የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከትላንት በስትያ ከጅቡቲ ጋር አድርጎ በፍፁም የበላይነት 8ለ1 በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈችበት የምትገኘው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ወንዶች እግር ኳስ ውድድር ከጥቅምት 24/2016 ዓ.ም ጀምሮ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ስምንት ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር እያደረጉበት በሚገኘው በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ የጅቡቲ አቻዋን ከግማሽ ደርዘን በላይ ግብ በማስቆጠር ስታሸንፍ ስድስት ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል። አንድ ተጫዋች ደግሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን የወከሉት ወጣቶች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በጀርመኑ ስሪ ፖይንትስ ተባባሪነት በካፍ አካዳሚ ውስጥ የእግር ኳስ ስልጠናቸውን እየወሰዱ የሚገኙና እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የተካተቱበት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም የዕድሜ እርከናቸውና ሜዳ ላይ ባሳዩት ማራኪ እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ አሳይተዋል፡፡
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታቸው ደቡብ ሱዳንን በመግጠም 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት የተለያዩት እነዚህ ታዳጊዎች በውድድሩ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎም ተስፋ ተደርጎባቸዋል።
ተስፈኞቹ ታዳጊዎች በጅቡቲው ጨዋታ የጎል አካውንታቸውን በሁለተኛው ደቂቃ በመክፈት ይሁን ካሳሁን ከመረብ ባሳረፋት ግብ መምራት ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጨዋታ የበላይነቷን በማስቀጠል በርካታ ሙከራዎችን እያደረጋች ጫና ፈጥራ በመጫወት በ10ኛው ደቂቃ ሙእተሲምቢላ ፋሲል በተሰራበት ጥፋት የተገኛውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ግሩም ግብ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ታዳጊዎቹ ተደጋጋሚ የሆነ የጅቡቲን የጎል ክልል በማንኳኳት በ22ኛው ደቂቃ ከመሃል ሜዳ ጀምሮ ባደረጉት ድንቅ ቅብብል ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ገብቶ በመስፍን መላ ሶስተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ማራኪና ተስፋን የሚያጭር እንቅስቃሴን ማስመልከት የቻሉት ወጣቶቹ ተስፈኞች 3 ለ 0 እየመሩ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴን ማሳየት የቻሉት ወጣቶች በ55ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን አራተኛ ጎል በኦዳ መሐሙድ አማካኝነት በማስቆጠር መሪነታቸውን አጠናክረው የማሸነፍ እድላቸውን ማስፋት ችለዋል፡፡ ተጨዋቹ ከመሃል ሜዳ የተላከለትን ኳስ በአየር ላይ አክርሮ በመምታት የጅቡቲውን ግብ ጠባቂ እግሮች አልፋ ከመረብ ልትገናኝ ችላለች፡፡ በሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ላራንጎ በ77 ደቂቃ ከመሃል ሜዳ የተሻማለትን ኳስ በአስገራሚ ሁኔታ በጭንቅላቱ በመግጨት ከመረብ በማሳረፍ የቡድኑን መሪነት ወደ 5 ጎሎች አሳድጓል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አሌክስ ዳሮ ከመስፍን መላ የተሻገረለትን ኳስ ብቻውን አግኝቶ የጎል መጠኑን ወደ 6 አድርሶታል፡፡ ማሸነፋቸውን እያረጋገጡ የመጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተስፈኞች በመስፍን መላ በ88ኛው ደቂቃ ለቡድኑ ሰባተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ሰዓት አብነት ማርቆስ ስምንተኛዋንና የማሳረጊያዋን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ ታዳጊዎች ብሔራዊ ቡድን 8 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጅቡቲዎችን ከመሸነፍ ያልታደገቻቸውን አንድ ግብ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ አብዲ ሳዲቅ አስቆጥሯል። ኢትዮጵያ ታዳጊዎች ብሔራዊ ቡድን በሙሉ የጨዋታ ሰዓት በሁሉም የእግር ኳስ መለኪያዎች የተሻለና ተስፋን የሚያጭር እንቅስቃሴን በማድረግ ጨዋታውን መጨረስ ችሏል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ነገ ከጠንካራዋ ዩጋንዳ ጋር በማድረግ የሚያጠናቀቅ ሲሆን ጠንከር ያለ ፈተና እንደሚገጥመውም ይጠበቃል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታቸው ጅቡቲን ገጥመው 15 ለምንም ያሸነፉት ኡጋንዳዎች በሁለተኛ ጨዋታቸው ደቡብ ሱዳንን 3 ለ ምንም ረተው ምድቡን በበላይነት እየመሩ ኢትዮጵያን ይገጥማሉ፡፡
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከዩጋንዳ፣ ጅቡቲና ከደቡብ ሱዳን ተደልድላ ውድድሯን እያደረገች ሲሆን ታንዛኒያ ዛንዚባር፣ ሶማሊያ እና ሩዋንዳ በምድብ ሁለት ተደልድለው ውድድራቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡ ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2019 ዓ.ም በኤርትራ መዲና አስመራ ተካሂዶ የውድድሩ የመጀመሪያ አሸናፊ የአሁኗ አስተናጋጅ ሀገር ዩጋንዳ ነበረች፡፡ ውድድሩ እስከ መጨረሻ እጅግ ከፍተኛ ፉክክርን እንደሚያስተናግድ ሲጠበቅ በሚቀጥለው ዓመት በዞን ደረጃ ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የሚለዩበት እንደሚሆን የውድድሩ አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም