የሕዳር በሽታ እንዳይለምድብን!

በተለምዶ ‹‹የሕዳር በሽታ›› እየተባለ የሚጠራ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተከሰተ ወረርሽኝ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት ነው፡፡ በዘመኑ እንደ አሁኑ የረቀቀ የመመርመሪያ ቴክኖሎጂ የለም፡፡ ክስተቱ እንደ ቁጣ (መለኮታዊ ኃይል) ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ የሕዳር በሽታ የተባለው ደግሞ የተከሰተው በሕዳር ወር ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ሕዳር ሲታጠን›› የሚባል ልማድ አለ፡፡ “ለምን በሕዳር ወር ሆነ?። የሚለውን ጥያቄ በአሁኑ ዘመን ጥናት ማወቅ እንችላለን፡፡

ሰሞኑን የጤና ተቋማትና ማሕበራት መግለጫዎችን እየሰጡ ነበር፡፡ በሰጡት ማስጠንቀቂያ እንደተገለጸው፤ የጥቅምት እና የሕዳር ወር ጉንፋን መሰል ሕመሞች ይታዩበታል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በሁለት ሺህ ያህል ናሙናዎች ላይ ምርመራ አድርጎ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ መከሰቱን ይፋ አድርጓል። ለጉንፋን መሰል ክስተቶች ምክንያት የተባለውም፤ የዝናብ ወራት ማለፉን ተከትሎ በጥቅምትና ሕዳር ወቅት ላይ አብዛኛውን ጊዜ የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ የሚከሰት መሆኑ ነው፡፡ ከጥናቱ ባሻገር ሁላችንም በየአቅራቢያችን እንደምናስተውለው ሰሞኑን ብዙ ሰው የጉንፋን መሰል ሕመሞች ታማሚ ሆኗል፡፡ ይህ ክስተት በዚህ ዓመት ብቻ የተስተዋለ ሳይሆን የጥቅምትና ሕዳር ወራት ላይ በየዓመቱ የሚታይ ነው፡፡

ትዝብታችን እዚህ ላይ ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የጤና ባለሙያዎች ማሕበራት ለእንዲህ አይነት ክስተቶች ‹‹መከላከያ›› ብለው ያስቀመጧቸው ነገሮች አብዛኞቹ የማንተገብራቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በዓመቱ ጥቅምትና ሕዳር ወር ላይ የእንዲህ አይነት ክስተቶች ተጠቂ እንሆናለን፡፡ የወቅት መፈራረቅ በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ክስተት አይደለም፤ ዳሩ ግን የሰለጠኑት አገራት ሰው ሰራሽ በሆነው ጥበብ ይከላከሉታል፡፡

ተፈጥሮ ነውና ክረምት ተራውን ለመኸር ወቅት ይለቃል፡፡ በዚህን ጊዜ ብዙ አበቦች ይፈነዳሉ፤ ብዙ የዕፅዋት አይነቶች ያፈራሉ፡፡ ይህ ክስተት የአየር ለውጥ ያመጣል፡፡ በክረምት ውሃ የሞሉ ወንዞች መድረቅ ይጀምራሉ፡፡ እስከ ጥቅምት መጨረሻ መቆየት የቻሉ ወንዞች ካሉ ሕዳር ላይ ይደርቃሉ። ውሃ ያጠራቀሙ ቦታዎች ሁሉ ሲደርቁ ሌላ ሽታ ይፈጠራል፡፡

እነዚህ ከላይ የተገለጹት የተፈጥሮ ክስተቶች ወደ በሽታነት የተቀየሩት በእኛ በሰዎች ጥፋት ነው፡፡ ውሃ ይዘው የነበሩ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ እንጥላለን፤ ውሃው ሲደርቅ መጥፎ ሽታ ይፈጥራል፡፡ ውሃ በተፈጥሮ ብቻውን ሽታ የለውም።የሚረብሽ ሽታ እንዲኖረው አድርገን ያበላሸነው እኛ ሰዎች ነን፡፡ በክረምትና በመኸር ወቅት ላይ ያለውን የአየር መለዋወጥ በቴክኖሎጂ ማስተካከል ባንችል እንኳን ቢያንስ በቀላሉ ባለመበከል መከላከል እንችል ነበር፤ ዳሩ ግን እዚህ ደረጃ ላይ ባለመድረሳችን የሕዳር በሽታ በዚህ ዘመንም እየደገመን ነው፡፡

የጤና ተቋማቱ “መከላከያ፡፡ ብለው ካስቀመጧቸው ነገሮች ውስጥ ሌላው ደግሞ የግልና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ነው፡፡ ለአንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ሊነገር የሚገባውን የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉዳይ ከዲግሪ በላይ የትምህርት ደረጃ ላለው ማሕበረሰብ ማስተማር ምን ያህል ገና ብዙ እንደሚቀረን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ይህ ችግር እየተፈጠረ ያለው “የተማሩ፡፡ በሚባለው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጭምር ነው፡፡ በትልልቅ ተቋማት ውስጥ የምናያቸው ችግሮች አሳዛኝ ናቸው። እነዚያ ተቋማት ውስጥ ያሉት ግን “የተማሩ፡፡ የሚባሉ ሰዎች ናቸው፡፡

ጉንፋን እና መሰል በሽታዎች የሚከሰቱት ከመጥፎ ሽታ ነው፡፡ እነዚህ መጥፎ ሽታዎች የሚፈጠሩት ደግሞ ካለማወቅ ሳይሆን ከከፍተኛ ቸልተኝነት ነው። አልኮል ጠጥቶ ትራንስፖርት ውስጥ የሚገባ ሰው ሊረብሽ እንደሚችል አይጠፋውም፡፡ የጫማውን ንጽህና የማይጠብቅ ሰው ጫማ መጥፎ ሽታ እንደሚፈጥር አይሳነውም፡፡ ይህ መጥፎ ሽታ ጉንፋን እና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎችን እንደሚያመጣ አይይጠፋውም፤ ዳሩ ግን እነዚህ ሁሉ የሚሆኑት በከፍተኛ ቸልተኝነት ነው፡፡

ምንም እንኳን የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ላይ ቢሆኑም፤ ዳሩ ግን ዋናው ለውጥ መምጣት ያለበት የሰዎች ጭንቅላት ላይ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ብዙ የወንዝ ዳርቻዎች አፍንጫ ተይዞ የሚታለፉ ናቸው። ራስ የሚያዞር መጥፎ ሽታ ያላቸው ናቸው፡፡ ያ መጥፎ ሽታ የተፈጠረው በክረምቱ ወቅት የወረደው ዝናብ ቆሻሻ ሆኖ ሳይሆን እኛ ሰዎች በክለነው ነው። በተጠራቀመው የዝናብ ውሃ ላይ ሌላ ባዕድ ነገር ቀላቅለንበት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ የሚጥሉት ወንዝ መሰል ነገር ውስጥ ነው፡፡

የግዴለሽነታችን ነገር በጣም አሳሳቢ ነው። እንኳን እንዲህ ክረምትና መኸር የሚቀያየርበት ወቅት በሙሉው ክረምት ወይም የበጋ ወቅት ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ሙሉ ክረምት ሳይሻል አይቀርም፡፡ በእንዲህ አይነቱ ወቅት ብዙ መጥፎ ሽታዎች አሉ፡፡ በተፈጥሮ የተጠራቀመው እንዳለ ሆኖ፤ ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ደግሞ ችግሩን ያባብሱታል። ከእነዚህም አንዱ በየሰፈሩ የሚሰበሰብ ቆሻሻ ነው፡፡

በብዙ አካባቢዎች እንዳስተዋልኩት በሳምንቱ ውስጥ የተወሰኑ ቀናት (ለምሳሌ እሁድ፣ ረቡዕ እና ዓርብ) በየአካባቢው ያሉ የተሰበሰቡ ቆሻሻዎች የሚነሱበት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ቀናት የማንሻ መሆናቸውን የየአካባቢው ነዋሪ ያውቃል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ በዕለቱ የሚያነሱ ሰዎች ሲመጡ በጡሩንባ ‹‹ቆሻሻ አውጡ!›› እየተባለ በከፍተኛ ጩኸት ይነገራል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ቀን እየተበሳጨሁ ‹‹አንዴ ከተነገረ አይበቃም እንዴ!?›› ብየ በውስጤ እገረማለሁ፡፡ ለካ ወደው አይደለም፡፡

አሳዛኙ ነገር ያ ሁሉ ጩኸት ተጮሆ ቆሻሻ የማያወጡ ሰዎች አሉ፡፡ ልክ አንሺዎች አንስተው ሲሄዱ ከየት እንደመጡ ሳይታወቅ ቆሻሻ ጥለው ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንግዲህ ሊቀጡ ይገባ ነበር፡፡ ሲጀመር የቆሻሻ ማንሻ ቀናትን ማወቅ ነበረባቸው። እሱም ይረሳል እንበል፤ ለማስታወስ ተብሎ ያን ያህል አካባቢው እስከሚናጋ ድረስ ቅስቀሳ ሲደረግ ማውጣት ነበረባቸው፡፡ እሱንም ሳይሰሙ ቀሩ እንበል፤ ቢያንስ ምናለ በሚቀጥለው ቀን የሚያነሱት ሲመጡ ቢያወጡት? እንዲያው ምናልባት ሆን ብለው ይሆን?

በሱፍ እና ከረቫት ዝንጥ ብሎ የለበሰ ሰው ያለምንም መሸማቀቅ መንገድ ዳር የተጠቀመበትን ሶፍት ይጥላል፡፡ ይሄ ለዚያውም ቀላሉ ነው፤ ከዋናው አስፋልት ገለል ብሎ ሽንቱን የሚሸናው ማንም ሰው የሚታዘበው ነው፡፡ የግንብ ጥግ ሆኖ መጥፎ ሽታ የሌለው ላይገኝ ነው ማለት ነው፡፡ የውሃ ማፋሰሻዎች ሽንትን ጭምር ነው የሚያፈሱት ማለት ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ በሕዳር ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ጉንፋን ቢይዘን ምን ይገርማል? እንዴት በሽታ እንኳን አያስተምረንም? የሕዳር በሽታ እንዳይለምድብን አሁንም ቀልብ እንግዛ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You