ፌዴራል ፖሊስና ኦሮሚያ ፖሊስ የ10ኛው የጎዳና ላይ ውድድር አሸናፊ ሆኑ

10ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በትናንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ፣ ፌዴራል ፖሊስና ኦሮሚያ ፖሊስ አጠቃላይ አሸናፊዎች ሆነዋል። ከፍተኛ ፉክክር ባስተናገደው ውድድር በወንዶች ፌዴራል ፖሊስና በሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ የቡድን አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።

12 አትሌቶችን ያሰለፈው ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች 31 ነጥቦችን በመሰብሰብ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን በሴቶች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ፈጽሟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክና ኦሮሚያ ክልል በ35 እና 44 ነጥቦች ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የብርና የነሐስ ሜዳለያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል። 24 አትሌቶችን ያሰለፈው ኦሮሚያ ፖሊስ በበኩሉ በሴቶች 21 ነጥቦችን ሰብስቦ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫና የወርቅ ሜዳለያ ተሸላሚ በመሆን አጠናቋል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ በ61 እና መቻል በ65 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈፅመዋል።

በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ከፍተኛ ፉክክር የታየ ሲሆን፣ አንዷለም በላይ ከፌዴራል ፖሊስ ባለ ድል ሊሆን ችሏል። አትሌቱ በ1:31’33” ሰዓት ውድድሩን ያተናቀቀ ሲሆን፣ ቀዳሚ ለመሆን ከመቻል፣ ከኢትዮ ኤሌክትሪክና ከንግድ ባንክ አትሌቶች ብርቱ ፉክክር ገጥሞት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከ25 ኪሎ ሜትር ጀምሮ ከተፎካካሪዎቹ ተነጥሎ ፍጥነቱን በመጨመር የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቋል። 2ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሰቦቃ ንጉሴ ከኦሮሚያ ክልል በ1:32’11 ሰዓት በመግባት የብር ሜዳለያ ተሸላሚ ሲሆን ክብሮም ደስታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ1:32’15” ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያውን ወስዷል።

ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ ከፍተኛ ፉክክር ባስተናገደው የሴቶች ውድድር ፍቅርተ ወረታው ከመቻል ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ ባለ ድሏ አትሌት ከ20 ኪሎ ሜትር በኋላ ብቻዋን በመሮጥ 10 ኪሎ ሜትሩን በድንቅ ብቃት ጨርሳለች። በዚህም ከተፎካካሪዎቿ በ400 ሜትር ርቀት ቀዳሚና የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳለያ ተሸላሚ ሆናለች፡ ፡ አትሌቷ የ30 ኪሎ ሜትሩን ውድድር ለመጨረስ 1:45’30 የሆነ ሰዓት አስፈልጓታል፡፡ ጋዲሴ ሙሉ ከኦሮሚያ ፖሊስ በ1:46”27 ርቀቱን በማጠናቀቅ 2ኛ ሆና የብር ሜዳሊያውን አጥልቃለች፡፡ የኔነሽ ጥላሁን ከኦሮሚያ ክልል በ1:46’28 ሰዓት በመግባት 3ኛ ሆና ውድድሯን በመጨረስ የነሐስ ሜዳለያ ባለቤት ሆናለች።

በወንዶች ፉክክሩን በበላይነት የፈፀመው የፌዴራል ፖሊሱ አትሌት አንዷለም በላይ በውድድሩ ያስተናገደው ፉክክር ከባድ እንደሆነና በቡድን ሥራ ጥሩ ውጤት እንደተመዘገበ ተናግሯል። ሲዘጋጅ የነበረው በውጭ ሀገር ለሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች በመሆኑም በውድድሩ ውጤታማ እንዲሆን እገዛን እንዳደረገለት ከውድድሩ በኋላ ለአዲስ ዘመን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ የውድድሩ ቦታም ሞቃት ከመሆኑ በቀር እሱና የቡድን ጓደኞቹ ዝግጅታቸውን ካደረጉበት ስፍራ የሚቀራረብና ምቹ እንደነበረ ገልጿል። አክሎም በውድድሩ የታየው መተጋገዝና የቡድን ሥራው በሌሎች ውድድሮች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል።

የሴቶች ውድድር አሸናፊዋ የመቻል አትሌት ፍቅርተ ወረታ በበኩሏ፣ ውድድሩ ጥሩ እንደሆነና ያደረገችው ዝግጅት ለድል እንዳበቃት ጠቁማለች። ባደረገችው ጠንካራ ዝግጅትም እንደምታሸነፍ እርግጠኛ እንደነበረች ተናግራለች። ለዚህም አሠልጠኟ በደንብ እንዳዘጋጃትና ከፍተኛውን ትንቅንቅ እንደምታሸንፍ ነግሯት ወደ ውድድሩ እንደገባች ገልፃለች፡፡

ለውድድሩ አሸናፊ አትሌቶች እንደየደረጃቸው ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ላሸነፉ አትሌቶች 40 ሺ ብር በሽልማት መልክ ተበርክቷል። 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ለፈጸሙ አትሌቶች 20ሺ ብር የተበረከተ ሲሆን 3ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁት አትሌቶች ደግሞ የ18 ሺብር ሽልማት ተሰጥቷል። ሽልማቱ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁ አትሌቶችም እንደየ ደረጃቸው ከ16 ሺ እስከ 8 ሺ ብር ሽልማት ተሰጥቷል። በተጨማሪም አንጋፋ አትሌቶችም ከስድስት ሺ ብር ጀምሮ እስከ እስከ 5 መቶ ብር ሊበረከትላቸው ችሏል። ፌዴሬሽኑ ለሽልማት በአጠቃላይ 318 ሺ ብር ወጪ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2016 ዓ.ም ከሚያካሂዳቸው የውድድር ዓይነቶች አንዱና የመጀመሪያው የሆነው የ30 ኪ.ሜ የጎዳና ውድድር ኢትዮጵያን በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚወክሉ ውጤታማና ተፎካካሪ አትሌቶችን ለማፍራት ዓላማን አንግቦ የሚካሄድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከዘጠኝ ክለቦች፣ አራት ክልሎች፣ አንጋፋ አትሌቶችና የግል ተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። 322 ወንድና 108 ሴት አትሌቶች በአጠቃላይ 430 አትሌቶችም በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You