የአፍሪካ ባሎን ደ ኦር!

ታዋቂው የፈረንሳዩ መጽሔት ፍራንስ ፉትቦል በየዓመቱ የዓለም ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በመምረጥ የባሎን ደ ኦር ሽልማትን ይሰጣል:: ይህ መጽሔት የአፍሪካ ባሎን ደ ኦር ሽልማት ይሸልም እንደነበር ብዙም አይነገርም።

ፍራንስ ፉትቦል ይህንን የዓመቱን የአፍሪካውያን ኮከብ ተጨዋችነት ሽልማት በ1970 ጀምሮት በ1994 አቋርጦታል:: ከዛ በኋላ የየትኛውም አህጉር ተጫዋች በሽልማቱ ውስጥ እንዲካተት አድርጎ ሽልማቱን ቀጥሏል:: ለመሆኑ በፍራንስ ፉትቦል አፍሪካ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሸናፊ ማን ይሆን? በዛሬው የስፖርት ማኅደር ዓምዳችን እንመልከተው።

ሳሊፍ ኬይታ ይባላል:: የዝነኛው የሀገሩ ልጅ ዘፋኝ ሞክሼ ነው:: ማሊያዊ ነው:: የተወለደው በ1946 በመዲናዋ ባማኮ ነው:: የኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሪያል ደ ማሊ ሲሆን ሦስት ጊዜ የማሊ ዋንጫን ካነሳ በኋላ ለፈረንሳዩ ሴንት ኤትዬን ፈረመ:: 149 ጨዋታዎች አድርጎ 127 ጎሎችን አስቆጠረ:: አሁን ሊግ 1 እየተባለ የሚጠራውን ዋንጫ ሦስት ጊዜ እንደዚሁም ሁለት ጊዜ የካፕ አሸናፊ ሆኗል:: ከ1962 እስከ 1967 ለአምስት ሲዝኖች በፈረንሳዩ ክለብ ውስጥ ካሳለፈ በኋላ ወደ ኦሎምፒክ ደ ማርሴይ አምርቶ አንድ ሲዝን አሳልፏል:: ሦስት ሲዝን በቫሌንሲያ፣ ሦስት ሲዝን በስፖርቲንግ ፖርቹጋል ካሳለፈ በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሊግ በማምራት በኒው ኢንግላንድ ቲ ሜ ን ጫማውን ሰቀለ::

ሳሊፍ ኬይታ በሀገሩ ማሊ ዲያራ እና ካኑቴ እስኪመጡ ድረስ እጅግ በጣም የተከበረና ለበርካቶች እንደ ትልቅ አርዓያ የሚቆጠር ነበር:: ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው በ1963 ለማሊ ብ/ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው:: በ1972 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ሆነው ሲጨርሱ የእሱ ሚና ላቅ ያለ ነበር::

ጊኒያዊው የፊልም ዳይሬክተር ቼይክ ዱኮሬ በ1994 በእሱ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን “Le Ballon d’or” የተባለ ፊልም ሠርቶለታል:: አሁን የ76 ዓመት አዛውንት የሆነው ሳሊፍ ኬይታ ለሀገሩ ልጆች ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቹ አባላትም ጭምር ትልቅ ተምሳሌት ሆኗል:: ለምሳሌ የቀድሞው የባርሴሎና ኮከብ ሴይዱ ኬይታ፣ የቀድሞው የቫሌንሲያ፣ ሊቨርፑል እና ጁቬንቱስ የመሐል አማካይ ሞሐመድ ሲሶኮ እና ለረጅም ዓመት በሬንስ ክለብ አማካይ የነበረው ያያ ኬይታ የወንድሞቹ ልጆች ናቸው::

የዓለማችን ሁሉ ክዋክብት ትልቁ ሕልምና ስኬትም ይሄንኑ ሽልማት ማሸነፍ መሆኑ አያከራክርም። ያም ሆኖ በሽልማቱ ፍትሐዊነት ላይ ዘወትር ምክንያታዊ ጥያቄዎች መነሳታቸው ቀርቶ አያውቅም።

በተለያዩ ዘመናት በርካታ ጥቁር ተጫዋቾች የዓለምን እግር ኳስ አስደምመዋል። ይህን ታላቅ ሽልማት ማሸነፍ የቻለው ብቸኛ ተጫዋች ግን ላይቤሪያዊው ኮከብ ጆርጅ ዊሃ ሆኖ በታሪክ ተቀምጧል። ዊሃ ይህን ሽልማት በማሸነፉ ለበርካታ ጥቁር ከዋክብት ተነሳሽነትን ፈጥሯል፣ የዊሃ ስኬት ለመላው ጥቁር ሕዝብ ዛሬም ድረስ ኩራት ነው። ኮከቡ ግን ሽልማቱን በማሸነፉ ይከፋል እንጂ አይደሰትም። ለዚህም ምክንያት አለው።

በአሁኑ ወቅት ሀገሩ ላይቤሪያን በፕሬዚዳንትነት እየመራ የሚገኘው ዊሃ በ1995 በኤሲ ሚላን ባሳየው አስደናቂ ብቃት ትልቁን ባሎን ደ ኦር ሽልማት ያሸነፈ የመጀመሪያው ጥቁር ተጫዋች አድርጎታል። ይህን ትልቅ ስኬት ከእሱ በኋላም ለማግኘት የታደለ ጥቁር ኮከብ የለም። ዊሃ በአንድ ወቅት በሰጠው አስተያየት ግን ይህን ሽልማት በማግኘቱ ኩራት እንደማይሰማውና እንደማይደሰትበት አስገራሚ አስተያየት ሰጥቷል።

“የወርቅ ጫማውን በማሸነፌ ኩራት አይሰማኝም፣ ይህ ሽልማት ካገኘሁ በኋላ በአውሮፓ የዘረኝነት ሰለባ ሆኛለሁ” ይላል ዊሃ። የላይቤሪያው ወርቅ የብዙዎችን ልብ በሰበረው ቃለመጠይቁ ሽልማቱን ካሸነፈ በኋላ ሚዲያዎች የዘገቡበትን መንገድ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ሽልማቱን ባሸነፍኩ ማግስት ላ ጋዜጣ ዲሎ ስፖርት በፊት ለፊት ገፁ ጎልቶ በሚታይ ሰፊ ርዕስ ይዞት የወጣው ዘገባ ይታወሰኛል፣ ኦ ጥቁሩ ሰው የወርቅ ጫማ አሸነፈ” የሚል ነበር።

ዊሃ ሽልማቱን ካሸነፈ በኋላ በሚላን ከተማ ውስጥ ሰዎች በእሱና በአፍሪካ ይስቁ እንደነበር ያስታውሳል። “የወርቅ ጫማውን ሸጠህ ዳቦ ልትገዛላቸው ነው?” ያሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በአህጉሩ አፍሪካ ድህነት ይሳለቁ እንደነበርም ይናገራል። ዊሃ ሽልማቱን በማሸነፉ በቆዳ ቀለሙ መጥቆር በደረሰበት ነገር ብቻ አይደለም የሚቆጨው፣ በሽልማቱ ፍትሐዊነት ላይም ምክንያታዊ ጥያቄ ያነሳል። “ድሮግባ ከቼልሲ ጋር ሁሉንም ነገር አሳክቷል፣ ሳሙኤል ኤቶም ከባርሴሎናና ከኢንተር ሚላን ጋር ያላስመዘገበው ክብር የለም፣ ግን የወርቅ ጫማውን ሸለሟቸው? በፍፁም! ምክንያቱም እነሱ ይህን ሽልማት ለአፍሪካውያን ተጫዋቾች የመስጠት ሰብዓዊነቱም የሞራል ልዕልናውም የላቸውም” በማለት ዊሃ አስገራሚ አስተያየቱን ሰንዝሯል።

የዊሃ ታሪካዊ ድንቅ ንግግር ይቀጥላል:- “ለምርጥ ተጫዋች የሚሰጠው የወርቅ ጫማ አይደለም፣ ትክክለኛው ወርቅ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ንጹሕ ልብ ነው፣ ትክክለኛው የወርቅ ሽልማት የሌሎችን ስሜት አለመጉዳት ነው፣ እውነታው ግን እነሱ(“ነጮች”) ዘረኝነት እንጂ ሰብዓዊነት በውስጣቸው አለመኖሩ ነው”።

 ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2016

Recommended For You