በሀገራችን ቆዳንና ጸጉርን ለመንከባከብ የሚያገለግሉ የተለያዩ የምርት ዓይነቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ከእነዚህ ምርቶች አብዛኞቹ በፋብሪካ የተቀነባበሩና ከውጭ ሀገር የሚገቡ ናቸው። ተጠቃሚዎችም እነዚህን ምርቶች ከገበያ ላይ ገዝተው ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በሀገር ውስጥ የሚመረት አማራጭ የመዋቢያ ምርት እምብዛም አለመኖሩ ነው፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ድርጅቶች ብቅ እያሉ ስለመሆናቸው ገበያዎችና አንዳንድ መድረኮች እየጠቆሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለቆዳና ለጸጉር እንክብካቤ የሚያገለግሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እያመረተ የሚገኘው ‹‹ጥላ›› የተሰኘው ድርጅት አንዱ ነው፡፡
ድርጅቱን ያገኘነው በአፍሪካ የፋሽን ሳምንት ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ወደዚህ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመታት ያህል አስቆጥሯል፡፡ የድርጅቱ ምርቶች 96 በመቶ ያህሉ ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒ) ከሆኑ ነገሮች የሚመረቱ መሆናቸውን የጥላ ብራንድ አምባሳደር ወጣት ዓለምፀሐይ ቤዛው ትናገራለች፡፡
ብራንድ አምባሳደሯ እንደምትለው፤ እነዚህ ምርቶች በሀገር ውስጥ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲዘጋጁ ይደረጋል፤ ምርቶቹም ለሀገር ውስጥ ገበያ ይቀርባሉ፤ ለውጭ ገበያም ይላካሉ፡፡
ድርጅቱ ብራንድ የሆኑ ተፈላጊ ምርቶችን ያመርታል፡፡ እስካሁን ድረስ ለቆዳና ለጸጉር ተብለው በሀገር ውስጥ የተሰሩ መዋቢያና መንከባከቢያ ምርቶች የተለመዱ አይደሉም ያለችው ወጣት ዓለምፀሐይ፣ ለዚህም ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን ለመጠቀም እንገደዳለን ትላለች፡፡ ከውጭ የሚገባው ምርት ደግሞ ነጮቹ ለእነሱ ቆዳ በሚሆን መልኩ የሚያመርቱት መሆኑን ጠቅሳ፣ ይህ ምርት ለኢትዮጵውያን ቆዳና ጸጉር ተስማሚ ላይሆን ይችላል ብላለች፡፡ ድርጅቱ በሀገር ውስጥ የሚያመርታቸው ምርቶች ግን ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካውያን ቆዳና ጸጉር እንደሚስማሙም ትገልጻለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ እነዚህን ምርቶች ለማምረት ድርጅቱ የሚጠቀምባቸው ጥሬ እቃዎች ሺያ ቅቤ፣ ካካዎ፣ ቅቤና ጥቁር አዝሙድ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ክሬም፣ ሻውር ጄል፣ የጸጉር ሻምፖ፣ የጸጉር ትሪትመንት (መንከባከቢያ) ኮንዲሽነር እና ቦዲ ሎሽን ይመርታሉ። በውስጣቸው ያለው ይዘትም ሺያ ቅቤ ክሬም ቫይታሚን ያለው ነው፡፡ የካካዎ ክሬም ምርት ደግሞ የካካዎ ቅቤና ጥቁር አዝሙድ ያለው ሲሆን፣ ሁለት ዓይነት ሆኖ አንዱ በዘይት አንደኛው ደግሞ በውሃ የሚሰራ ነው፡፡
የሻውር ጄሉ ከንጹህ ነጭ ማር ይመረታል፡፡ የጸጉር ሻምፖ ደግሞ ከአቡካዶ ዘይትና ከግሪስሊን የሚሰራ ሲሆን፣ የጸጉር ትሪትመንቱ (መንከባከቢያ) የአቡካዶ ዘይት ያለው ነው፡፡ ኮኮናት ዘይቱም እንዲሁ ንጹህና መቶ በመቶ የተጣራ ሲሆን፣ ለጸጉር፣ ሰውነት ማሳጅ ለማድረግና ለሁሉም ዓይነት አገልግሎት የሚውል ነው፡፡
ምርቶቹ ከሕጻን እስከ አዋቂ ለሁሉም ሰው ቆዳና ጸጉር ተስማሚ በሆነ መልኩ እንደሚዘጋጁ ብራንድ አምባሳደሯ ጠቁማ፤ ደረቅና ወዛም ለሚባሉ የቆዳ ዓይነቶች እንዲስማሙ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸውንም ገልጻለች፡፡ ምርቱን ለመግዛት የሚመጡ ሰዎች ለቆዳቸው የሚሰማማቸውን ዓይነት ምርት እንዲያገኙ ለማድረግም ይሰራል፡፡ ለዚህም በቅድሚያ የትኛው የቅባት ዓይነት ለቆዳቸው ይስማማል የሚለው ታይቶ በእጃቸው ላይ ሞክረው እንዲያዩ ከተደረገ በኋላ ለቆዳቸው የሚስማማቸውን ዓይነት ምርት እንደገዙ እንደሚደረግ ትናገራለች፡፡
ወጣት ዓለምፀሐይ እንደተናገረችው፤ ምርቶቹን በቅድሚያ በእጅ ላይ እንዲሞከሩ የሚደረግበት ዋንኛ ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ለእንደዚህ ዓይነት ምርቶች አለርጂክ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው፡፡ አንድ በእጁ ቆዳ ላይ ሞክሮ አለርጂክ ከሆነበት ወዲያውኑ ይታያል፡፡ ይህም ምርቱን እንዳይጠቀም ለማድረግ ይረዳል፡፡
እነዚህ ምርቶች ተፈጥሯዊ ስለሆኑ በሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት የለም፡፡ ለወንድ ወይም ለሴት ተብሎ የሚለዩ ሳይሆን ለሁሉም ሰው የሚሆኑ ምርቶች ናቸው፡፡
ምርቶቹን የተጠቀሙ ደንበኞች የሚሰጡት አስተያየት ለድርጅቱ ሥራ የሚያበረታታ ሆኖ መገኘቱንም ነው ብራንድ አምባሳደሯ ያመለከተችው። ‹‹ሰዎች ምርቶቹን ከተጠቀሙ በኋላ በቆዳቸውም ሆነ በጸጉራቸው ላይ ወዲያውኑ ለውጥ እንደሚያዩና ምርቶቹንም በጣም እንደሚወዷቸው ገልጻለች፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ምርታችንን መጠቀም እስኪጀምሩ እንጂ ከጀመሩ በኋላ ወደ ሌላ በፍጽም አይሄዱም። በጣም ስለሚሰማማቸው ያልተጠቀሙበትን ጊዜ ይቆጩበታል፡፡›› ስትል ታብራራለች፡፡
ብራንድ አምባሳደሯ እንደምትለው፤ ምርቶቹ የሁሉንም ሰው የመግዛትና የመጠቀም አቅምም ያማከሉ ናቸው፡፡ ሰዎች ምርቱን በእጃቸው ቆዳ ላይ ሞክረው በተደጋጋሚ ተቀብተው አይተውትና ወደውት እንዲገዙ ለማድረግ እንዲያስችልም በትንሽ መጠን የሚዘጋጁ ምርቶችም አሉ፡፡
‹‹በኛ የቆዳ ዓይነት ያልተሰሩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ብዙ ሺ ብሮችን አውጥተን እንገዛለን፤ ይህንን ሁሉ ብር አውጥተን ገዝተንም ብዙም የማንረካበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል›› የምትለው ብራንድ አምባሳደሯ፤ ከዚህ አንጻር የጥላ ምርቶች ዋጋቸው ተመጣጣኝ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡
‹‹በተለይ እንደዚህ ዓይነት የዓለም አቀፍ የፋሽን ኤግዚቢሽን ላይ ስንቀርብ ደግሞ ሱቅም ከሚሸጥበት ዋጋ በታች ቀንሰን እንሸጣለን፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መድረኩ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ሰዎች የሚገኙበት እንደመሆኑ መጠን የገበያ ትስስርን ማስፋት የሚቻልበት አጋጣሚ ስለሚፈጥር ነው ብላለች፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ኤግዚቢሽን የዋጋ መቀነስ ብቻ ሳይሆን ምርቶቻችንን ለሚገዙ (ሁለት ትላልቅ ተመሳሳይ ምርቶች የገዛ ሰው) ሌላ አንድ ምርት በስጦታ የሚያገኝበትን ሁኔታ ፈጥረናል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ስጦታዎችም አሉ›› ስትል አብራርታለች።
እሷ እንዳለችው፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ትልቅ ፋብሪካ አለው፤ 70 በመቶ ያህሉ ምርቶቹ ወደ ተለያዩ ሀገራት ይላካሉ፡፣ በተለይ በአፍሪካ ሀገራት ላይ የራሱን ኩባንያ በመክፈት ምርቶቹ እንዲሸጡ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
ምርቶቹ ጥራታቸውን የጠበቁና በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተፈጥሯዊ ነገሮች ተሰርተው ቀርበዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ነው የተመረቱት ሲባል የሀገር ውስጥ ምርት ጥራት የሌለውና ዋጋውም ቢሆን ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ይሆናል የምትለው ብራንድ አምባሳደሯ፤ መወደድ የነበረበት የሀገር ውስጥ ምርት መሆኑን ገልጻለች፡፡ ‹‹ለራሳችን ቆዳና የጸጉር ዓይነት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ ከተሰራ እኛ መምረጥ ያለብን ይህን ምርት ነው፡፡ እስካሁን ደንበኞቻችን ምርቶቹን ወደውታል፤ ያልሞከሩትም ሞክረው አይተው መውደድ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸውም ምርት ሊኮሩ ይገባል›› በማለት ምክረ ሀሳቧን ለግሳለች፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም