ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለስራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የክልሉ ማዕድን ልማት

የአማራ ክልል በተፈጥሮ ሀብቶች ባለጸጋ ከሆኑ ክልሎች አንዱ ነው:: ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶቹ ውስጥ የማዕድን ሀብት ተጠቃሽ ነው:: ከክልሉ እምቅ የማዕድን ሀብት ክምችቶች መካከልም እንደ ወርቅ፣ ኦፓል (የከበሩ ማዕድናት)፣ የድንጋይ ከሰል፣ ጂብሰም፣ የኖራ ድንጋይ ይገኙበታል:: የማዕድን ሀብቶቹ በጥናት የተለዩ ናቸው። ይሁንና በክልሉ ካሉት የማዕድን ሀብቶች እስካሁን 70 በመቶ ያህሉ በጥናት እንዳልተለዩ መረጃዎች ያመላክታሉ:: በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የብረት ማዕድን ስለመኖሩም ሌሎች መረጃዎች ይጠቁማሉ::

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴም በርካታ የማዕድን ሀብቶች እንዳሉ ይገልጻሉ:: እስካሁን 40 የሚደርሱ ማዕድናት በጥናት ተለይተዋል በማለትም ከእነዛ ውስጥ፤ ኦፓል፣ ወርቅ ፣ ጂብሰም፣ የድንጋይ ከሰል፣ ቤንቶናይት፣ ሁሚስት፣ የኖራ ድንጋይ እና የመሳሳሉት የማዕድናት አይነቶች እንደሚገኙ አመልክተዋል:: ዘንድሮም በጥናት ከተለዩት ማዕድናት መካከልም ሲሊከስንት የተሰኘው ማዕድን ይገኝበታል::

አቶ ታምራት እንደሚሉት፤ ማዕድናቱን ለሚያለሙ ባለሀብቶች ፍቃድ እየተሰጠ ሲሆን፤ ሲሊከስንት ማዕድንን ለሚያለሙ ሰባት ባለሀብቶች ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ለአንድ ባለሀብት ፍቃዱ ተሰጥቷል::

የኦፓል ማዕድን

የኦፓል ማዕድን ምርት በአብዛኛው በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ይገኛል:: በሁለቱ ዞኖች በሚገኙት ስምንት ወረዳዎች 7ሺ430 የሰው ኃይል ያላቸው 69 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ኦፓል እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ናቸው:: በ2016 በጀት ዓመት 18ሺ 156 ኪሎግራም የኦፓል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ 7ሚሊዮን 200 ሺ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል:: በሩብ ዓመቱ 10ሺ959 ኪሎ ግራም የኦፓል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ፤ 324ሺ 428 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ ታምራት አስታውቀዋል:: ይህም ገቢ እሴት የተጨመረበትና ያልተጨመረበትን የኦፓል ምርት እንደሚያካትት ጠቁመዋል::

የወርቅ ማዕድን

በክልሉ በተደረገው ጥናት በጎንደር፣ በምዕራብ ጎጃምና በአዊ ዞን የተለያዩ ቦታዎች ላይ የወርቅ ማዕድን ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል:: በእነዚህ ቦታዎች ወርቅ ለማምረት አንድ ሺ156 የሰው ኃይል ያላቸው 67 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል::

በ2016 በጀት ዓመት 120 ኪሎ ግራም ወርቅ ለውጭ ገበያ በመላክ፤ 4ሚሊዮን 628ሺ 950 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል:: ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት፤ በክልሉ ወርቅ በአነስተኛ አምራቾችና በኩባንያ ደረጃ ባሕላዊና ዘመናዊ መንገድ ይመረታል:: በተያዘው በጀት ዓመት በኩባንያ ደረጃ 100ኪሎ ግራም ወርቅ ፤ በአነስተኛ አምራቾች ደግሞ 20 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዷል:: ለወርቅ አምራቾች በተለያዩ አካባቢዎች ሳይትና ቦታ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል::

ለአብዛኛዎቹ አምራቾች የተሰጣቸው ፍቃድ በምርመራ ላይ ስለሆነ፣ የምርመራ ፍቃዱ እንዳለቀ የምርት ፍቃድ ይሰጣቸዋል፤ የምርመራ ፈቃዱ የሚቆየው ለስድስት ወር ሲሆን፤ ከስድስት ወር በኋላ የምርት ፈቃድ ይወሰዳሉ:: አምራቾቹ የምርመራ ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ የምርት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ለአምስት አምራቾች ፍቃዶች ተሰ ጥተዋል ብለዋል::

ሌሎች ማዕድናት

ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ከታቀዱት የሌሎች ማዕድናት ምርት ውስጥ አምበር /ለተለያዩ ጌጣጌጦች መስሪያ የሚያገለግል ውብ ቀለም ያለው ማዕድን/ አንዱ ነው:: በተያዘው በጀት ዓመት 250 ኪሎ ግራም አምበር ለውጭ ገበያ በመላክ፤ 10ሺ 120 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል:: ወደ ውጭ ለመላክ በእቅድ ከተያዘው ውስጥ ሌላኛው የማዕድን ምርት ጂብሰም ሲሆን፤ 7ሺ 500ኪሎግራም ጂብሰም ለውጭ ገበያ በመላክ፤ 681 ሺ 819 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል::

የሥራ እድል ፈጠራ

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ በወርቅና በኦፓል የማዕድን ልማት ላይ 8ሺ 586 የሰው ኃይል ያላቸው አንድ ሺ336 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል:: ከዚህ በተጨማሪ የከበሩ ማዕድናትን እሴት ጨምረው ወይም ፕሮሰስ አድርገው በማምረት ለሀገር ውስጥ ሆነ ለውጭ ሀገር ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾች እንዳሉም ጠቅሰዋል::

በተያዘው በበጀት ዓመት ለ15 የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ እስካሁን ለአራት አምራቾች ፍቃድ ተሰጥቷል ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ የከበሩ ማዕድናት የእደጥበብ ብቃት ደግሞ በበጀት ዓመቱ 30 አምራቾች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ ለሦስት አምራቾች ፍቃድ ተሰጥቷል ብለዋል። በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ በ2016 በጀት ዓመት ለ45ሺ 143 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ በሩብ ዓመቱ ለ4ሺ149 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል::

የዘርፉ ተግዳሮቶች

በማዕድን ዘርፉ በመጀመሪያ ደረጃ የሚነሳው ችግር አምራቾቹ ማዕድኑን (ኦፓል ሆነ ሌሎች ማዕድናት) የሚያመርቱ በባሕላዊ መንገድ መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አክሳሪ ባልሆነ መንገድ ማዕድኑ እንዲወጣ ለማድረግ አነስተኛ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ከዚህ አኳያ ማዕድን ማውጣት የሚያስችል የተሻሻለ ቴክኖሎጂ እንዲቀርብላቸው እየጠየቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል:: የማዕድናት ሀብቱን በአግባብ አውጥቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂዎቹ አለመኖራቸው የዘርፉ ትልቅ ማነቆ ነው ይላሉ::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚነሳው ችግር ወደ ውጭ የሚላከው የማዕድን ምርት ጥሬ ኦፓል (ምንም እሴት ያልተጨመረበት፣ ፕሮሰስ ያልተደረገ) ነው:: በእዚህ ምርት ላይ ሀገር ውስጥ እሴት ቢጨመርበት ተጨማሪ የስራ እድል ሊፈጥር ይችላል:: ኦፓል እሴት ሳይጨመርበት ለውጭ ገበያ መቅረቡ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች ትልቅ ችግር ነው:: በዚህ የተነሳ የሚያመርቱት አነስተኛ ከመሆኑ በላይ ማዕድኑን ፕሮሰስ አድርጎ አለማውጣትም ችግር ይገጥማቸዋል::

አሁን ላይ እሴት ሳይጨመርበት እየተላከ ያለው ማዕድን ለውጭ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሪያ እየሆነ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል የቢሮ ኃላፈው፤ ማዕድናቱ ላይ እሴት በመጨመር የውጪውን ገበያ ፍላጎት ሊያረካ የሚችል ምርት ለማምረት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጉም ይጠቁማሉ::

እሳቸው እንዳመለከቱት፤ በሦስተኛ ደረጃ የሚነሳው የገበያ ትስስር ጉዳይ ነው:: በጣም አጭር የሆነና አምራቹ ወዲያውኑ ምርቱን ሸጦ ገቢውን እና ኑሮውን ሊያሻሽል የሚችልበት የገበያ ትስስር የለም:: በዚህም ምክንያት አምራቹ ምርቱን ለመሸጥ በተለያየ ቦታ ላይ ይንገላታል:: ሌላው ችግር በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ተጨማሪ ቴክኖሎጂ መግዛት የሚያችሉበት የብድር ሥርዓት አለመኖሩ ነው:: አበዳሪ ተቋማት ብድር ማቅረብ አለመቻላቸው እንደ ችግር እንደሚነሳ ይጠቀሳል::

በማዕድን ዘርፉ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ ወጥ ተግባር ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፈው ጠቁመዋል:: በተለያዩ ቦታዎች ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር እንዳለ ይታወቃል:: ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ማዕድን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የሚያዘዋወሩ የሚሸጡ፤ የሚገዙ አካላት ተበራክተዋል የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ እነዚህ አካላት ሕጋዊ መስመር ተከትለው ወጣቶችንም ሆነ ባለሀብቶችን ከመጠቀም ይልቅ ሕገወጥ በሆነ መልኩ በአቋራጭ ማዕድን ለመውሰድ የሚፈልጉ አካላት እንደሚታዩ አመላክተዋል::

መፍትሔዎች

በበጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ለዚህም በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ላይ ማዕድን መሸጫ የገበያ ማዕከል መገንባቱን አስታውቀዋል:: ማዕከሉን በማቋቋም ሥራ ለማስጀመር ከፋይናንስ ቢሮ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል:: ይህ የገበያ ማዕከል የገበያን ረጅም ሂደት ሊያሳጥር እንደሚችል አስታውቀው:: የገበያ ትስስር የሚያሰፋ እና ገዥዎችም ወደ ገበያ ማዕከሉ መጥተው መግዛት እንዲችሉ ሰፊ እድል የሚከፍት ነው ይላሉ::

ማዕድናቱ በሚገኙበት አቅራቢያ ላይ የማዕድን ዘርፉን ሊመራ የሚችል ተቋም ተመስርቷል ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው ሂደት በዞንም ሆነ በወረዳ ቅርንጫፎች አልነበረውም ብለዋል:: አሁን ላይ በዞን መመሪያ፣ በወረዳም ደረጃ ጽህፈት ቤት መዋቀሩን ገልጸዋል::

ለአብነትም በደላንታ ላይ የተገነባው የገበያ ማዕከል ተጠሪነቱ ለወረዳው ማዕድን ሀብት እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል:: ማዕከሉን በተለያዩ ቁሳቁስ በማደራጀት፤ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ኦፓል ረጅም ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል:: ከዚህ አንጻር ደላንታ ላይ ያለውን ጽሕፈት ቤት በማቋቋም፣ በማደራጀት፣ በማጠናከርና በቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል::

“የገበያ ማዕከሉን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ መመሪያዎች አዘጋጅተናል” የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በተለይ ኦፓል በሰሜን ወሎና በደቡብ ወሎ አካባቢ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ የደቡብ ወሎ ደላንታ ላለው የገበያ ማዕከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን የማሟላት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል:: በተያዘው በጀት ዓመትም በሰሜን ወሎም የገበያ ማዕከል ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል::

እንደ ክልል ሕገወጥነት ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የማእድን ሕገወጥነትን ለመከላከል ስራ ላይ ያለው ግብረ ኃይልም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል:: በየቀበሌውና በየወረዳው የሚዘዋወሩ ሕገወጥ ማዕድናት ከተለያዩ አጋር አካላት (ከፖሊሲ፣ ከፍትሕና፣ ከሰላምና ከደህንነት ጋር ተያያዥነት ካላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች) ጋር በመቀናጀት ኬላ በማቋቋምና ፍተሻ በማድረግ በሕገወጥ መልኩ የሚዘዋወሩ ማዕድናት ካሉ የመቆጣጠር ሥራ ለ መሥራት የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ መሆኑንና በቅርቡ በክልሉ የሚመለከተው አካል ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ አመላክተዋል:: መመሪያዎቹ ጸድቀው ወደ ሥራ ከገቡ ሕገወጥ የማዕድን የዝውውሮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል::

በሌላ በኩልም ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አንጻር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል:: በማዕድን ሚኒስቴር ደረጃ የማዕድን ንቅናቄ መድረክ ማይን ቴክስ ኤክስፖ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ በአማራ ክልልም በሕዳር ወር በማዕድን ዙሪያ በተለይ ሕገወጥ ዝውውር ያሳደረውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስረዳ የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ እንደሚካሄድ አመላክተዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016

Recommended For You