ባልንጀሮቿ ብዙ የተባለለትን ሰው ለማወቅ አንጋጠጡ። እንደ ባል በውዴ ቀኝ የተቀመጠ የለም፡፡

ከሙሽሮቹ ቦታ ሙሽሪትን ብቻ ያዩ “ለምን?።፣ “እንዴት?፡፡ ሲሉ ጠየቁ፡፡ ውዴ ለመዋሸት አፏን ያዛት፡፡ አማትና ቤተሰቦቿ ግን ምላሽ አላጡም። ለጠየቃቸው ሁሉ ሙሽራው ባገር አለመኖሩን እያሳመኑ ተናገሩ፡፡

ስለ ልጃቸው ትዳር ጭምጭምታ የሰሙት አባት ተመልሳ እንዳትሄድ ሊያሳምኗት ሞከሩ፡፡ እሷ ኑሮ ብላ የገባችበትን ሕይወት ማፍረስ አልፈለገችም። “ትዳሬን አልፈታም፣ ባሌን አልተውም፡፡ ስትል ‹‹እምቢኝ›› አለች።

ውዴና አባቷ ሙግት ይዘዋል፡፡ እሷ በውሸት ታሪክ የልጅነት ዓለሟን፣ የጠዋት ዕድሏን፣ እንደሰበሩባት እየነገረቻቸው ነው፡፡ አሳልፈው ከሰጧት፣ ከባልንጀሮቿ በታች ካደረጓት በኋላ አሁን ‹‹ ተመለሺ፤ ትዳሩ ይቅርብሽ›› ማለታቸው አልተዋጠላትም፡፡

የአባትና ልጅ ስንብት ባለ መስማማት ተቋጨ። አባት ውዴን ከሸኙ በኋላ ያለ እሷ ፈቃድ ባደረሱባት በደል ፀፀት ገባቸው፡፡ ይህ ስሜት ውስጣቸው አልቀረም። ተታለልኩ፣ ተዋሸሁ ብለው ከሙሽራው ወገኖች ጠብ ገጠሙ፡፡

ውዴና አማቷ ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡ ሕይወት በአዲስ አበባ ከባድ ነው፡፡ የአንድ እጅ ገቢ ባለበት ጎጆ የዕለት አስቤዛው ይቸግራል፡፡ አካባቢውን የነዋሪው ሕይወት ያመሳስለዋል፡፡ የአብዛኞች ገቢ ቤትን ለሴተኛ አዳሪዎች በማከራየት ላይ ተመሥርቷል። ውዴ ትዳር ከያዘች ጀምሮ ቤቷን የምትመራው በየቀኑ የጓዳ አልጋዋን እያከራየች ነው፡፡

የመጀመሪያ ልጅዋ ከተወለደች በኋላ ሕይወት መክበድ ያዘ፡፡ አካልጉዳተኛ አባወራ፣ ጨቅላ ሕፃንና አሮጊት እናት ባሉበት ቤት ጫናው በውዴ ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡ ቤተሰቡን ለማኖር የልጅነት ጉልበቷን ገበረች። በየቤቱ ልብስ ማጠብ፣ ያገኘችውን መሥራት ግዴታዋ ሆነ፡፡ እንዲያም ሆኖ ጠግቦ ማደር አልሆነም፡፡ አንዱ ሲሞላ ሌላው እየጎደለ ቤቱ በችግር ተፈተነ፡፡

የነበረው እንደነበረ…

ጊዚያት ነጎዱ፡፡ ሕይወት አልተለወጠም፡፡ ውዴ ተጨማሪ ሦስት ልጆች አከታትላ ወለደች፡፡ በቤቱ ድህነትና ችግር ተንሰራፋ፡፡ አባወራዋ ሕመሙ ባሰ። እግሮቹ መላወስ አቃታቸው፣ ከዊልቸርም ዋለ። ይህ አጋጣሚ እጆቹን ለልመና አዘርግቶ ምጽዋት አስጠየቀው፡፡

ውሎ አድሮ በሰፈሩ ቤትን ለሴተኛ አዳሪዎች ማከራየቱ ቀረ፡፡ ውዴ እጇ ነጠፈ፡፡ ልጆቿ ተራቡ። ይሄኔ ለሊት፣ ዘጠኝ ሰአት እየወጣች ለንግድ ቤቶች ቡና መቁላት ጀመረች፡፡ መንገዱ ለሌባ ያሰጋል፡፡ የምታገኘው ገንዘብ ቀዳዳ አይደፍንም፡፡ እሱን ይዛ ለቤተሰቡ ዳቦ ታቃምሳለች፡፡

ዓውደ ዓመት በደረሰ ግዜ ውዴ ጭንቀቷ ያይላል። ልጆቿ የሰው ቤት እንዳያዩባት አትሆነው የለም፡፡ አንዳንድ ልበ መልካሞች ዝም አይሏትም፡፡ እንደወጉ የአቅሟን ሞልታ ቀኑን ታሳልፋለች፡፡

ያልጎበጠ ትከሻ

ውዴ አምስተኛውን ልጅ አርግዛለች፡፡ ይህ እርግዝናዋ ጤና አልሰጣትም፡፡ በሄደችበት ሆስፒታል ሁሉ ልጁ በተለመደው አቀማመጥ ላይ እንዳልሆነ ተነግሯታል። አንድ ቀን በድንገት ምጥ ተያዘች፡፡ ሆስፒታል መድረስ አልቻለችም፡፡ ቤት ውስጥ ወንድ ልጅ በሰላም ወለደች። አራት ሴቶች ስላሏት ልጆቿ ወንድም ስላገኙ ተደሰተች። በሆስፒታል አብሯት የዋለው ሕጻን ብዙ አልቆየም፡፡ መሞቱ ተነገራት፡፡

ከዓመት በኋላ ውዴ በድጋሚ ነፍሰጡር ሆነች፡፡ ውሎዋ ይፈትናል፡፡ ሥራዋ ፀሐይ፣ ዝናብ፣ እሳት፣ ውሀ አይልም፡፡ የአሁኑ እርግዝና በጣም እያስጨነቃት ነው፤ ዕንቁጣጣሽ ደርሷል፡፡ ዕለቱን ቡና ስትቆላ ውላለች። ድንገት ሕመም ተሰማት፡፡ ሰባት ወሯ ቢሆንም ስሜቱ ምጥ ነበር ፡፡

ሐኪም ቤት ስትደርስ ባሰባት፡፡ ማማጥ ጀመረች። ሥራ የጎዳው አካሏ አላገዛትም፡፡ በድካም ዛለች፡፡ ጊዜው ደርሶ በጭንቅ ስቃይ ተገላገለች፡፡ ጥቂት ቆይቶ ሐኪሞቹ ሁለት ልጆች ስለመውለዷ ነገሯት፡፡ ለጊዜው ከሕመሟ እፎይ አለች፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን ሕመሙ ቀጠለ፡፡ ሦስተኛው ልጅ እየመጣ ነበር፡፡

ሦስት መንታ ልጆችን የወለደችው ውዴ ለተሻለ ሕክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል ተላከች፡፡ እስካሁን ልጆችዋን ያሳያት የለም፡፡ ለቀናት ሆስፒታል ስትተኛ ሙቀት ክፍል መሆናቸው ተነግሯታል፡፡ ከድካሟ ስትነቃ ‹‹ልጆቼን›› አለች ሁሉም ዝም አላት፡፡ ደግማ ጠየቀች፡፡ የሰማችው ክፉ ዜና ውስጧን ሰበረው፡፡ የሶስቱም መንታ ልጆቿ ሕይወት አልቀጠለም፡፡

ውዴ – የታዛው ስር ዋርካ

ውዴ በቤቷ ታዛ ስር ላሉ ነፍሶች ሁሉ ታላቅ ዋርካ ነች፡፡ ሁሉንም በጉልበቷ፣ በላቧ ወዝ ታሳድራለች። አካል ጉዳተኛ ባለቤቷን አክባሪ፣ ትዳሯን ወዳድ ወይዘሮ ናት፡፡ ዛሬ ዕድሜ የተጫናቸውን አማቷን ጨምሮ ለሥራ ያልደረሱ ልጆቿ ተስፋ የእሷ ትከሻ ነው፡፡ ውዴ ለባለቤቷ ሚስት ብቻ አይደለችም፡፡ እጅና እግሩም ነች። እንደ እናት፣ ታስብለታለች፣ እንደ ሚስት አጋሩ ነች፡፡

በእነ ውዴ ቤት እንደሌሎች ጤፍ መግዛት ይከብዳል። ከዕለት የማይዘለው ገቢ ከግዢ እንጀራ አያልፍም፡፡ በተገኘ ጊዜ ሁሉም እሱን ተቃምሶ ያድራል። በሌለ ቀን ጥሬ ቆርጥሞ ውሀ ጠጥቶ ማደር ብርቅ አይደለም፡፡ እንዲህ ሲሆን እናት ስለራሷ ግድ አይላትም። ቅድሚያውን ለልጆቿ ትሰጣለች፡፡

አንዳንዶች የአካሏን መወፈር ሲያዩ ጠግባ አዳሪ ትመስላቸዋለች፡፡ እሷ ግን በልተው ከተረፋቸው ፍርፋሪ ለልጆቿ ቢሰጧት ለመቀበል አታፍርም፡፡ ጠንካራዋ፣ ብርቱዋ ሴት ዛሬ ከአስራ ስምንት ዓመታት በላይ ትዳሯን መርታለች፡፡

እነዚህ ዓመታት በዥንጉርጉርና ሻካራማ የሕይወት መንገድ አራምደዋታል፡፡ ትናንትን በችግር አልፋለች፡፡ ዛሬ ላይ ስትቆም ስለነገ ተስፋ አትቆርጥም፡፡ የቤቱ ታዛ የቤተሰቧ ዋርካ ነች፡፡ ውዴ አለ ተስፋው፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You