የአዲስ አበባ ከተማ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በከተማዋ የጤና አገልግሎት ጥራትና ብቃትን ለማረጋገጥ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በሁሉም የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማትና የመድኃኒት ቸርቻሪ ድርጅቶች የሕክምና መስጫ ግብዓቶችን ይቆጣጠራል፤ብቃታቸውን ያረጋግጣል፡፡ በተመሳሳይ መሥሪያ ቤቱ የምግብና ጤና ነክ ግብዓቶችና አገልግሎቶችን ሀገራዊ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ የቁጥጥር ሥራ ይሰራል፡፡
ይህ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋነኛ ተግባርና ኃላፊነት ሆኖ ታዲያ ሁሉንም የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች ባስቀመጠው እቅድ ልክ መከወን አልቻለም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በተቋሙ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች የሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣት፣ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴው ከቁጥጥር ሥራው በላይ እየበለጠ በመምጣቱ፣ በሕገ ወጦች ላይ የሚወሰደው ርምጃ አስተማሪና ጠንካራ አለመሆን፣ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ አለመሥራት ብሎም በጉዳቱ ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ ያለመሥራት ከምክንያቶቹ ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
በእነዚህና በተለያዩ ምክንያቶች የከተማዋ ነዋሪ የጤና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መጥቷል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የቁጥጥር ሥርዓቱ መላላት ሕገወጦች እንደልባቸው እንዲፈነጩ በር ከፍቷል፡፡ ለዚህም ይመስላል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የቁጥጥር ሥራውን ይበልጥ በማጠንከር የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ከሌሎች የከተማው ሴክተር ቢሮዎች ጋር በጋራ ሆኖ ለመሥራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ከሰሞኑ የተፈራረመው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ እንደሚናገሩት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተለይ በሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ወቅት በየቦታው ተመርተው በሚወጡ ምግቦች ጥራታቸውን የጠበቁና በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ከፍተኛ የቁጥጥር ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም በርከት ያሉ ጊዚያቸው ያለፈባቸው የምግብ ምርቶች ተይዘው እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡
የቁጥጥር ሥራ አሁንም እየተሰራ ነው፡፡ ተቋማት የንግድ ፍቃድ ከማውጣታቸው በፊት የብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው የሚያስችል ሕግ የከተማ አስተዳደሩ ምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕግ አውጥቶ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ግን ደግሞ የቁጥጥር ሥራው የተሟላ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ገና ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ጥራት ያለው ምግብና መድኃኒት ለማቅረብ እንዲሁም የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ አሳዳጅ፤ ሌላው ደግሞ ተሳዳጅ የሚሆንበት ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉም በባለቤትነትና ጉዳዩ ይመለከተኛል በሚል እንዲሰራ በተለይ የአመለካከት ለውጥ ላይ ከፍተኛ ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎም ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁንም በቁጥጥር ማነስ ምክንያት ጥራት ያላቸውን ምግቦችና መድኃኒቶችን ማቅረብ ላይ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህን ለማሻሻል ባለሥልጣኑ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
ከነዚህ የሪፎርም ሥራዎች ውስጥ አንዱ የነበረውን የሕግ ክፍተት መሙላት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በቁጥጥር ሂደት የሚገኙ ጥራታቸው ያልተጠበቁ ምግቦች ላይ ወዲያው የሕግ ውሳኔ ያለመስጠትና በሕግ ተጠያቂ ያለማድረግ ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን ለማሻሻል ደንቦች፣ ሕጎች፣ አዋጆችና ስታንዳርዶች እየተከለሱ ይገኛሉ፡፡ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለምሳሌ ተቋሙ የራሱ ኢንተለጀንስ ኖሮት መረጃ እንዲደርሰው የማድረግ ሥራዎችን ለማከናወን ጥናት ተደርጓል፡፡ ወደ ሥራ መግባት ብቻ ይቀራል፡፡ ለቁጥጥር ሥራው የሚያስፈልጉ ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ጤናማና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ እስከሆነ ድረስ የቁጥጥር ሥራው የባለሥልጣኑ ብቻ ስላልሆነ የሁሉንም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተሳትፎና ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ሰዎች ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንጂ በሕክምና ስህተት ተጨማሪ ጉዳት ማስተናገድና መሞት የለባቸውም፡፡ ለዚህም ባለሥልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንዳለበት አምኖ ሥራዎች እየሰራ ነው፡፡ እስካሁን የተከማቹና ፍትህ ያላገኙት ላይ ደግሞ በዘመቻ እየሰራ ይገኛል፡፡
በቀጣይ ደግሞ ቁጥጥሩን ይበልጥ ለማጥበቅ ጠንካራ ሥራ ይሰራል፡፡ በተለይ ደግሞ በቸልተኝነት ስህተት የሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጠንከር ያለ ሕግ ርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ ይሰራል። በተመሳሳይ በሌሎች የምግብና መጠጥ ምርቶች ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከተፈለገ በዋናነት አምራቹ ዜጋ መቀየር አለበት፡፡ ምክንያቱም አምራቹ በተዘዋዋሪ ምርቶቹን ለእናቱ፣ አባቱ፣ እህቱ፣ ወንድሙና ልጁ ስለሚሸጥ ጉዳቱ በራሴና በቤተሰቦቼ ላይም ጭምር ነው የሚለውን አመለካከት ማዳበር ይኖርበታል፡፡
ይህን አመለካከት ለመቀየር በተለይ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማቀበል ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸውና ይህን ሚናቸውን በሚገባ በመወጣት የቁጥጥር ሥራውን ይበልጥ ማጠንከር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እስካሳሰበው ድረስ በዚህ የቁጥጥር ሥራ ውስጥ መሳተፍና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን በበጎ ፍቃድ ሊያግዝ ይገባል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጇ እንደሚያብራሩት፣ ከሕግ አንፃር ደግሞ አስተማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱና የቁጥጥር ሥራውን ለማጠንከር ተተግባሪ መመሪያዎች፣ አዋጆችና ደንቦች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ መመሪያዎች፣ ደንቦችና አዋጆች እንዲከለሱ ተደርጓል፡፡ ለፍትህ ቢሮም ተልከዋል፡፡ ፍትህ ቢሮ ሲያጸድቃቸው ሥራ ላይ የሚውሉ ይሆናሉ፡፡ ለመቅጣትና በሕግ ተጠያቂ ለማድረግም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ያግዙታል፡፡
ከሙስና ጋር በተያያዘም ከባለሃብቱም ሆነ ከተቆጣጣሪ ሠራተኛው በኩል ችግሮች ይታያሉ። ከዚሁ ሁኔታ አንፃር ከሙስና ፀድቶ ዝቅ ብሎ ማገልገል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ዝቅ ብሎ ለማገልገል ባለሙያው መስፈርቶችን ማሟላት አለበት። መጀመሪያ ባለሙያው ለራሱ ሲል በልበ ሙሉነት መሥራት አለበት፡፡ ሁለተኛ አምራቹ የሚሸጠው ምርት ለቤተሰቡ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የካንሰርና የሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ የአካል ጉዳትና ሞት ጉዳይ የኔ ነው የሚውን አስተሳሰብ መያዝ አለበት፡፡
የባለሥልጣኑ ባለሙያ ጥራት ያለው ምግብና የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር በዚህ ሂደት የሚመጡ ጥቅማጥቅሞችንና መደለያዎች መቀበል የለበትም። ለዚህም አምራቹና ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ይህን ችግር ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ግን ደግሞ ገና ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡
ይህ ችግር ከአመለካከት ጉድለትም ጭምር የሚመጣ ነው፡፡ ምክንያቱም ሀብት ማለት ሰው ነው፡፡ ሰው ከሰው ጋር ሲኖር ነው በችግር ውስጥ የሚሻገረው እንጂ ሀብቱ ወይም ገንዘቡ አይደለም የሚያሻግረው። ዛሬ ሀብት ያለው ሰው ነገ ደሃ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ሰው ችግር ሲደርስበት ለችግሩ የሚቆምለትና አብሮ የሚያሳልፈው ሰው ነው፤ ጎረቤት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ከህሊናም ጭምር ነው፡፡ የቁጥጥር ሥራው ሰፊ ንቅናቄና ተነሳሽነት ይጠይቃል፡፡ የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ ያስፈልገዋል። በዚህ ሴክተር አገልጋይነትን የተላበስ ሥራን መሥራት የግድ ይላል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጇ እንደሚገልፁት፣ የበጀት ዓመቱ አንደኛ ሩብ ዓመት በአብዛኛው የእቅድ ዝግጅት፣ መልሶ ማደራጀት፣ የበጀትና የግብዓት መሟላት ላይ ያተኩራል። ስለዚህ በዚህ ጊዜ ስልጠናና ንቅናቄ ብዙ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በዚህ ሩብ ዓመት የግንዛቤ ማስጨበጫን በሚመለከት እምብዛም ሥራ ያልተሰራው። በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስተኛ ሩብ ዓመት ግን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎቹ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ከባህል ሕክምና ጋር በተያያዘም ህብረተሰቡ መሰል ችግሮች እንዳሉ ያነሳል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ሆነው ከዘመናዊው ሕክምና ጎን ለጎን በጤናው ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት የሚያግዙ አሉ። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም በባህል ሕክምና በኩል የሚታዩ አንዳንድ ስህተቶችን በማየት በሕግ አግባብ ለመጠየቅ እየሰራ ይገኛል፡፡ አስፈላጊው የቁጥጥርና ክትትል ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በ2015 ዓ.ም በትምባሆ መከላከል ዙሪያ አበረታች የንቅናቄ ሥራ ተሰርቷል። ሆኖም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በርካታ ወጣቶች አሁንም በሱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በየተቋማቱ ትምባሆ እንዳይጨስ የሚከለክሉ ሕጎች ቢወጡም አሁንም እየተተገበሩ አይደለም፡፡ በአንደኛ ሩብ ዓመት በብዛት ወደ ንቅናቄ አልተገባም፡፡ በቀጣዮቹ ሩብ ዓመታት ግን ወደ ትምባሆ ቁጥጥርና የንቅናቄ ሥራ በስፋት ይገባል፡፡
የባለድርሻ አካላት ስለትምባሆ ያላቸውን ግንዛቤና የቁጥጥር ሥራ ለማጠንከር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከባለድርሻ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በዚሁ መሠረት ሥራው የት እንደደረሰ በየጊዜው ግምገማ ይካሄዳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥጥር ባለሥልጣን በ2016 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በ18 የጤናና በ734 የምግብና የመጠጥ ተቋማት ላይ የማስተካከያ ርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ሲሆን በ31 የመድኃኒት ቸርቻሪ ተቋማት ላይም ፍቃድ የመሰረዝና የማሸግ ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ባለሥልጣኑ በዚሁ ሩብ ዓመት በጤና ፣ መድኃኒት ችርቻሮ፣ ምግብና መጠጥ ተቋማት ላይ በሠራው ሥራ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተበላሹ የምግብ፣ መጠጥ እንዲሁም ከ254 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች ማስወገድ መቻሉም ተነግሯል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም