በደርግ ጊዜ ነው አሉ። አንድ የደርግ ካድሬ ወደ ገጠር ዘምቶ ገበሬውን ሰብስቦ ስለአብዮቱና መሰል ጉዳዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጠ ነው። በንግግሮቹ ውስጥ ‹‹ሌኒን እንዳለው፣ ስታሊን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳለው….›› እያለ በወቅቱ ከደርግ ካድሬ አፍ የማይጠፉ አብዮተኞችን ይዘረዝራል። እነዚህ የተባሉት ሰዎች ምን እንደሆኑ የማያውቁት አንድ የገጠር አባት ተገርመው ‹‹እኔ እምለው? ይሄ አባ እንዳለው የሚባል ሰውዬ ስንት ልጆች ነው ያሉት?›› አሉ ይባላል። በገጠር አካባቢ እንዳለው የሚባል የሰው ስም ስላለ ካድሬው ‹‹እገሌ እንዳለው›› ሲል የተጠሩት ሰዎች አባታቸው እንዳለው ሆኖ ነው የመሰላቸው።
ከዚሁ ጋር የተገናኘ አንድ ቀልድ ልጨምር። ይህን ቀልድ የሰማሁት ከስድስት ዓመት በፊት ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር እየተጓዝኩ ነበር። ደጀንን ይሁን ደብረ ማርቆስን እንዳለፍን አንድ ፖሊስ እንድንተባበረው ጠየቀን። መኪናችን ትርፍ ወንበሮች ስላሉት ገባ እና አብሮን መጓዝ ጀመረ። እንደሚታወቀው የመስክ ጉዞ ላይ ቀልዶች ይበዛሉ፣ ሳቅ ጨዋታ ይደምቃል። ብዙ ስንሳሳቅ ከቆየን በኋላ ፖሊሱን ‹‹እባክህ አንተም ተጫወት›› ዓይነት ጉትጎታ ተጀመረ። ‹‹ኧረ እኔ ምንም አላውቅም›› ቢልም እንደምንም ገፋፋነው። ምንም አላውቅም ብሎ የነገረን ቀልድ ግን እስከ ባህር ዳር ነበር ያሳቀን።
አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ እንደዚሁ ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ ይላካል። የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስቦ በል የተባለውን መልዕክት ያስተላልፋል። ሲናገር ታዲያ እንደተለመደው እሱም የወቅቱ መንግሥት ይጠቀማቸው የነበሩ የካድሬ ቃላትን ይደጋግማል። እነዚያን ቃላት ያልተረዱ ተሰብሳቢዎች ልቅም አድርገው በማውጣት ‹‹ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? ይሄኛውስ ምን ማለት ነው?›› ይሉታል። እነዚያን ቃላት ማብራራት ያልቻለው ካድሬ ‹‹እኔ ምንም መቀየር አልችልም ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው›› አለ ብሎ የሰማውን ቀልድ ነገረን።
ቀልዶቹ በትክክል የተከሰቱ ሊሆንም ላይሆኑም ይችላሉ። የተፈጠሩ ቢሆኑ እንኳን ቀልዶቹ ለምን ተፈጠሩ ነው ዋናው ጥያቄ። ቀልዶቹ የተፈጠሩበት ምክንያት ከሚያጋጥመው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ነው። ብዙዎቻችን በተግባር እንደታዘብነው ለገጠሩ ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጡ የመንግሥት ተወካዮች የአካባቢውን ዓውድ ባላገናዘበ መንገድ ነው። በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚዘወተሩ የፖለቲካ ቃላትን በመደጋገም ነው። መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሄዱት አካላት ደግሞ የእንግሊዝኛ ቃላትን በመደጋገም ነው።
እዚህ ላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ በአካባቢያችን የሰማሁትን ምሳሌ ላድርግ። በወቅቱ (1990ዎቹ) ሰዎች ለሰዎች (ሜሽን ፎር ሜሽን) የሚባል ድርጅት በየአካባቢው የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጥ ነበር። ታዲያ ይህን የሚያስተባብሩላቸው በየቀበሌው ያሉ ሚሊሻዎች ናቸው። አንደኛው ሚሊሻ ‹‹እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ስላለ›› በሚል ‹‹ኢንፎርሜሽን›› ተናገር ተብሏል። ሚሊሻው የትምህርት ዝግጅት ስለሌለው ለእንግሊዝኛ ቃላት በጣም ሩቅ ነው። በየመንደሩ እየዞረ ‹‹ፉርሽኝ አለ›› እያለ ነበር የሚናገር። የአካባቢው ሰዎችም ‹‹ፉርሽኝ ምን ይሆን?›› በማለት የሆነ የሚታደል ነገር በመጓጓት ነበር የሄዱት። እኔም በወቅቱ ‹‹ለምን መረጃ ብለው አይነግሩትም?›› እያልኩ ስናደድ ነበር።
ቀልዶቹም ሆኑ እውነተኛ ገጠመኞች ገጠር ላይ የሆኑበት ምክንያት የከተሜው ነዋሪ ለእንግሊዝኛ ቃላት ቀረብ ይላል በሚል ነው። የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽነት ስላለው በተደጋጋሚ የመስማት ዕድሉ የተሻለ ይሆናል በሚል ነው። የገጠሩ ማህበረሰብ ግን የማንም የውጭ ድሪቶ የማያገኘው ቱባ የሆነ የራሱ ባህልና ቋንቋ ያለው ነው። በራሱ ቋንቋ መግባባት ብቻ ሳይሆን ቅኔ የሚቀኝ ነው። በራሱ ቋንቋ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ተረቶችና እንቆቅልሾች ያሉት ነው። ጥልቅ ፍልስፍና ያላቸው ወጎች ያሉት ነው።
ይህን ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሄዱ ሰዎች ግን የአካባቢው ማህበረሰብ በሚገባው ቋንቋ አይደለም የሚያስረዱት፤ ራሳቸውም ባልገባቸው የውጭ ቃላት ነው። ሲባል የሰሙትን ቃል እዚያ ሄደው ይለማመዳሉ። እነዚያ የሚናገሯቸው የእንግሊዝኛ ቃላት ግልጽ የሆነ የአማርኛ አቻ ያላቸው ናቸው። ምንም እንኳን አንዳንድ የቴክኖሎጂ ቃላት ቢኖሩም ቢያንስ ግልጽ የሆነ ሀገርኛ ትርጉም ያላቸውን ቃላት ግን በአካባቢው ቋንቋ መናገር ትዝ አይላቸውም።
የሰው ልጅ ደመ ነፍሳዊ አይደለም። ከፍጥረታት ሁሉ ከሚለይባቸው ነገሮች አንዱ በቋንቋ የሚግባባ መሆኑ ነው። ቋንቋ መግባቢያ ነው። የሚያግባባ ቋንቋ ደግሞ የጋራ ቋንቋ ይባላል። ለምሳሌ፤ ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ይህን ጽሑፍ የሚያነበው አማርኛ ማንበብ የሚችል ሰው ነው። ስለዚህ ይህ ቋንቋ የእኔ የፀሐፊው እና የዚህ ጽሑፍ አንባቢ ሰው የጋራ ቋንቋ ነው ማለት ነው። ተግባባን ማለት ነው። ምንም አማርኛ የማይችል አንድ ቻይናዊ ይህን ጽሑፍ ቢያየው ሊያነበው አይችልም፤ ስለዚህ ለዚህ ሰውዬ የጋራችን አልሆነም ማለት ነው። ይሄ ሰውዬ እኔን ግንዛቤ ሊያስጨብጠኝ ወይም እኔ ላስጨብጠው አንችልም ማለት ነው። እኔና እርሱ ልንግባባ የምንችለው የጋራ ሊሆን በሚችለው በእንግሊዝኛ ይሆናል ማለት ነው።
እነዚህ ግንዛቤ ሊያስጨብጡ የሚሄዱ ሰዎች የመረጡት ቋንቋ አማርኛ ነው እንበል። ሊያስተምሩ የሚሄዱትም የአማርኛ ተናጋሪ ባለበት አካባቢ ነው። የሚገርመው ሊያስተምር የሚሄደውም የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት እንደማንኛውም ሰው በትምህርት ያገኛት የእንግሊዝኛ ዕውቀት ትኖራለች።
አንድን ሃሳብ በሰዎች ላይ ለማስረጽ በሚገባቸው ቋንቋ መሆን አለበት፤ እንዲያውም እንኳን ቋንቋው አቀራረቡ ራሱ ሳቢ መሆን አለበት ነው የሚባለው። እየሆነ ያለው ግን ጭራሽ ቃላቱ ራሱ የሚናገረው ሰው የማያውቃቸው ናቸው። መሆን የነበረበት ግን ቋንቋውን እነርሱ የሚያውቁት ማድረግ ብቻ ሳይሆን አቀራረቡ ራሱ በእነርሱ ዓውድ ነው። ምሳሌ ሲሰጥ በአካባቢያቸው የሚያውቁት ነገር መሆን አለበት። የሚነገሩት ቃላት አማርኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሕዝብ የሚያውቀው አማርኛ ነው ወይ የሚለው ታሳቢ መደረግ አለበት።
በገጠር አካባቢ የሚሰማሩ የግብርና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እና በተለያዩ ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚላኩ ባለሙያዎች መጀመሪያ ራሳቸው መሰልጠን አለባቸው። አወዛጋቢና አሻሚ ትርጉም ያለው ያልተለመደ ቃል ባይጠቀሙ፤ ሲጠየቁ ሊያብራሩት የሚችሉትን ቃላት ነው መናገር ያለባቸው።
ቃላት መረጣ ብቻ ሳይሆን አቀራረብ ራሱ በተቻለ መጠን ለአካባቢው ሕዝብ ቢሆን ዓውድ ቢሆን። ከባለሥልጣናት እና ከምሁራን ጋር እንደሚደረገው ውይይት መደበኛ እና ፕሮቶኮሉን የጠበቀ ከሚሆን ይልቅ እንደ ደንባቸው ኢመደበኛ እና ቀለል ያለ ቢሆን። ምክንያቱም ነፃ ሆነው ሃሳባቸውን ሊናገሩ ይችላሉ። ይህ እንኳን ባይቻል፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጥ ትምህርቱ የሚሰጣቸው ሰዎች በሚገባቸው አገላለጽ ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016