
አዳማ:- በዘንድሮው ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃ ሚዎች ቁጥር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ60 ሚሊዮን በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዱአለም በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን በአራት ክልሎችና በ13 ወረዳዎች ላይ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በአሁኑ ጊዜ ከ1 ሺህ 90 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በዘንድሮው ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በየዓመቱ አዳዲስ አባላትን የሚመዘግብና ነባር አባላትን ደግሞ የሚያድስ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸው፤ በእዚህ ዓመት ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሲባል በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለትም ሦስትም ሊኖር እንደሚችልና ከ60 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች በእዚህ ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆኑ የቻሉት በእማና አባወራ ደረጃ ተቆጥረው መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር በእዚህ ዓመት ከ60 ሚሊዮን በላይ የሆነው የነበሩ፣ አድሰው የመጡና አዲስ የተመዘገቡ በአንድ ላይ ተቆጠረው መሆኑን አስረድተዋል።
ከፈንድ አሰባሰብ ጋር ተያይዞም በእዚህ ዓመት መክፈል ከሚችሉ በመዋጮ፣ መክፈል ከማይችሉ ከክልል በተናጠል ድጎማ የገባና ያንን ታሳቢ አድርጎ በፌዴራል መንግሥት የተደረገውን ድጎማ ጨምሮ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ለጤና መድህን ሽፋን መሰብሰቡንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘው ገልጸዋል።
አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውን የጤና ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማትን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ማድረሱንም ተናግረዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የአገልግሎት ጥራት ማነስ በየቦታው የሚታይ ችግር መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፤ በተለይ በስጋት ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ የታዩ ክፍተቶች በመኖራቸው በቀጣይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም