የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግና ከፍተኛ ሊግ ውድድሮች የሚጀመሩበትን ቀንና ቦታን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ባካሄደው የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በሐዋሳ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር በባቱ ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚመራቸው የእነዚህ ውድድሮች የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 26- 2016 ዓ.ም ተደርጓል። የዕጣ ማውጣት ሂደቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የውድድር ዳይሬክቶሬት፣ የሴቶች ልማትና ውድድር ኮሚቴ አባላት እና የሴቶች ፕሪሚየር ሊግና ከፍተኛ ሊግ ክለብ ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል። የ2015 ዓ.ም የውድድር ሪፖርቶች እና የ2016 ዓ.ም የውድድር ደንብ ቀርቦም ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቋል። በመድረኩም ለሴቶች እግር ኳስ ትኩረት በመስጠት መሠራት እንደሚኖርበትና በክለብ ፈቃድ አሰጣጥ እና የፊዚዮቴራፒስት የሕክምና ጉዳይ ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
በወጣው መርሐግብር መሠረት የዘንድሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከኅዳር 16 -2016 ዓ.ም ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ እንደሚከናወን ተገልጿል። 14 ክለቦችን የሚያፎካክረው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያ ሳምንት የሚደረጉት ጨዋታዎችም ይፋ ተደርገዋል። የአምናው የሊጉ ቻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን በማድረግ የውድድር ዓመቱን የሚጀመር ሲሆን በሌሎች የሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ቦሌ ክፍለ ከተማ ከመቻል፣ ልደታ ክፍለ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ፣ ይርጋጨፌ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀምበርቾ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዲስ አበባ ከተማ ከሲዳማ ቡና በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ሊጉ ጅማሬውን የሚያደርግ ይሆናል።
የሴቶች የከፍተኛ ሊግ ውድድር ደግሞ ከኅዳር 22 ጀምሮ በባቱ ከተማ እንደሚደረግ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የክለብ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት በተደረገው የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ወቅት ተገልጿል። በዚህም በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች 11 የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በመኖራቸው በመጀመሪያ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ሲካሄዱ አንድ ክለብ ጨዋታን የማያደርግ ይሆናል። በወጣው
መርሐ ግብር መሠረትም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ሸገር ከተማ ከለሚ ኩራ፣ ባህርዳር ከተማ ከአምቦ ጎል (ፊፋ) እና ሞጆ ከተማ ከፋሲል ከነማ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚያርፍ ቡድን ይሆናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በቀጣይ ለሴቶች እግር ኳስ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል። የተፎካካሪ ክለቦች ቁጥር ቢጨምር በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ኢትዮጵያ ውጤታማ መሆን እንደምትችልም ተናግረዋል። ለዚህም ክለቦች ትኩረት ሰጥተው በመሥራትና የተፎካካሪ
ክለቦችን ቁጥር በመጨመር የሴቶችን እግር ኳስ አንድ እርምጃ ወደ ፊት በማምጣት የፌዴሬሽኑን ጥረት መደገፍ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። ፌዴሬሽኑ የወንድ ክለብ ያላቸውን ክለቦች ተከታትሎ የሴት ክለብ እንዲመሰርቱ የማድረግ ክፍተቱን በማስተካከል ሁሉም ክለቦች የሴቶች እግር ኳስ ክለብ እንዲያቋቁሙ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ለዚህም የክለብ ፍቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ከ15 ዓመት በፊት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፊፋ ሥልጠና የተሰጠ ቢሆንም የተሻሻለ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ አዲስ ባለሙያ ቀጥሮ ግብጽና ታንዛኒያ በመላክ ሥልጠና እንደሰጠና የኢትዮጵያ ክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን በማዘጋጀት ለክለቦች የግንዛቤ ሥልጠና ከተሰጠ በኋላ መነቃቃት ተፈጥሯል። የክለብ ፍቃድ ሕጉ የሚለውን፣ መሬት ላይ ያለውን እና መጨመር ያለበትን ዓለም አቀፉን የሴቶች ልማት ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በመቀየር መዘጋጀቱን እና ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ ለክለቦች ይፋ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ሁሉም ክለቦች የሴት ፊዚዮቴራፒስት መቅጠር እንደሚገባቸውና ፌዴሬሽኑ በዘንድሮ ዓመት ይህንን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የጨዋታዎቹን የቀጥታ ስርጭትን በተመለከተም በተሰጠ ማብራሪያም ስርጭት መኖሩ ጥቅሙ የሁሉም ቢሆንም ሥራውን ገብቶ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ተቋማት አናሳ መሆኑና ፍላጎት አለማሳየታቸው ለፌዴሬሽኑ ፈተና እንደሆነበት ተጠቁሟል። ያምሆኖ የተመረጡ ጨዋታዎችን ከፌዴሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በቀጥታ የሚተላለፉበትን ሁኔታዎች ለመፍጠር ጥረት እንደሚደረግ ታውቋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016