በአዲስ መልክ የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ምድብ ድልደል ይፋ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና የከፍተኛ ሊግ ክለቦች እርስ በእርሳቸው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል:: በመርሃ ግብሩ መሠረትም 32 ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው እንደሚፋለሙም ተገልጿል::
ታሪካዊ የሆነውና በቀድሞ ስያሜው የኢትዮጵያ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሲባል የቆየው የኢትዮጵያ ዋንጫ ከሦስት ዓመት መቋረጥ በኋላ ወደ ውድድር መመለሱ የሚታወስ ነው:: ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ብቻ የሚያፎካክር ሲሆን፤ አሁን ግን አሠራሩን በመቀየር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ክለቦችን በማካተት እያወዳደረ ይገኛል:: በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ዙር ውድድራቸውን አከናውነው ወደ ሁለተኛ ዙር የተቀላቀሉትን የከፍተኛ ሊግ ክለቦችንና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን እርስ በርስ ያገናኛል::
በመጀመሪያ ዙር 32 የከፍተኛ ሊጉ ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው ከፍተኛ የሆነ የእርስ በርስ ፍልሚያ ካካሄዱ በኋላ ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉ ክለቦች መለየታቸው አይዘነጋም:: እነዚህ ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉ 16 የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም ከ16ቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ ይፋለማሉ:: ውድድሩም ከኅዳር 15-17/2016 ዓ∙ም ድረስ ወደ ፊት በሚገለጽ ቦታ የሚካሄድ ሲሆን፤ ጠንካራ የሆነ ፉክክርም ይስተናገድበታል ተብሎ ይጠበቃል::
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው በዚህ ፉክክርም ሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች በተለያዩ ምድቦች ተደልድለው ውድድራቸውን እንደሚያከናውኑም ታውቋል:: በፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚ ባለድል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዲስ አዳጊው ሀምበርቾ ዱራሜ ይፋለማል:: የሊጉ ሌላኛው አዲስ አዳጊ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ ካፋ ቡና ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ ያካሂዳል:: ሌላው ሁለቱን የሊጉ ክለቦች የሚያፋልመው ሀድያ ሆዕሳናን ከአዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያገናኘው ጨዋታ ነው:: ወላይታ ድቻ ከደሴ ከተማ፣ ቢሾፍቱ ከተማ ከሀላባ ከተማ፣ አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና፣ ነገሌ አርሲ ከስልጤ ወራቤ እና ኢትዮጵያ መድን ከድሬዳዋ ከተማ በዚሁ ምድብ ውድድራቸውን የሚያደርጉ ክለቦች ናቸው:: የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፉክክርም በተለይ በአጓጊነት ይጠበቃል::
በሌላኛው ምድብም እንዲሁ 16 ክለቦች ተደልድለው ውድድራቸውን የሚያደርጉ ሲሆን፤ እስከ መጨረሻው የውድድሩ ፍጻሜ ድረስ በርካታ ትዕይንቶችን እንደሚያስመለክቱም ይገመታል:: በዚህም መሠረት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ፉክክርን ማስመልከት የቻለው ባህር ዳር ከተማ ከሸገር ከተማ ይጫወታል:: ኦሮሚያ ፖሊስ ከአርባምንጭ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ይጫወታሉ:: መቻል ከወልቂጤ ከተማ ጋር የሚጫወት ሲሆን፣ ደብረብርሃን ከተማ ከጋሞ ጨንቻ ጋርም ይፋለማሉ:: ፋሲል ከነማ ከነቀምት ከተማ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑም ይሆናል:: በዚህ ታሪካዊ ውድድር እስከ መጨረሻው ማን ጥሩ ብቃት አሳይቶ ቻምፒዮን ይሆናል የሚለው አጓጊና በውድድሩ ፍጻሜ መልስን የሚያገኝም ይሆናል::
የኢትዮጵያ ዋንጫ እአአ ከ1945 ዓ∙ም ጀምሮ እየተካሄደ በርካታ ክለቦችን ቻምፒዮን ማድረግ የቻለ አንጋፋና ታሪካዊ ውድድር ነው:: ነገር ግን ከ1961-69 ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ በ1979፣ በ1989፣ ከ1991-92፣ በ2012 እና ከ2019 ዓ∙ም አሁን እንደ አዲስ እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስም ባሉት ዓመታት ውድድሩ አልተካሄደም ነበር:: በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ከቀረባቸው ዓመታት ውጪም ውድድሩ በርካታ የኢትዮጵያ ክለቦችን ለብዙ ዓመታት እያፋለመ እዚህ ደርሷል:: በዚህም የቀድሞ የኢትዮጵያ አካል የነበረችው ኤርትራ ክለቦችም ጭምር ተሳትፈው ቻምፒዮን መሆን ችለዋል:: ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን 10 ጊዜ ከፍ አድርጎ ያነሳ ክለብ ሲሆን፣ መቻል 9 ጊዜ ማንሳት ችሏል:: ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ ቻምፒዮን ሲሆን፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4 ጊዜ አሸናፊ ነበር:: ኢትዮጵያ መድን እና ደደቢት ደግሞ 2 ጊዜ ዋንጫውን መውሰድ የቻሉ ክለቦች ሆነው በታሪክ ማህደር ሰፍረዋል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016