ሰፋፊዎቹ የኒውዮርክ ጎዳናዎች የፕላቲኒየም ደረጃ ካላቸው ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች በዓመቱ የመጨረሻው ሆነውን ሩጫ አስተናግደዋል፡፡ ከ50ሺ በላይ ሰዎች ተሳታፊ በሆኑበት ሩጫ ላይም ከአትሌቶች ባለፈ በርካታ የሙዚቃ፣ የፊልም የቴሊቪዥን ዝግጅት አቅራቢዎች እንዲሁም በመላው ዓለም ዝነኛ ሆኑ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ዘንድሮ ለ52ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በሴቶች በኩል ደግሞ በቅርቡ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን የተቀላቀለችው ብርቱዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ልታጠናቅቅ ችላለች፡፡
በርካታ ምርጥ አትሌቶች ተሳታፊ በነበሩበት በዚህ የሩጫ ውድድር አሸናፊ የሚሆነውን አትሌት አስቀድሞ ለመለየት አዳጋች የነበረ ሲሆን፤ ፉክክሩ እንደተጠበቀውም በኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን አትሌቶች መካከል ነበር፡፡ የውድድሩ ጠንካራ መሆንም በኒውዮርክ ማራቶን ከዓመታት በኃላ ፈጣን ሰዓት እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ታምራት ቶላ፣ ጀማል ይመር እና ሹራ ቂታጣታ ፉክክሩን በማክረር ፈጣን ሰዓት እንዲመዘገብ አድርገዋል፡፡ ኬንያዊያኑን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ቀድመው በመውጣትም 21 ኪሎ ሜትሩን 1:02:45 በሆነ ሰዓት ማቋረጥ ችለዋል፡፡ ሩጫው 40ኛ ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርስም ተረጋግቶ ይሮጥ የነበረው የርቀቱ የቀድሞ የዓለም ቻምፒዮን ታምራት 2:04:58 በሆነ ሰዓት አሸናፊ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
እአአ በ2022ቱ የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሸናፊ የነበረው አትሌት ታምራት ቶላ በኒውዮርክ ማራቶን ቀድሞ ከነበረው ሰዓት በ2 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ የፈጠነ ሰዓት በመግባት የቦታው ክብረወሰን ባለቤት ሊሆን ችሏል፡፡ ከድሉ በኋላም ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ በኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ በመሆኔ ተደስቻለሁ፡፡ በዚህ ውድድር ስሳተፍ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፤ ለሁለት ጊዜያት አራተኛ ደረጃን በመያዝ ባጠናቅቅም አሁን አሸናፊ መሆኔ አስደስቶኛል›› ማለቱን የዓለም አትሌቲክስ አስነብቧል፡፡ በማራቶን ልምድ ካላቸው አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ታምራት በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ሜዳሊያ ሳይሳካለት ቀርተል፡፡ ከወራት በፊትም በለንደን ማራቶን ሶስተኛ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ኬንያዊው ተፎካካሪ አልበርት ኮሪር ከሁለት ደቂቃ መዘግየት በኋላ ውድድሩን በሁለተኛነት ሲያጠናቅቅ፤ ሌላኛው የአሸናፊነት ግምት ያገኘው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሹራ ቂጣታ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ አምና በዚህ ውድድር ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀው አትሌቱ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓትም 2:07:11 ነው። ሌላኛው ጠንካራ ተፎካሪ እና ከአሸናፊዎቹ መካከል ይሆናል በሚል የተጠበቀው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ጀማል ይመር በበኩሉ ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡
በዚህ ውድድር እጅግ አጓጊና ማን ያሸንፍ ይሆናል የሚለውን ለመገመት አዳጋች የነበረው በሴቶች ሴቶች መካከል የነበረው ፉክክር ነበር፡፡ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን አትሌቶችን ባካተተው በዚህ ውድድር የርቀቱን ግማሽ በአንድላይ በመሆን ያቋረጡት 14 አትሌቶች ነበሩ፡፡ ይኸውም የፉክክሩን መጠን የሚያሳይ ሲሆን፤ አትሌቶቹ ለአሸናፊነት የሚያደርጉትን ጉዞ የጀመሩት ከ35ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ነው፡፡ በዚህም በማራቶን እምብዛም የማትታወቀው ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቤሪ አሸናፊ መሆን ችላለች፡፡
ባለፈው ዓመት በዚሁ ሩጫ ተሳትፋ ስድስተኛ መውጣት የቻለችው አትሌቷ ዘንድሮ ስኬቷን ማጣጣም ችላለች፡፡ ባለፈው ዓመት የነበሯትን ስህተቶች አርማ መገኘቷ ለድል እንዳበቃት የገለጸችው አትሌቷ ‹‹በተለይ ግን ለተሰንበት ግደይን በማግኘቴ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ መም ላይ የተገናኘን ያህል ነው የተሰማኝ›› ስትልም አስተያየተን ሰጥታለች፡፡ በ2022 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለቱ አትሌቶች በ10ሺ ሜትር ያደረጉት እጅግ ከፍተኛ ፉክክር እና ጽናት ምልክቷ በሆነው አትሌት ለተሰንበት አሸናፊነት መጠናቀቁ በአትሌቲክስ ቡተሰቡ ዘንድ የሚታወስ ነው፡፡
ከመም ባለፈ በጎዳናም እጅግ ጠንካራ ፉክክር ያደረገችው ለተሰንበት ግደይ ከተቀናቃኟ ጋር የነበራት ትንቅንቅ መም ላይ የነበረውን ይመስል ነበር። አሸናፊነቱን ብትነጠቅም በጎዳና ላይ ውድድሮች ባልተለመደ ሁኔታ በስድስት ሰከንዶች ልዩነት 2:27:29 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው፡፡ አምና የመጀመሪያውን ማራቶን ቫሌንሺያ ላይ በመሮጥ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው አትሌቷ፤ በርቀቱ ያላትን ተስፋ አሳይታለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016