ዛሬ በሚካሄደው ሀገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል

የፈረንጆቹ የክረምት ወራት የሀገር አቋራጭ ውድድሮችን ለማካሄድ ምቹ እና ተመራጭ ወቅት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ተፈጥሯዊ መሰናክሎችን፣ ውሃማ እና አስቸጋሪ ጭቃማ ስፍራዎችን ለሚፈልገው ሀገር አቋራጭ ዝናባማው ወቅት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም በርካታ የአውሮፓ፣ እንዲሁም ጥቂት የአሜሪካ እና የአፍሪካ ከተሞች ይህንን ውድድር ያስተናግዳሉ፡፡ እነዚህ የዙር ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ያላቸው ሲሆኑ ከወርቅ እስከ ነሐስ ያሉ ደረጃዎች አሏቸው፡፡ ከሳምንታት በፊት በስፔን ሁለት ከተሞች የተጀመረው የዘንድሮው የዓለም ሀገር አቋራጭ የዙር ውድድርም ዛሬ ሦስተኛውን ፉክክር በካርዲፍ (በእንግሊዟ ዌልስ) የሚያከናውን ይሆናል፡፡

ካለፈው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ አንስቶ እስከ አዲሱ ዓመት ሁለተኛው ወር አጋማሽ ድረስ 15 ውድድሮች የሚደረጉ ሲሆን፤ ማጠቃለያውም የዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ይሆናል፡፡ ይህንን ተከትሎ እንዲሁም የጎዳና ላይ ውድድሮች ወቅት እስኪመጣ ድረስም ከመላው ዓለም በርካታ አትሌቶች በሀገር አቋራጭ የዙር ውድድሮች ላይ ይካፈላሉ፡፡ ዛሬ በካርዲፍ በሚከናወነውና በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው ውድድር ላይም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንዲሁም ተቀናቃኞቻቸው ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ በሀገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የተሻለ የውጤታማነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይም አትሌቶቿ እንደተለመደው ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ይጠበቃል፡፡

ውድድሩ በወንዶች 9ነጥብ6 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች ደግሞ 6ነጥብ4 ኪሎ ሜትር በመሸፈን ንፋሳማ በሆነ ስፍራ ይካሄዳል፡፡ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድም በተለይ በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ይሆናሉ የሚለው ግምት አይሏል፡፡ ግምቱን በቀዳሚነት ካገኙ አትሌቶች መካከልም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የውድድር ዓመት በተለያዩ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበረችው አትሌት ልቅና አምባው አንዷ ናት፡፡

አትሌቷ በአንድ የመም፤ እንዲሁም፣ በሦስት የ10 እና 15 ኪሎ ሜትር ሩጫዎች ላይ ተሳትፋ መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች፡፡ ከሳምንታት በፊት በስፔን በተደረገው ሀገር አቋራጭ ቱር በመካፈል 29:36 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ነበረች፡፡ ጠንካራዋ አትሌት ልቅና በሌላ ውድድር ወቅት የሆድ ሕመም ቢገጥማትም በቀላሉ እጅ ሳትሰጥ ከሕመሟ ጋር እየታገለች አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋም አስደናቂ ብቃቷን ያስመሰከረ ሆኗል፡፡ ይህ የሁለተኛ ጊዜ የመድረኩ ተሳትፎዋ በመሆኑም ለጠንካራ ተፎካካሪነት እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡

ሌላዋ ወጣት አትሌት አስማረች አንለይም በዚህ ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች አንዷ መሆኗ ታውቋል። በዚህ ዓመት የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በ3ሺ ሜትር የወርቅ፤ እንዲሁም፣ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለችው አትሌቷ ተስፋ ከተጣለባቸው ተተኪ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። አትሌቷ ካለችበት ወቅታዊ አቋም አንጻርም በካርዲፍ ከፍተኛ የአሸናፊነት ፉክክር ያደርጋሉ በሚል ከተገመቱት መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መሠረት የሻነህም ተመሳሳይ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካል ትገኛለች፡፡ የ18 ዓመቷ አትሌት ባለፈው ዓመት በካሊ በተደረገው የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለሀገሯ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው፡፡

በወንዶች በኩልም ሌላኛው የ17 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሐንስ አስማረ በዚህ ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆን አትሌቲክስ ዊክሊ በዘገባው ጠቁሟል፡፡ ባለፈው ዓመት አሰላ ላይ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1ሺህ 500 ሜትር አሸናፊ የነበረው አትሌቱ፤ በዚህ ዓመት ደግሞ ናይሮቢ ላይ በተደረገ ውድድር ተሳትፎ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ከሳምንታት በፊት በሰሜን አየርላንድ በተካሄደው የሃገር አቋራጭ ቱር ውድድር ላይም አሸናፊ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ወጣቱ አትሌት በውድድሩ አሸናፊ ከመሆን በዘለለ ልምድ ያገኘበት መድረክ እንደመሆኑ በዛሬው ውድድር ላይ ተፎካካሪዎቹን በመርታት አሸናፊ ለመሆን እንደሚችል ተጠብቋል። ነገር ግን፣ በሁለቱም ጾታዎች የኬንያ፣ ብሩንዲ እና እንግሊዝ አትሌቶች ለኢትዮጵያውያኑ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You