ኢትዮጵያ ከ80 በላይ በሚሆኑ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የተገነባች፤ ይህም ድምቀት ሆኗት ለበርካታ ዓመታት የኖረች አገር ነች፡፡ ይህ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ ከመሆን ይልቅ ውበት፤ የጥል ግድግዳ ከመገንባት ይልቅ የመቀራረብ ድልድይ ሆኖ አንዱ ጋር ያለውን ሌላው እየተዋሰ ፤ በአንዱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት ሌላው እየተጠቀመ እንዲሁም ባህልና እሴቱን እየተጋራ ህብረተሰቡ ዘመናትን በአብሮነት እንዲያሳልፍ አድርጓል፡፡
ብዝሃነት የኢትዮጵያ ድምቀት ነው፡፡ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ባዳበሩት የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የአኗኗር ባህላቸው እንዲሁም የቤት አሠራር ጥበባቸው ልዩ ልዩ ህብር ይፈጥራሉ፡፡ ይህም ዜጎች በስስት እንዲያዩት፤ የውጭ ጎብኚዎች በቀደመው ስልጣኔያችን በመደመም ባህር አቋርጠው እየመጡ ማንነታችንን እንዲገነዘቡና ለኢኮኖሚ ትሩፋት የሚሆን ገንዘብ እንዲያወጡ ያስገድዳል፡፡
ኢትዮጵያን የገነቡት ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነታቸው እንደተጠበቀ የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ኢትዮጵያን በጋራ ገንብተዋል፡፡ ይህ ብሄረሰባዊ ማንነታቸው እስከዛሬ ኢትዮጵዊነታቸውን አላደበዘዘውም፤ አልሸፈነውም፡፡ ይህም ዘወትር በሄዱበት ‹‹እኔ ኢትዮያዊ ነኝ›› እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በጋራ ያቆሙትና ያኖሩት ቅርስና የገነቡት ታሪክ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ስላልሆነ በአደባባይ ይደምቁበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን የደመቁበት ህብረ ብሄርነት ጉልበትም ኃይልም ነው፡፡ አገሪቱን በተደጋጋሚ ለመውረር የሞከሩ ጠላቶች እንደ አንድ በተሰለፉ የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ተመክተውና አፍረው መመለሳቸውን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ይህንን አኩሪ ታሪክ መላው ህዝብ እንዲሁም መሪዎቻችን በኩራት እንደ አብነት ያነሱታል፡፡
ለእዚህም ነው ከሰባት ወር በፊት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩን የተረከቡት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ‹‹አማራው በካራ ማራ ለሀገሩ ሉአላዊነት ተሰውቶ የካራ ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል፡፡ ሱማሌው፣ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ ፣ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል›› በማለት ምስክርነት የሰጡት፡፡
እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ያን የመከራ ጊዜ በህብረት አልፈናል፡፡ ባህር አቋርጦ ድንበር ለመግፋት የሞከረውን ጠላት በጋራ መክተናል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩት ብሄር ተኮር ጥቃቶችና ትንኮሳዎች የቀደመ ማንነታችንን ፈትሸን ወደ ቀልባችን መመለስ አለብን የሚያስብል ነው፡፡ እኛን ኢትዮጵውያንን ካሳለፍነው የአብሮነት ታሪክ ጋር ሲመዘኑም ሚዛናቸው እጅግ የሚቀል በመሆኑ ሊገቱ ይገባቸዋል፡፡
ብዝሃነት ላወቀበት ጉልበት ለዘነጋው ደግሞ የመከፋፈያ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከአሁን አንድ አድርጎ ያዘለቀን ልዩነታችንን አቻችለን የጋራ ጠላታችንን በጋራ መመከታችን ነው፡፡ አሁንም በብሔር ብሔረሰቦች ስም እየተነገደ ለመከፋፈል የሚደረገውን ሴራ ነቅቶ መጠበቅ ብሎም መግታት የሁሉም ዜጋ ተግባር መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዘመናት ሂደት መስተጋብር ፈጥረው በአብሮነት ኀዘንና ደስታን ያሳለፉ በመሆናቸው ብዝሃነትን ባለማወቅ ለልዩነትና ለመከፋፈል እንዳዋሉት አገራት መሆን አይገባም፡፡ ከእነርሱም ስህተት መማር ብልህነት ይሆናል፡፡
ዘንድሮ ለአስራ ሦስተኛ ጊዜ የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ‹‹በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ መልዕክት ሲከበርም ህብረ ብሄራዊነታችን ለአንድነታችን ጉልበት መሆኑን በመገንዘብ እንጠብቀው፤ እናስቀጥለው!