ውጤታማ ተቋራጮችና አማካሪዎች በውጭ ገበያ እንዲሳተፉ ድጋፍ ይደረጋል

አዲስ አበባ፡– በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ተቋራጮችና አማካሪዎች በውጭ ገበያ እንዲሳተፉና ሀገርን በበጎ እንዲያስጠሩ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ።

ከ20 በላይ ሀገራት ምርቶቻቸውን የሚያሳዩበት የኮንስትራክሽን ንግድ ትርዒት በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ተከፍቷል።

ወይዘሮ ጫልቱ በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር፤ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ውጤታማ ተዋናዮች እውቅና የሚያገኙበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ ነው።የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋናዮች የሚመዘኑበት፣ ውጤታማ የሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች እውቅና የሚያገኙበት እና በጨረታ ወቅት የተለየ ዕድል የሚያገኙበት አሠራር ይዘረጋል ብለዋል።ይህም ብቁ የሆኑ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋናዮችን በማውጣት በውጭ ገበያ እንዲሳተፉና ሀገርን በበጎ እንዲያስጠሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።ለእዚህም ተቋራጮችና አማካሪዎች እንዲሁም የመንግሥት ፕሮጀክት ባለቤቶች ተመዝነው ውጤታማ የሆኑት የሚለዩበትና ደረጃ የሚወጣበት አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በሂደቱ ውጤታማ ተዋናዮች ከዕውቅና በተጨማሪ በጨረታ ወቅት የተለየ ዕድል የሚያገኙበት አሠራር እንደሚዘረጋም ገልጸዋል።

በየዓመቱ በሚደረገው ግምገማና የደረጃ ልየታ  በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ቢያንስ 20 የሚጠጉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢንሼቲ ቮችን በመቅረጽ ወደ ትግበራ እየተሸጋገርን እንገኛለን ብለዋል።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግዙፍ ካፒታል የሚያንቀሳቅስ፣ በሀገርም ሆነ በውጭ የሚመረቱ ግብዓቶችን የሚጠቀም፣ ከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የሚያስፈልገው፣ በርካታ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ እና ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም መሆኑንም ጠቅሰዋል። በሁሉም ጉዳዮች ከዘርፉ ተዋናዮች እና የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን ተከታታይ ሥራዎች እንደሚሠሩ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢንዱስትሪው አካሄድ አሳሳቢ ነው ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ፤ የሚደረጉ ጥረቶችም በተበታተነ መልኩ የሚከወኑ በመሆናቸው የኢንዱስትሪው ተዋናዮች የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት የሚያስችል ወጥ አሠራር አልተከተሉም ብለዋል።

በዘርፉ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ውጤታማ ካልሆነው  ተዋናይ ሳይለይ በጥቅሉ የሚወገዝ አካሄድ አለመሆኑን አንስተው፤ በኢንሺቲቩ የተያዙ ዝርዝር ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ተግባራዊ የሚደረጉ ስለመሆናቸውም አመልክተዋል።

እነዚህ ሥራዎች በፖሊሲ እንዲደገፉና ሕጋዊ ማሕቀፍ ኖሯቸው አፈጻጸማቸው ወጥ በሆነ መልኩ እንዲተገበር፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲው አዳዲስ ሃሳቦችን በማካተት መከለሱን ተናግረዋል።የተከለሰው ፖሊሲም በአጭር ጊዜ በመንግሥት ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም በሀገራችን ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ውጤታማነት በሚያገለግሉ ግብዓቶች ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በመለየት የመፍትሔ ሃሳብ ለማቅረብናበመስኩ ያለውን ችግር ለመፍታት ያግዛል።በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተሞክሮና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመለዋወጥ ያስችላል።

በሚሊኒያም አዳራሽ ከትናንት አንስቶ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ስትራቴጂክ አጋር የሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው፤ ኤክስፖው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና ትብብሮችን በማጠናከር በኢትዮጵያ የትራንስፎርሜሽን ውጥን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

መድረኩ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያሉ አዲስ ፈጠራዎች፣ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች፣ ግብአቶች፣ ቴክኖሎጂዎች የቀረቡበት መሆኑን ገልጸዋል። ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ160 በላይ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

አውደ ርዕዩና ሲምፖዚየሙ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ በሚገኙ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት መካከል ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰዋል።

ትናንት የተጀመረው ኤግዚቢሽን ዛሬና ነገም ለታዳሚዎች ክፍት ሆኖ የሚቆይ መሆኑን ኢንጂነር ዮሐንስ አመልክተዋል፡፡

በቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You