ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ለተለያዩ የግብርና ምርቶች በሚሆን የአየር ንብረትና ለም መሬት የታደለች ናት፡፡ በቡና መገኛነቷ ትታወቃለች፤ በቡና ምርቷም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች፡፡ እነዚህ ሁሉ በቡና ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዳላት ይመሰክራሉ።
ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ይታወቃል፡፡ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ሆኖም ነው የኖረው፤ ዛሬም ቡና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወሳኙ ሰብል ሆኖ ቀጥሏል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ በመሥራት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቡና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ እያሳደረ ያለውን አበርክቶ ከፍ ማድረግ እንዲቻል እንደ ሀገርም ቡና በሚለማባቸው ክልሎች ደግሞ እንደ ክልል በቡና ልማት ላይ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡
የቡና ልማትን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ክልሎች መካከልም አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ከሀገሪቱ የቡና ምርት አብዛኛው ይመረትበታል፡፡ በዛሬው የግብርና አምዳችንም በክልሉ የቡና ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ያለውን ሥራ ለማሳየት ከክልሉ ግብርና ቢሮ የቡናና ሻይ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አቦሴ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ የኦሮሚያ ክልል በተፈጥሮ የታደለና ለቡናም ሆነ ለሻይ ምርት ምቹ ሁኔታ አለው፡፡ ቡና በክልሉ በሰፊው የሚለማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል። አጠቃላይ የኦሮሚያ ክልል በተለይ ለቡና ልማት እጅግ ተስማሚ ኢኮሎጂ አለው፡፡
አርሶ አደሩ ቀደም ሲል ጀምሮ ማንም ሳይነገረውና ኤክስቴንሽኑ ሳይደግፈው ቡናን ሲያለማ እንደነበር አቶ ተስፋዬ አስታውሰው፤ የቡና ኤክስቴንሽን ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ የቡና ልማትና የገበያ አቅርቦቱ ከዓመት ዓመት እያደገና እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለማልማት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በክልሉ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል፡፡
ሁሉም የቡና ችግኞች በተለያዩ ምክንያቶች ምርት የሚሰጡ አለመሆናቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ ምርት የማይሰጥ መሆኑ ተረጋግጧል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ምርት የሚሰጠው መሬት በየዓመቱ እያደገ እንዲመጣ መሠራቱን ተከትሎ ለውጥ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ዋናው ምክንያቱ የተተከለ ቡና ምርት መስጠት የሚጀምረው ከአራትና አምስት ዓመታት በኋላ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ነው በቡና የተሸፈነ መሬት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምርት ወደ መስጠት የሚገባ በመሆኑ የቡና ምርት በየዓመቱ እያደገ የሚሄድ ነው ብለዋል፡፡
በ2015 የምርት ዘመን በኦሮሚያ ክልል 10 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ቡና መመረቱን ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ፤ በተያዘው 2016 በጀት ዓመት 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማምረት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ይህን ዕቅድ ለማሳካትም በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች የክትትል ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህም የቡና ምርት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በቀጣይም ምርትና ምርታማነቱ እያደገ የሚሄድ ይሆናል፡፡
በበጀት ዓመቱ በክልሉ ለማምረት የታቀደውን 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ቡና መሰብሰብ እንዲቻል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ በዋናነት ቡናው ደርሶ ሲሰበሰብ በጥራት መሰብሰብ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከክልሉ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ በዋናነትም በቡና ልማት ዙሪያ ያለውን ችግር በመለየት ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር ውይይት መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ቡናው ደርሶ በሚሰበሰብበት ወቅትም ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ በአሰባሰብ ሂደትም እንዲሁ ውይይቱን ወደ ዞን፣ ቀበሌና ወረዳ በማውረድ ቡናው ሲደርስ እንዴት መሰብሰብ እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ቡናው ከተሰበሰበ በኋላም እንዴት መድረቅ እንዳለበት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በዚህም በየጊዜው ለውጥ እየተመዘገበና የሚፈለገው የቡና ጥራትና ዕድገት እየመጣ ነው ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የቡና ምርትን ለማሳደግ በዋነኛነት ጥራቱን ለማስጠበቅና ቡና እንዳይባክን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋርም እንዲሁ በስፋት እየተሰራ ይገኛል። ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ የህብረት ሥራ ማህበራቱ አባሎቻቸውን ጨምረው በመሳተፍ ጥራቱን የጠበቀ ቡና እንዲመረትና ብክነት እንዳይፈጠር ቡናውን በጥራት ሰብስበው ለገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡
የቡና ምርት መጠንን ከፍ ለማድረግ ጥራቱ ላይ መሥራት አንዱና ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ጥሩ ቡና ከተመረተና በጥራት መሰብሰብ ከተቻለ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ የቡና ዋጋ ወደቀ ሲባል በጥራት የማምረትና የመሰብሰብ አሰራሩን ቀንሶ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እንደፈለገ ይሰበስባል፤ ትኩረት አድርጎ የማምረትና የመሰብሰብ ፍላጎቱም ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ቡናውን በጥራት ሰብስቦ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
በጥራት የተመረተና የተሰበሰበ ቡና ደግሞ ጥሩ ገበያ ያገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት። አርሶ አደሩ ላመረተው ቡና ጥሩ ዋጋ ሲያገኝ በቀጣይ የማምረትና በጥንቃቄ የመሰብሰብ ፍላጎቱ እንደሚጨምርም ገልጸዋል፡፡ በዚህ መልኩ እንዲሰራ የማበረታታት፣ የመደገፍና የመከታተል ሥራን አጠናክሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ ሌሎች የአመራር ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ ለአብነትም በማሳ እንክብካቤዎች ላይ አርሶ አደሩ በትክክል እንዲሰራ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ለምርትና ምርታማነት እንዲሁም ለቡና ጥራት እንደ ኦሮሚያ ክልል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራው ያረጁ ቡናዎችን መጎንደል መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ እንደ ኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው የሚገኙት የቡና ዛፎች ያረጁና ከ60 እስከ 70 ዓመት ዕድሜን ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ያረጃ ቡና ጥራት ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ምክንያት በምርትና ምርታማነት ላይም እንዲሁ በጣም የወረደ አፈጻጸም ነው የሚያሳየው፡፡ ስለዚህ የመጎንደል ሥራው በየዓመቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የቡና ጉንደላ ሥራ በክልሉ በየዓመቱ የሚከናወን ሥራ ቢሆንም፣ ተጎንድሎም ውጤታማ የማይሆን የቡና ተክል በመኖሩ በቦታው ላይ ሌላ የቡና ችግኝ እንዲተካ የሚደረግበት ሁኔታም አለ፡፡ ቡናን በየዓመቱ በመጎንደል ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በ136 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝን የቡና ተክል የመጎንደል ሥራ ተሰርቷል፤ ምርት የማይሰጡትን የመተካት ሥራም ተከናውኗል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ይህንንም ጊዜው ሲደርስና ቡናው ከተሰበሰበ በኋላ ለመሥራት የታቀደ ሲሆን፤ በዕቅዱ መሠረት ለመሥራትም የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን ተጠናቅቀዋል፡፡
ቡና ተተክሎ ከአራትና አምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ምርት እንደሚሰጥ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ የተጎነደለ ቡና ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ምርት እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት፡፡ ይህም አርሶ አደሩን እንደሚጠቅም ጠቅሰው፣ እዚህ ላይ በስፋት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ይህንንም አርሶ አደሩ በከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚተገብረው ገልጸው፣ በተለይም ባለፈው በጀት ዓመት አብዛኛው አርሶ አደር በስፋት የሄደበትና ከታቀደው በላይም የሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ችግሩን በሚገባ የተረዳው እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል፡፡ እንደ ኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ ያረጁ ቡናዎች እየተጎነደሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ከሚገኙ 290 ወረዳዎች መካከል 193 ወረዳዎች ቡና የሚያመርቱ ናቸው፡፡ ከ21 ዞኖች መካከል በ18 ዞኖች ቡና ይመረታል፡፡ ከአንዱ ዞን ሌላኛው ዞን በመጠን የሚበላለጥ ይሁን እንጂ በአብዛኛው በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ዞኖች ቡና ይመረታል፡፡ ከዚህ ቀደም ቡና የማይመረትባቸው እንደ ሸዋ ያሉ አካባቢዎች አሁን አሁን ቡና ማምረት ጀምረዋል፡፡
በቡና ልማት ቀደም ሲል ጀምሮ ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎች ስለመኖራቸው ያነሱት አቶ ተስፋዬ፤ ነባር ቡና አምራቾች በሀገሪቱ ምዕራብ አካባቢዎች በጅማ፣ በደሌ፣ በኢሉባቦር፣ በወለጋ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ቡና በስፋት እንደሚመረትና ከዓመት ዓመት የምርት መጠናቸውም እየጨመረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በምዕራብ አርሲ ነንሰቦ ወረዳም እንዲሁ በከፍተኛ መጠን ቡና እንደሚመረት ጠቁመው፣ በዚህ አካባቢ የሚመረተው ቡና በተለየ ሁኔታ በውጭ ገበያ ተፈላጊ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ ቡና በአብዛኛው በአርሶ አደር እንደሚለማ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ በኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ቡናን የሚያመርቱ ጥቂት ባለሃብቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ ከሚመረተው 95 በመቶ ያህሉ ቡና በኦሮሚያ ክልል በአርሶ አደር አማካኝነት እንደሚመረትም ጠቅሰዋል፡፡
የቡና ሻይ ባለሥልጣን በበኩሉ በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በቡና ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መሆኑን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከቡና ምርት ባለፈ በኤክስፖርት ግኝትም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ውጤት የተመዘገበው ከሁሉም ክልሎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እና በመናበብ መሥራት በመቻሉ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ድርሻም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት 350 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። ዕቅዱን ለማሳካትና የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኤክስፖርት ገቢውን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በዘርፉ ያሉ እድሎችን በሙሉ አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በቡና ብቻ ሳይሆን በሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎችም ኢትዮጵያ ምቹ ሁኔታና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዳላት የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከቡና በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ወረዳዎች የቅመማ ቅመም ምርት በስፋት እየተመረተ እንደሚገኝና የልማት ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። ይህም ከቡና ቀጥሎ የሀገሪቱን የኤክስፖርት ግኝት በማሳደግ ኢኮኖሚውን በመደገፍ ትልቅ አቅም ሊፈጥር እንደሚችልም ነው ያብራሩት። ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ መላው የተቋሙ ሠራተኞች በመንግሥት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መነሳሳት የፈጠሩበት ጊዜ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም