በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት የኅብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለዋጋ ንረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ቆይተዋል፡፡ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ኃብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣ የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ፣ የምርት አቅርቦት መቀነስ፣ የምርት ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የብር የመግዛት አቅም መዳከም ተደጋግመው ሲነገሩ የኖሩ የዋጋ ንረቱ ምክንያቶች ናቸው፡፡
እነዚህ ምክንያቶች ተደጋግመው ይገለፁ እንጂ ኑሮ ናላውን ላዞረው ኅብረተሰብ በሚፈለገው ደረጃ መፍትሄ አላስገኙም፡፡ ‹‹ኑሮውን አልቻልነውም … የዋጋ ንረቱ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል …›› የሚሉና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደመጡ የቆዩ የኅብረተሰብ ድምፆች ዛሬም እየተስተጋቡ ነው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች የዘንድሮው የዋጋ ንረት ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁሉ የተለየ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በአንዳንዶቹ ምርቶች ላይ ደግሞ በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት ጠዋትና እና ከሰዓት በኋላ የዋጋ ልዩነት እስከማሳየት የደረሰ ነው ይላሉ፡፡
እጅግ የሚያስገርመው ነገር አገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ሰማይ መድረሱ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ይናራሉ፡፡ በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው፡፡
‹‹…አንዳንድ ጊዜ የአትክልትና ፍራፍሬ ገዢ ስለማይኖር ማሳ ላይ ይቀርና ከብት ይበላዋል …›› ይህ ከአንድ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች አርሶ አደር የተነገረ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ሽንኩርትና ቲማቲም ከማሳቸው ላይ የሚሸጡት በዝቅተኛ ዋጋ ቢሆንም ምርቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች ከገባ በኋላ ግን ገበሬው ከሸጠበት ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ ይሸጣል። የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ለማሳያነት ያህል ተጠቀሰ እንጂ በሌሎቹም ምርቶች ላይ ያለው የዋጋ ንረት የሚቀመስ አይደለም፡፡
ታዲያ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መሀል ደግሞ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ የሚፈጠርና በኅብረተሰቡ በተለይም ደግሞ በሸማቹ ላይ የተጋረጠ እጅግ አደገኛ ነቀርሳ አለ፡፡ ይህ ነቀርሳ ውስብስቡ የደላሎች ሰንሰለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በደላሎች ተፅዕኖ ስር ያልወደቀ የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም፡፡
‹‹ደላላ በመሀል ሲገባ ገበሬ እና ነጋዴ አይገናኙም። ደላላና ነጋዴ ይነጋገራሉ፤ ደላሎች ከገበሬው እንደፈለጉ ገዝተው ነው ለነጋዴው የሚሸጡት …›› ይላሉ አርሶ አደሮቹ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ገበሬውንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባሻገር የኅብረት ስራ ዩኒየኖች ምርቶችን በሙሉ አቅማቸው ተረክበው ለተጠቃሚው ማድረስ እንዳይችሉ እስከማድረግም እየደረሰ መሆኑ ይጠቆማል፡፡ ይህ ቅጥ ያጣው የደላሎች ተግባር ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብትም ትልቅ መሰናክል ሆኗል፡፡
በንግዱ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉት እነዚህ ችግሮች መንግሥት አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት ሸማቹ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ፣ አምራቹም ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ለሚያስችሉ አሰራሮች ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና አምራችን ከሸማች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እየሰራ ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች አካባቢ የሚስገነባቸው የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ከእነዚህ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ማዕከላት ከአምራች አርሶ አደሩ እስከ ሸማቹ ድረስ ያለውን እጅግ የተንዛዛውንና የተበላሸውን የግብይት ሰንሰለት ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ ሸማቹ ጥራት ያለው ምርት ፍትሀዊ በሆነ ዋጋ እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል፡፡ የገበያ ማዕከላቱ የግብርና ውጤቶችን በወቅቱ በማቅረብ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ የከተማውን ነዋሪ ከኑሮ ውድነት ጫና ለመታደግ የሚያስችሉ ከመሆናቸው ባሻገር አምራቾችም ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማዕከላቱ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ይህ አሰራርም ፍትሐዊ ግብይትን በመፍጠር ማኅበራዊ መረጋጋት እና ጤናማ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዲኖርና በጎ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዋጋ ንረት በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ የፈጠረው ጫና ከባድና አሳሳቢ በመሆኑ በከተማዋ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት ግንባታዎችን በቀን ለ16 ሰዓታት ያህል በትጋት በመሥራት በፍጥነት ለማጠናቀቅ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላቱ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ማሟላት ያሉባቸውን ቴክኖሎጂዎች ሁሉ ያሟሉ ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ በሙቀት የሚበላሹ ምርቶችን ለማቆየት እንዲሁም በቅዝቃዜ ውስጥ መቆየት የማይችሉትን ምርቶችን ደግሞ ለማሞቅ የሚያስችሉ ናቸው። የደህንነት ካሜራዎች፣ የቆሻሻ ማስወገጃና የመኪና ማቆሚያም የማዕከላቱን አገልግሎት የተሟላ የሚያደርጉ ግብዓቶች ናቸው፡፡
የማዕከላቱን ግንባታ የሚያከናውነው የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት የፕሮጀክቶቹን የዲዛይን ስራዎችንም እንዲሰራ መደረጉ የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ጥራት ለመቆጣጠርና ፕሮጀክቶቹ ተጨማሪ ዋጋ እንዳይጠይቁ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም የማዕከላቱ ግንባታ ለበርካታ ዜጎች ስራ እድሎችን ፈጥሯል። የማዕከላቱ ግንባታ በአገር በቀል የስራ ተቋራጭ ድርጅት እንዲከናወን መደረጉም ለአቅም ግንባታና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡
ከእነዚህ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት የመጀመሪያ የሆነውና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል ጳጉሜ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት እንደበቃ ይታወሳል፡፡ ይህ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት ግንባታ ተግባር ቀጥሎ፣ የትልልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚያስገነባቸው የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል አንዱ የሆነውና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ (ቤተል ሳይት) የሚገኘው የኮልፌ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ይህ ማዕከል በሁለት ነጥብ ሦስት ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ለግንባታውም ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል፡፡
በ‹‹ኦቪድ ኮንስትራክሽን ግሩፕ›› (OVID Construction) በአስር ወራት ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የግብይት ማዕከሉ፤ በውስጡ አራት ትልልቅ ህንፃዎች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ዘመናዊ የምርት ማቀዝቀዣና ማሞቂያ፣ ለምርት ማጠቢያ፣ ለባንኮች እና ለቢሮ ግልጋሎት የሚውሉ ክፍሎች፣ የምርት ማከማቻዎች፣ የጅምላና የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች እንዲሁም በአንድ ጊዜ ከ200 በላይ ተሽከርካሪዎችን መያዝ የሚችል የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ያካተተ ነው።
የግብይት ማዕከሉ የአስተዳደር ሕንፃ በውስጡ ለባንክ፣ ለካፌ እና ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ ክፍሎችንም ይዟል፡፡ የችርቻሮ መሸጫ ሱቁ ደግሞ ከ80 በላይ የችርቻሮ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬት፣ ሚኒ ሱፐር ማርኬት፣ የምርት ማቀዝቀዣና ማሞቂያ ክፍሎች አሉት፡፡ ከ12 በላይ ሱቆችን አካትቶ የያዘው የጅምላ መሸጫ ሱቅም የማዕከሉ አካል ነው፡፡
ከ90 በላይ የምርት ማስቀመጫና ማከማቻ፣ ከዘጠኝ በላይ የምርት ማሞቂያ እንዲሁም ለሽያጭ የሚቀርቡ ግብዓቶች የሚታጠቡባቸው ከ10 በላይ የማጠቢያ ክፍሎች የሚገኙት ደግሞ በማዕከሉ የማከማቻ ሕንፃ ውስጥ ነው። ማዕከሉ በዋናነት ከምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የግብርና ምርቶች ለሸማቹ በቀጥታ የሚቀርቡበት የግብይት ስፍራ ነው፡፡
ማዕከሉን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች የሚያስገነባቸው የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት፣ አምራቹ ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኝና ዋጋ እንዲረጋጋ ለማድረግ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባው የኮልፌ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል ወደ ስራ መግባት ሸማችን ከአምራች ጋር በቀጥታ በማገናኘት በከተማዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት በዘላቂነት በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል፡፡
‹‹ይህ ፕሮጀክት በአምስቱም የአዲስ አበባ በሮች ትልልቅ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላትን በመገንባት የሕዝባችንን የኑሮ ጫና እናቃልላለን፣ አምራቹንና ሸማቹን እናገናኛለን ብለን ቃል ከገባንባቸው እና ቃላችንን ጠብቀን ከገነባናቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡›› ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የማዕከላቱ ግንባታ አምራችንና ሸማችን በቀጥታ ያገናኛል፡፡ አምራችና ሸማቹን ማገናኘት በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዋጋን ያረጋጋል፣ ሸማቹ ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ በግብይት ሰንሰለት ላይ ያሉ ችግሮችን በማቃለል ግብይቱን የተረጋጋ ያደርገዋል፡፡››ሲሉም ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ትልቅ ጫና የሚያቃልል ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የከተማ አስተዳደሩ በግብርና ምርቶች ዋጋ መናር ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ በሁሉም የከተማዋ መግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላትን እየገነባ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሰል ፕሮጀክቶች በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
‹‹ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በየደረጃው ተግባራዊ እያደረግን ነው›› ያሉት ከንቲባዋ፣ ‹‹አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስና ውብ እናደርጋለን ስንል የሕዝቡንም ኑሮ በማሻሻል፣ የሰውም ሕይወት አብሮ እንዲያብብ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ለሕዝብ የገባነውን ቃል ወደተግባር እየመነዘርን ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ መገንባታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን›› በማለት አስታውቀዋል፡፡
የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት ግንባታ ኃላፊ ኢንጂነር ብስራት አባተ፤ የኮልፌ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከል ተገቢውን የጥራት ደረጃ አሟልቶ የተገነባ ማዕከል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ማዕከሉ ለ24 ሰዓታት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡ ለዚህም የራሱ የሆነ የትራንስፎርመር ሰብስቴሽን አለው፡፡ መብራት በአጋጣሚ ቢቋረጥ ወዲያውኑ አገልግሎቱን ማስቀጠል የሚችሉ ጀነሬተሮችም ተገጥመውለታል›› በማለት የማዕከሉን ዘመናዊነት ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለትና የግብርና ምርቶችን ለማገበያየት የሚስፈልጉ መሰረተ ልማቶች የተዘረጉለት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ በርካታ የጅምላ እና የችርቻሮ ማከማቻና መሸጫ ሱቆች፣ የምርት ማሞቂያና ማቀዝቀዣ ክፍሎች፣ ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ እና ሌሎች ዘመናዊ ግብዓቶች እንዳሉትም ኢንጂነር ደቦ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ማዕከሉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር፤ አምራቾችን ከሸማቾች በቀጥታ የሚያገናኝ ግዙፍ የልማት ትሩፋት ነው›› ብለዋል፡፡
ማዕከላቱ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ከማሳ ወደ መጋዘን ይዘው እንዲገቡ በማድረግ በምርት ጥራትና በአቅርቦት አስተማማኝነት እንዲሁም በዋጋ ተመጣጣኝነት አምራቹንና ሸማቹን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረዋል። ከሁለት ወራት በፊት አገልግሎት መስጠት በጀመረው የለሚ ኩራም ሆነ ሰሞኑን በተመረቀው የኮልፌ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት ምርቶቻቸውን ያቀረቡ አምራቾች የማዕከላቱ መገንባት ምርቶቻቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለሸማቹ እንዲያቀርቡ እንዳስቻላቸው መግለጻቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም በዋጋው ላይም ተጨባጭ ለውጥ እንዲኖረው ማድረጉን መናገራቸው ተመልክቷል፡፡
በማዕከላቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሸማቾች በበኩላቸው፣ በማዕከላቱ የሚቀርቡ ምርቶች በሌሎች የግብይት ስፍራዎች ከሚቀርቡ ምርቶች የተሻለ ጥራትና ዋጋ እንዳላቸው መገለጻቸው ተጠቁሟል፡፡ በመደበኛ የግብይት ቦታዎች ላይ ጥራቱን የጠበቀና ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት እኩል ሲሸጥ መመልከታቸውን የገለጹት ሸማቾች፣ በግብይት ማዕከላቱ የቀረቡ ምርቶች ግን ከፍተኛ ጥራት እንዲሁም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ስለመሆናቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016