ሀገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለማሳደግ ብሎም አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን (Free Trade Zones) ማቋቋም ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣና ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና›› (Special Economic Zones) የሚባሉት የንግድና ኢንቨስትመንት መከወኛ ስፍራዎች አካል ሲሆን፣ እሴት የሚጨምሩ የምርት፣ የሎጅስቲክስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል ተግባራትና አገልግሎቶች የሚከናወኑበት ቦታ ነው፡፡
በዚህ ስፍራ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ አስመጪና ላኪዎች ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት በቀጣናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀነባብሩበት እንዲሁም መልሰው ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡበት እንዲሁም ሂደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚቀርብበትም ነው፡፡ የተቀናጁ የፋይናንስና የምክር አገልግሎቶችም ይሰጥበታል፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ቀጣና የንግድ እንቅፋቶች የሌሉበት እንዲሁም ቀረጥና ግብር ያነሰበት የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳለጫ አካባቢ እንደሆነም ይገለፃል፡፡ በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ሕጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ የላሉና አንፃራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ናቸው። እነዚህ አሰራሮች ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን የሥራ እድል፣ ለሀገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና ለዋጋ ግሽበት መቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም ላይ ከአምስት ሺ በላይ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች አሉ። በርካታ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ያሏቸው ሲሆን፣ ለእዚህም የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት ሀገራትም ይህን የነፃ ንግድ ቀጣና አሰራር ተግባራዊ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጣናን እስካሁን ድረስ ባለማቋቋሟ ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለጽ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ነፃ የንግድ ቀጣናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው፡፡
ስለሆነም ነፃ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው፣ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ይታወሳል። በድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉት ተግባራት ሲከናወኑ ከቆዩ በኋላ ሥራ እንዲጀምር የተደረገው ነፃ የንግድ ቀጠናው፤ ለበርካታ ዓመታት ከነፃ የንግድ ቀጠና አሰራር ርቆ ለኖረው የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠናው በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አራት ሺ ሄክታር መሬት የማስፋፈፊያ ቦታ ተዘጋጅቶለታል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴና የሎጂስቲክስ ፍላጎት መጨመርን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አካል ነው›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋንና አካባቢውን የሚያነቃቃ፣ ለነዋሪዎች የሥራ እድል የሚፈጥር እና የወጪና ገቢ ንግድን የሚያሳልጥ ከመሆኑም ባሻገር ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እና በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡
‹‹ነጻ የንግድ ቀጠናው የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ከማስቻሉ በተጨማሪ ተኪ ምርቶች እንዲመረቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሀገሪቱ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል›› ይላሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሰማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶችን በፍጥነት ለማስተናገድ እየሰራ እንደሚገኝም ይናገራሉ፡፡
አቶ አክሊሉ እንደሚያብራሩት፣ ነፃ የንግድ ቀጣናው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለደንበኞች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን አሟልቷል፤ የአሰራር ሥርዓቶችን ዘርግቷል፡፡ የባለሃብት ምልመላ መስፈርትና የአገልግሎት ዋጋ ተመን አዘጋጅቷል፡፡ የተለያዩ ሀገራት በነፃ የንግድ ቀጣና አስተዳደር ዘርፍ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ተቀምሯል፡፡
በዚህ ረገድ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የቱርክና የጅቡቲ ተሞክሮ ተጠንቶ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ባለበት ሥነ ምህዳራዊና ፖለቲካዊ አስተዳደር ውስጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ያስችላሉ ተብለው የታመነባቸው አሰራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናው ለአምራቾች፣ ለአስመጪዎች፣ ለላኪዎችና ለሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አመቺ እንዲሆን ተደርጎ ከመልማቱ በተጨማሪ ከዋና ዋና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት አማራጮች በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
እስካሁን ድረስ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ከወጪ ንግድና ከተኪ ምርቶች ምርት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል፡፡ ቀጣናው በሚቀጥሉት ወራት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናው በመሠረተ ልማት አቅርቦት ረገድ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የፍሳሽ ማጣሪያ፣ ለቢሮና ለንግድ የሚሆኑ ሕንፃዎች፣ ለማምረቻና ማከማቻ የሚያገለግሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖች፣ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት 48 ሄክታር የለማ መሬት፣ የምርት ማሳያ ቦታዎችን አካትቶ በዓለም አቀፍ ልምድ መሠረት ሥራ እንዲጀምር ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም በበኩላቸው፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው በይፋ ከተመረቀ በኋላ ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በነፃ ንግድ ቀጠናው ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደ አቶ ካሚል ገለፃ፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው ከተመረቀ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ ቀጠናው ገብተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉትን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል መዋቅር የመዘርጋት፣ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ በመቀመር የታሪፍ መመሪያ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባለሀብቶች መመልመያ መስፈርት እና የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን ጨምሮ የፋይናንስ መመሪያዎችን የማዘጋጀት ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናው በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ ብዙ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች ያላነሰ የመሠረተ ልማት አቅርቦት አለው፡፡ በዚህም ምክንያት በቀጠናው ውስጥ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በ2015 የበጀት ዓመት የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁና ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ሲቀመሩ ቆይቷል፡፡ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች ተሰርተዋል›› ይላሉ። ነፃ የንግድ ቀጣናው ከምርት ተግባር በተጨማሪ በንግድና በሎጂስቲክስ ዘርፎች የሚሰሩ ተቋማት እንደሚሰማሩበት የሚገልፁት አቶ ካሚል፣ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በነፃ የንግድ ቀጣናው ከተመረቱ ምርቶች አምስት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ ነፃ የንግድ ቀጣናው በነፃ የንግድ ቀጣና የአሰራር ሥርዓት መሠረት ሥራ አልጀመረም። በዚህም ምክንያት በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ሥራቸውን እያከናወኑ ያሉት በቀደመው የኢንዱስትሪ ፓርክ አሰራር ሥርዓት መሠረት ነው፡፡
አቶ አክሊሉ እንደሚናገሩት፣ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ተፈራርመው ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መጽደቅን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል፡፡ የነፃ የንግድ ቀጣናው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባት የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ፣ የግብርና ግብዓቶችን አቅርቦት በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎትን በማሻሻል፣ የንግድና ሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ ረገድ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዋጁ በፍጥነት ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ጥረት እንደሚደረግ ያስረዳሉ፡፡
አቶ ካሚል በበኩላቸው በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቀው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ በንግድና በሎጂስቲክስ ዘርፎች የሚሰሩ ተቋማት በነፃ የንግድ ቀጣናው ሥራ እንዲጀምሩ እንደሚያስችላቸው ጠቅሰው፣ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁለቱ ዘርፎች የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት አቅም እንደሚፈጥር ይገልጻሉ። ‹‹በንግድና በሎጂስቲክስ ዘርፎች መሰማራት የሚፈልጉ በርካታ ባለሃብቶች ተመዝግበው እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ በንግድና በሎጂስቲክስ ዘርፎች እንደ ሀገር ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ አዋጁ ሲጸድቅ ባለሃብቶቹ ሥራ ስለሚጀምሩ ይህን ክፍተት ለማስተካከል ይረዳል፡፡ በግብዓት አቅርቦትና በምርት ሥራ ሂደት ብዙ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ፤ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋትም ያግዛል›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን፣ እቃቸውንና እውቀታቸውን ይዘው የሚመጡበት የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሆነ የሚገልፁት የ‹‹ኢፒክ ሶሉሽን›› ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀቢብ አብዱልሃሚድ፣ የነፃ የንግድ ቀጠና አሰራርና ትግበራ ገበያን በማረጋጋትና እሴት በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይናገራሉ፡፡ አሰራሩ ለምርት፣ ለግብይትና ለሎጂስቲክስ ሥራዎች የሚያስፈልገውን ጊዜ በማሳጠር ውጤታማ የንግድ እንቅስቃሴን እውን እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ የሕግ ማዕቀፎችን ዝግጅት በማጠናቀቅ ነፃ ንግድ ቀጣናውን በሙሉ አቅሙ ሥራ ማስጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሙሉጌታ ግርማ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት በጥንቃቄ ሊከናወን እንደሚገባ ይመክራሉ። ‹‹የነፃ የንግድ ቀጠናዎች ትግበራ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ ሂደት ውስጥ አስቻይ ሁኔታዎችንና አማራጮችን በተረጋጋ ሁኔታ መገምገምና መመልከት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፎች በበቂ ጥናት ላይ ተመስርተው ካልተዘጋጁ ለሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ተናግረው፣ እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ በጥልቅ ምልከታ ላይ የተመረኮዘ የአሰራር መመሪዎች ዝግጅት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም