የምናባዊ ዕይታ ኃይል

የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከመጣ ወዲህ እያንዳንዱን ነገር መተግበር የሚጀምረው ከሃሳብ ነው፡፡ ሀሳብ ዘር ነው፡፡ የተዘራ ዘር ደግሞ ይበቅላል፡፡የዘራነው ዘር የስንዴ ከሆነ ስንዴ ይበቅላል፡፡ የዘራነው ዘር ማሽላ ከሆነ ማሽላ ይበቅላል ∙ ∙ ∙ ወዘተ፡፡ መቼም ስንዴ ዘርተን ማሽላ ልንጠብቅ አንችልም፡፡ የሰው ልጅ ሀሳብም እንደዛ ነው፡፡ለምሳሌ የአንድ ገበሬ ማሳ በሚገባ ታርሶ ከተዘጋጀ በኋላ ጤፍ ቢዘራበት ጥሩ የጤፍ ምርት ይሰጣል፡፡ ማሽላም ከተዘራበት ጥሩ የማሽላ ምርት ይሰጣል፡፡ ይህ ምሳሌ ታዲያ እንዴት ከእኛ ሕይወት ጋር ሊያያዝ ይችላል?

ማሳው ወይም የእርሻው ቦታ የኛ አእምሮ እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ይቻላል፡፡በማሳው ላይ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ሌሎችንም ዘሮችን እንደምንዘራ ሁሉ በአእምሯችን ላይ የምንዘራው ሀሳብ ነው፡፡ በአእምሯችን የምንዘራው ሀሳብ ታዲያ በጎም መጥፎም ሊሆን ይችላል፡፡በአእምሯችን ላይ በጎ ነገሮችን እስከዘራን ድረስ የምናጭደው በጎ በጎውን ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በአእምሯችን ላይ የምንዘራው መጥፎ ነገር እስከሆነ ድረስ የምናበቅለው ጥሩ ያልሆነውን ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ መልካም ማንነት ሊመጣ የሚችለው በአእምሯችን ላይ በጎ ነገሮችን በዘራን ቁጥር ነው፡፡ መልካም ነገሮችን በአእምሯችን ውስጥ ባስገባን ቁጥር ውጤቱ መልካም ይሆናል፡፡

አንድ ዘር ተዘርቶ አንድ ዘር አይሰጥም፡፡በእጥፍ ተራብቶ ነው ዘር የሚሰጠው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዘር እንክርዳድ በማሳ ውስጥ ቢዘራ ሙሉ ማሳውን በእጥፍ ያዳርሳል፡፡ በተመሳሳይ መጥፎ ነገርም በአእምሮ ውስጥ እስከተዘራ ድረስ መጥፎ ነገሮች ተመልሰው በአእምሮ ውስጥ በእጥፍ ይራባሉ፡፡በተቃራኒው ደግሞ መልካም ነገር በአእምሮ ውስጥ ሲዘራ በእጥፍ መልካም ነገሮችን ያባዛል፡፡

ይህም አንድ ሰው አላስፈላጊና መጥፎ ሀሳቦችን ወደ አእምሮው ማስገባት የለበትም ማለት ነው፡፡ ስለውድቀቱ፣ ስለ ድክመቱ፣ ከሰዎች ጋር መግባባትና አብሮም መስራት ስላለመቻሉና ሌሎች አሉታዊ ሃሳቦችን፤ ወይም፣ የሰውን አእምሮ የሚገሉ ሃሳቦችን ወደ አእምሮው ማስገባት የለበትም፡፡እነዚህ የማይጠቅሙ ሀሳቦች በአእምሮ ላይ እስከተዘሩ ድረስ መብቀላቸው አይቀርም፡፡ያን ግዜ በዛ አሉታዊ ሃሳብ ውስጥ ሆነን እንገኛለን፡፡

በልጅነት፣ በወጣትነት ወይም ደግሞ አሁን ባለንበት የእድሜ ዘመን በሕይወታችን እየገጠመን ያለው ነገር በርግጥ የምንፈልገውን አይነት ሕይወት ነው እየኖርን ያለነው? ‹‹እኔ እንዲህ አይነት ሕይወት መኖር እፈልጋለሁ›› ብለን ያሰብነውን ሕይወት ነው እየኖርን ያለነው? ወይስ ከዚህ ወጣ ያለና ያልሆነ ሕይወት ውስጥ ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ገንዘብ ፈልገን የገንዘብ እጦት ይገጥመናል፡፡ ለምን? አእምሯችን የሚያስበው ስለገንዘብ ማጣት እንጂ ስለማግኘት ባለመሆኑ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይህች ዓለም በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት የተትረፈረፈች ናት፡፡ በሀብት ውስንነት የተገደበች አይደለችም፡፡ ፈጣሪም ቢሆን ይህችን ዓለም ውስን አድርጎ አይደለም የፈጠራት። ሁሉንም ነገር አትረፍርፎ ነው በዚህች ምድር የፈጠረው፡፡ “መትረፍረፍ፡፡ ማለት ደግሞ አንድ ፍሬ የስንዴ ዘር ዘርቶ በእጥፍ አራብቶ እንደመሰብሰብ ነው፡፡ነገር ግን ውስን እንድንሆን የሚያደርገንና ለራሳችን ገደብ የምናበጀው እኛው ራሳችን ነን። እንዲህ እንድንሆን ሊያደርገን የሚችለው የተማርነው መደበኛና የሕይወት ልምድ ትምህርት፣ አብረን የምንውላችው ሰዎች ወይም ጓደኞቻችን፣ ቤተሰቦቻንና ዘመዶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እነዚህ የእኛን አእምሮ የማሰብ ፍላጎት ይገድቡታል፡፡ ስለሆነም በምንፈልገው ነገር ላይ ማተኮር አለብን፡፡ሁሉም ድርጊትና መሻት የሚመነጨው ከሃሳብ ነው፡፡ሀሳብ ወደ ቃል ይቀየራል፡፡ቃልም ድርጊት ወይም ተግባር ይሆናል።ለምሳሌ አንድ በጣም የምትወዱትና የምታከብሩት ሰው ቢሰድባችሁና ቢያመነጫችቃችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ በትዕግስት ታልፉታላችሁ፡፡ በሌላ ግዜም ያ የምትወዱትና የምታከብሩት ሰው በቀልድ ወይም በሌላ መንገድ ለሁለተኛ ጊዜ ቢያመናጭቃችሁ፤ አልያም ቢሰድባችሁ ዝምታችሁ ወደ ቃል ያድጋል፡፡ትእግስታችሁ ወደ ማጥቃት ይሸጋገራል፡፡

በመጀመሪያ ያ የምንወደው ሰው እንዲያ ሲሰድበንና ሲያመናጭቀን ‹‹ምን አስቦ ነው እንዲህ የሚሰድበኝ፤ የሚያመናጭቀኝ?›› ብለን እራሳችንን እንጠይቃለን። ከራሳችን ጋር እናወራለን፡፡ይህን ስናብሰለስለው የቆየነውን ሃሳብ ድጋሚ ሲሰድበንና ሲያመናጭቀን ወደ ቃል ለውጠነው አንድ ነገር እንለዋልን፡፡ ማለትም ሃሳባችን ወደ ቃል፤ ወይም ወደ ማውራት ይቀየራል ማለት ነው፡፡መልስ ወደ መስጠት እንሸጋገራለን፡፡መልሳችን ‹‹አንተ ስርዓት ይኑርህ፣ ምን ሆነህ ነው የምትሳደበው፣ እገልሃለሁ ….››ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ጋር ሰዎች እንዲህ ሲባሉ ከሃሳባቸው በኋላ የሚወስዱት እርምጃ ቃል አውጥቶ ለዚያ ስድብና ማመናጨቅ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ምላሹ ግን እንደየሰው ባህሪና የማስተዋል ደረጃ ይወሰናል። ዞሮ ዞሮ ግን ሰዎች እንዲህ ሲባሉ በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ የቃላት ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ይህ የቃላት ምላሽ ካደገና ከዛኛው ሰው በኩል ከተደጋገመ ወደ ድርጊት ተሸጋግሮ ወደ ፀብ ሊያመራ ይችላል፡፡አንዳንዴ ደግሞ ጉዳዩ ከሮ እስከ ሕይወት መጠፋፋት ሊያደርስ ይችላል፡፡እናንተም በሕይወታችሁ ውስጥ በአእምሯችሁ የምታመላልሱት ጉዳይ ሁሉ የዚሁ ምሳሌ ነፀብራቅ ነው፡፡

ስለዚህ በአእምሯችሁ በየእለቱ የምታመላልሱት ጉዳይ ፍቅር ነው?፣ ስኬት ነው?፣ ለውጥ ነው?፣ አንድነት ነው?፣ በእምነት ስለመጠንከር ነው?፤ ወይስ ስለውድቀት ነው? መልሱ እናንተ ጋር ነው ያለው። እንደውም ጥናቶች የሚያሳዩት በየሰከንዱ ከአስራ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሀሳቦች በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ እንደሚመላለሱ ነው፡፡ይህ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ በቀንና በወር ሲታሰብ ደግሞ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ስለዚህ በሕይወታችን ምን ላይ ማተኮር እንዳለብን፣ ፍላጎታችን ምን እንደሆነና የት መድረስ እንደምንፈልግ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። እቅዳችንን፣ ግባችንንና ራእያችንን ማወቅ ግዴታችን ነው፡፡ ምን አይነት ሕይወት መኖር እንደምንፈልግ ማወቅ አለብን፡፡ የራስህ ቤት፣ ሃብት፣ ድርጅትና ሌሎችም እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ? ስለዚህ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ከአእምሮህ ውስጥ አውጥተህ በወረቀት ላይ ፃፋቸው፡፡ በዚሁ መሰረት በቅድሚያ እቅድ አውጣ፡፡ እቅድህ አጭር፣ መካከለኛና የረጅም ግዜ ሊሆን ይችላል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ያወጣኸውን እቅድ በመልካም ጎኑ አድርገው ወይም ጀምረው፡፡ በርግጥ ሁሌም ቢሆን መጥፎ ሃሳቦች ወደ አእምሯችን በተደጋጋሚ ይመላለሳሉ፡፡ ሆኖም ግን መፅናት ያለብን መልካሙ ሀሳብ ላይ ነው፡፡ የምትፈልገው ውጤት ባይመጣም እንኳን ውጤት እንደሚመጣ በውስጥህ መሳል አለብህ፡፡ ለምሳሌ “ምን አይነት ቤት ውስጥ መኖር ትፈልጋለህ?፡፡ ተብለህ ብትጠየቅ ምን አይነት ቤት ውስጥ ነው መኖር የምትፈልገው? ብዙ አይነት ቤት አለ፡፡ ምርጫው ያንተ ነው፡፡ ነግር ግን መኖር የምትፈልግበትን ቤት በምናብህ ሳለው፡፡ቤቱ ያንተ እንደሆነ እመን፡፡ በውስጡ እየኖርክበት እንደሆነ አስብ፡፡

ሀሳብህን እውን ለማድረግና በምትፈልገው ቤት ውስጥ ለመኖር ታዲያ ካንተ በኩል ቁርጠኝነት፣ ፅናትና ዘለቄታዊነት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንደተሰጠህና እንዳገኘኸው አድርገህ ምኞትህን አውን ለማድረግ ትጋ፡፡ ለዚህም እምነት ሊኖርህ ይገባል፡፡በአእምሮህ ውስጥ የተፀነሰው ሃሳብ ነው ወደ ቃልና ድርጊት ተቀይሮ እውን የሚሆነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢሊየነር የሆኑና በሀብትም ሆነ በዝና የናኙ ሰዎች ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት ስለተማሩ ብቻ ሳይሆን ያሰቡትን ሃሳብ እውን በማድረጋቸው ነው፡፡ስለዚህ አንተም ብትሆን ጭንቅላትህን አሰራው፤ በአእምሮህ ውስጥ የሚመላለሰውን ሀሳብ አውጣውና እውን አድርገው።

ስለምንፈልገው ነገር በማሰብና በማሰላሰል በሕይወታችን ላይ ለውጥ ማምጣት ከፈለገን የምንፈልገው ነገር ላይ ሙሉ ትኩረታችንን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እዚህ ጋር አይምሯችን ሁለት ክፍል እንዳለው ልብ ልንል ይገባል፡፡ የመጀመሪያው ኮንሺየስ ወይም ንቁው የአእምሮ ክፍል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሱብኮንሺየስ ወይም ድብቁ የአእምሮ ክፍላችን ነው፡፡ንቁው የአእምሮ ክፍላችን እያንዳንዱን ስራ የምንሰራበት ሲሆን፣ ድብቁ የአእምሮ ክፍል ግን ብዙም ጥቅም የሚሰጥ የማይመስለው፤ ነገር ግን ከተሰራበት አስገራሚ ውጤቶችን የሚያሳይ የአእምሮ ክፍል ነው፡፡

ስለዚህ በሕይወታችን ለውጥ ለማምጣት ፍላጎታችን ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ የምንፈልገው ነገር እውን ሆኖ ከማየታችን በፊት በምናብ መሳል ትልቁ የስኬት ሚስጥር እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይህ ነው ወደ እምንፈልገው ስኬት የሚንደረድረን። ይህ ነው በህይወታችን ለውጥ ማምጣት የሚያስችለን። ስለዚህ ፍላጎት ላይ በማተኮር የምንፈልገውን ነገር አውን ለማድረግ ነገሩን በምናብ በመሳል በአእምሯችን ውስጥ በተደጋጋሚ ማመላለስ ያስፈልጋል፡፡ሕልማችን እውን እንዲሆን ማመን ያስፈልጋል፡፡ይህ ማለት የምንፈልገው ነገር እንደሆነልን አስበን በምናባችን ወይም በሕሊናችን ማየት ነው፡፡

በአንደበታችን ደግሞ ያሰብነው ነገር እውን እንደሆነ አስበን ማመስገን ያስፈልጋል፡፡ ያሰብነው ነገር ባይሳካ እንኳን ቢያንስ በምናባችን አይተነዋል። ስለዚህ ሌላ ጊዜ እውን መሆኑ አይቀርምና የምንፈልገውን ነገር በአእምሯችን ውስጥ መሳልና ደግሞ ደጋግሞ የማመላለስ ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል ያስፈልገናል። ለምሳሌ አንድ ሰው የሆነ ነገር ሲያድረግላችሁ ታመሰግኑታላችሁ፡፡ ባያደርግላችሁም ቢያንስ ለጥረቱ ስትሉ ታመሰግኑታላቸው፡፡ልክ እንደዛው ሁሉ በአይምሯችሁ ስታመላልሱት የነበረው የሃሳብ ፍላጎት እውን ሳይሆን ቢቀር ማመስገን እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባችሁም፡፡ ምክንያቱም ሀሳብ መቋጫ የለውምና ዳግም በአእምሯችሁ ሌላ የፍላጎት ሃሳብ እንዲመላለስ በማድረግ ሃሳባችሁን እውን ማድረግ ትችላላችሁ፡፡

ስለዚህ ስሜታችሁን በምትፈልጉት ነገር ላይ ማቆየት ይኖርባችኋል፡፡ ውጤታማ እንደምትሆኑ፣ የምትፈልጉት ቦታ ላይ እንደምትደርሱ አምኖና ይህ እንደተሳካ አስቦ መስራት ያስፈልጋል፡፡መስራትና መተግበር ያለብንን ነገሮች ማድረግ፤ ሁሌም በጎ በጎ ነገሮችን ማሰብና መመኘት፤ ብሎም፣ ይህን ለአእምሮ መንገር፣ ለሰዎችም ማካፈል፣ የመስጠትና መቀበል ሕግን በደምብ መተግበር ከምናብ ዕይታ ወደ እውናዊ ክስተት የሚያንደረድሩ ቁልፍ የሕይወት መርሆች ናቸው፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You