ፖሊዮ (ፖሊዮሚለትስ) ተብሎ የሚጠራው የልጅነት ልምሻ በሽታ በ1800 አካባቢ እንደተከሰተ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡የልጅነት ልምሻ በዋናነት የሚያጠቃው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣ በቫይረሱ በተበከለ ምግብ እና ውሀ አማካኝነት ወደ ሰውነት ሲገባ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡በሽታው ዓይነት 1፣ ዓይነት 2፣ እና ዓይነት 3 በሚባል ይታወቃል። በዘላቂነት የሰውን የአካል ቅርፅ በመቀየርም ለአካል ጉዳት ይዳርጋል፡፡ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ በሽታው ለሞትም ያበቃል፡፡
በአንድ ወቅት ፖሊዮ እንደሌሎች በሽታዎች ሁሉ ዓለም አቀፍ ስጋት ነበር፡፡በፖሊዮ ወይም የልጅነት ልምሻ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በርካታ ሕፃናት ለአካል ጉዳተኛነት፣ ባስ ሲል ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል፡፡እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ፖሊዮ በ1900 በወረርሽኝ መልክ በኢኮኖሚ አደጉ በተባሉ አገሮች ተከስቷል።
ሆኖም በሽታው በሕክምና የማይድን መሆኑን የተረዳው የዓለም የጤና ድርጅት ታዲያ እኤአ በ1988 በሽታውን በክትባት መከላከል የሚያስችል ስልት በመቀየሱና ተግባራዊ በማድረጉ በወቅቱ የልጅነት ልምሻ በነበረባቸው 125 አገራት በየዓመቱ ይመዘገብ የነበረው 350ሺህ የልጅነት ልምሻ በሽታ በዓመት ወደ 175 መውረድ ችሏል፡፡በዚህም በርካታ ሕፃናትን ከአካል ጉዳተኛነትና ከሞት መታደግ ተችሏል፡፡
ምንም እንኳን እንደ ሁልጊዜው ሁሉ አዲስ ክትባት ሲገኝ በቅድሚያ ተደራሽ የሚሆነው ላደጉት ሀገራት ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት በሂደት የፖሊዮ ክትባቱ ደርሷቸው ህፃናቶቻቸውን ከትበዋል፡፡በዚህም በጊዜው ሊደርስ የሚችለውን የአካል ጉዳትና ሞት መቀነስ ችለዋል፡፡ሆኖም አሁንም ድረስ ፖሊዮ፣ በተለይ ገና አዳጊ በሆኑ ሀገራት ለሕፃናት አካል ጉዳተኛ መሆንና ሞት መንስኤ መሆኑን ቀጥሏል።
እንዲህም ሆኖ ኢትዮጵያ የልጅነት ልምሻን በክትባት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡በአስመዘገበችው ውጤትም ኢትዮጵያ ከፖሊዮ ነፃ ተብላ የምስክር ወረቀት አግኝታ ነበር፡፡ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከበሽታው ነፃ ተብለው የነበረ ቢሆንም ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በሶማሌ ክልል የፖሊዮ ቫይረስ ያለበት ግለሰብ በመገኘቱ ክትባቱ እንደገና እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ክትባት ዋናው መፍትሔ መሆኑን በመገንዘብም እስካሁን ድረስ በሁለት ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተደርጓል፡፡በዚህም በተደረገ የመጀመሪያ ዙር ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን መከተብ ተችሏል፡፡በሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባትም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከትበዋል፡፡
እንግዲህ ፖሊዮ በአደጉት ሀገራት ታሪክ ሆኖ ከቀረ የሰነበተ ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ገና በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ምንም እንኳን እየቀነሰ እንደመጣ ቢነገርም አሁንም አልጠፋም፡፡በተለይ ደግሞ በአፍሪካ በዋናነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ፖሊዮ አሁንም ድረስ አለ፡፡በፖሊዮ ምክንያት ሕፃናት አሁንም አካል ጉዳተኛ ይሆናሉ፤ ይሞታሉ፡፡በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስከተብ ዝግጁ አለመሆን፣ በቀጠናው የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችና የፖሊዮ ክትባት ተደራሽ እንዳይሆን ተፅእኖ ማሳደርና ሌሎችም ምክንያቶች በሽታው ከቀጠናው እንዳይጠፋ ምክንያት ሆነዋል፡፡በኢትዮጵያም የሚታየው ይኸው ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ ዓለም አቀፍ የፖሊዮ ቀን ‹‹በጋራ ፖሊዮን እናጥፋ›› በሚል መሪ ቃል ባሳለፍነው ሳምንት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በኢትዮጵያ የተከበረው፡፡በርግጥ የፖሊዮ ቀን ፖሊዮ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ግዜ ጀምሮ ይከበራል፡፡ዋናው ቁም ነገሩ ግን በየዓመቱ ቀኑን እየጠበቁ ማክበር ብቻ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ፖሊዮን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ ከሕብረተሰቡና ከመንግስት በኩል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግንና በትብብር መስራትን ይጠይቃል፡፡በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በክትባት ተደራሽ ለመሆን በተለይ በግጭት ቀጠና ያሉ ቦታዎች ወደ ሰላም ሊመለሱና የክትባት ስራውን ሊያግዙ ይገባል፡፡ሕብረተሰቡም ቢሆን በአንዳንድ የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት ልጁን ከማስከተብ ወደ ኋላ ማለት የለበትም፡፡ይህም ጤና ሚኒስቴር ሁሌም የሚጎተጉተው ጉዳይ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደሚናገሩት አስካሁን ድረስ ፖሊዮን ከናካቴው ከሀገሪቱ ለማጥፋት ባይቻልም፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1988 ጀምሮ ዓለም አቀፉ ፖሊዮን ጨርሶ የማጥፋት ንቅናቄ /Global Polio Eradication Initiative – GPEI/ያስቀመጠቻቸውን ዋና ዋና የፖሊዮ ማጥፋት ስልቶች በመተግበር በርካታ ስራዎችን ሰርታለች፡፡በዚህም ከ99 ነጥብ 9 በመቶ በላይ የፖሊዮ ጉዳቶችን መቀነስ ችላለች፡፡በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናትም ከሕመም፣ ከሞትና ከአካል ጉዳተኝነት አትርፋለች። በዚህ ስኬት ውስጥም የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የክትባት አገልግሎት ታሪክ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ይነገራል፡፡ከነዚህ የክትባት አገልግሎቶች ውስጥ ታዲያ አንዱ የፖሊዮ ክትባት ነው፡፡የፖሊዮ ክትባት በኢትዮጵያ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ሕጻናትን ከሞት፤ ከሕመምና ከአካል ጉዳት ለመታደግ ተችሏል፡፡በሌላ በኩል እንደ ሀገር የኮቪድ_19 ክትባትን ጨምሮ፣ ከአስራ ሶስት በላይ ሌሎች የክትባት አይነቶች ለሕጻናትና ለሕብረተሰቡ እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡በአሁኑ ግዜ ደግሞ የማሕፀን በር ካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ሴት ልጆች እየተሰጠ በመሆኑና የማህፀን በር ካንሰርን በክትባት መከላከል ስለሚቻል ሕብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጤና ሚኒስቴር ይጠይቃል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፖሊዮ ነፃ ሆኖ ለማደግ ሁሉም ሕፃናት ክትባት የማግኘት መብት እንዳላቸው በመገንዘብ ቤት ለቤት የክትባት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት በመስራት ሙሉ በሙሉ ፖሊዮን በማጥፋት ከስነ-ልቦና ጫናና ከአካል ጉዳት መታደግ ይገባል፡፡ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡ፖሊዮ ወይም የልጅነት ልምሻን ሕፃናትን በወቅቱ የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ መከላከል የሚቻል ከመሆኑ አኳያ መከላከል ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል፡፡ይህም በፖሊዮ ምክንያት በሕፃናት ላይ ለሚደርሰው የአካል ጉዳት ድጋፍ ሊወጣ የሚችለውን ወጪ ለመቀነስ ያስችላል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ፖል ሜይኑካ በበኩላቸው እንደሚሉት አሁንም ቢሆን ከፖሊዮ ነጻ የሆነች ኢትዮጵያና አፍሪካን ለመፍጠር ቅንጅታዊ ስራዎችና ትብብሮች ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባቸው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ፖሊዮን ለማጥፋት በፅኑ ፍላጎትና በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል፡፡ለዚህ ታዲያ በሀገር ውስጥ ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ታችኛው ሕብረተሰብ ክፍል ድረስ ፖሊዮን ለማጥፋት ከሚደረገው የጋር ርብርብ በተጨማሪ የዓለም ጤና ድርጅት የፖሊዮ በሽታ ከኢትዮጵያ እስኪወገድ ድረስ የገባውን ቃል መጠበቅ ይኖርበታል፡፡አስፈላጊውን ድጋፍም አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
በርግጥ ፖሊዮን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረጉ ጥረቶች ብዙ ለውጦች እየመጡ ነው፡፡የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ባደረገው ከፍተኛ ጥረትና ፖሊዮን የማጥፋት ዘመቻ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2017 በአፍሪካ ክልላዊ የፖሊዮ ማጥፋት ኮሚሽን ባካሄደው መደበኛ ክትትል ሂደት ኢትዮጵያ ከዱር ፖሊዮ-ነፃ በመሆን እውቅና ማግኘቷ የዚህ ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ይህም ስኬት የተገኘው የጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በሰራቸው ጠንካራ ስራዎችና የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ ነው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጤና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር መሰረት ዘላለም እንደሚገልፁት ከፖሊዮ ነፃ ሆኖ ለማደግ ሁሉም ሕፃናት ክትባት የማግኘት መብት እንዳላቸው በመገንዘብ ቤት ለቤት የክትባት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት በመስራት ሙሉ በሙሉ ፖሊዮን ጨርሰን በማጥፋት ከስነ-ልቦና ጫናና ከአካል ጉዳት መታደግ ያስፈልጋል።
በተለይ ደግሞ በገጠራማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የፖሊዮ ክትባትን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ፖሊዮን ለማጥፋት የተጀመረውን አጠቃላይ ዘመቻ አጠናክሮ ማስቀጠል የግድ ይላል፡፡ግጭቶች በነበሩባቸውና በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ቦታዎች የሚገኙ ሕፃናትንም በተመሳሳይ በክትባት ተደራሽ መሆንና ሕፃናቱን ከአካል ጉዳትና ከሞት ማዳን ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡ለዚህ ደግሞ እስከታች ድረስ ያሉ የክልል መዋቅሮችና ጤና ሚኒስቴር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል፡፡
በዚህ በ2023ቱ “በጋራ ፖሊዮን እናጥፋ” በሚል ባሳለፍነው ሳምንት በተከበረው ዓለም አቀፍ የፖሊዮ መታሰቢያ ቀን ጉባዔ ላይ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የፖሊዮ በሽታ አሁን ላይ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ገለፃ በጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት፣ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉት በፖሊዮ ክትባት ተደራሽ ሆነው ፖሊዮን እንዲያጠፉ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችና ስትራቴጂዎችም ቀርበዋል፡፡የልምድ ልውውጥም ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ፣ የአጋር ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተጋበዙ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም በተገኙበት፣ በቀጣይ ከፖሊዮ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ምን ሊደረግ እንደሚገባ የሚያመለክቱ አቅጣጫዎች ተቀምጧል፡፡
ሁሌም ቢሆን ‹‹ፖሊዮን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት›› እየተባለ በየዓመቱ ይነገራል፡፡ፖሊዮ ግን ሲጠፋ አልታየም፡፡ስለዚህ ፖሊዮ ከኢትዮጵያ ጠፍቶ ልክ እንደሌሎቹ ሀገራት ታሪክ ሆኖ እንዲቀር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡በቁርጠኝነት መስራት ከተቻለ ደግሞ ፖሊዮን ከኢትዮጵያ ማጥፋትና ፖሊዮን ለማጥፋት የሚውለው ገንዘብ ለሌሎች የልማት ስራዎች ማዋል እንደሚቻል የብዙዎች እምነት ነው፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016