ገብረመድህን ኃይሌ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

አዲሱ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) አሠልጣኝ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ የዋልያዎቹ መሪ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ውል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትናንትናው እለት አስረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት የዘለቁት አንጋፋው አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሾማቸውን ተከትሎ፣ ሥራቸውን እአአ ለ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የሚጀምሩ ሲሆን፤ የብሔራዊ ቡድን ስብስባቸውንም አሳውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኅዳር 5 እና ኅዳር 11/2016 ዓ.ም የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎቹን ከሴራሊዮን እና ቡርኪናፋሶ አቻዎቹ ጋር በተከታታይ በሜዳው ያከናውናል፡፡ ይህንንም ተከትሎ አሠልጣኙ ዋልያዎቹን ከሴራሊዮን ጋር ለሚኖራቸው የመጀመሪያው ጨዋታ ከነገ ጀምሮ ወደ ዝግጅት በመግባት ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ለቀናት በሚኖራቸው የዝግጅት ጊዜም አንድ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ግጥሚያው ወደሚደረግበት ሞሮኮ እንደሚያቀኑም ነው ትናንት በተደረገው የፊርማ ሥነሥርዓት ያስታወቁት፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ተፎካካሪ ቡድን የሆነው ኢትዮጵያ መድንን በማሠልጠን ላይ የሚገኙት አሠልጣኙ፤ ከክለቡ ጋር ለረጅም ጊዜ የሚያቆያቸው ውል አላቸው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለም ከክለብ አገልግሎታቸው ጎን ለጎን ዋልያዎቹን ለአንድ ዓመት ለማሠልጠን መስማማታቸው ተጠቁሟል። በወር የተጣራ 250ሺ ብር እየተከፈላቸውም ዋሊያዎቹን የሚመሩ ይሆናል። በቀድመ አጠራሩ መከላከያ(መቻል)፣ ጅማ አባቡና፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ ከተማ፣ ሲዳማ

 ቡና እና አሁኑን ኢትዮጵያ መድንን እያሠለጠኑ የሚገኙት ገብረመድህን በተጫዋችነት ዘመናቸው ከወጣት ቡድን አንስተው እስከ ዋና ብሔራዊ ቡድን አምበልነት የመሩ ድንቅ ተጫዋች እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሠልጣኝነትም ከ20 ዓመት በታች አንስቶ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ማገልገል ችለዋል።

አሠልጣኝ ገብረመድህን በተለይም እአአ 2016 በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዋልያዎቹን በጊዜያዊነት የመሩ ሲሆን ሌሴቶንና ሲሼልስን እንዳሸነፉ ይታወሳል። ከዚያም በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ረዳት በመሆን የሴካፋ ዋንጫን ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡

ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነታቸው የተመለሱት አሠልጣኙ ‹‹በድጋሚ ወደ ብሔራዊ ቡድን ተመልሻለሁ፣ ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት አዲስ አይደለሁም፡፡ ይሄ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ክለቤንም ብሔራዊ ቡድኑንም እንዳሠለጥን ነው ስለዚህም ባለው ፕሮግራም መሠረት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት በተጫዋቾች ምልመላ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ በአጭር ጊዜ በቡድኑ አዲስ ነገር መፍጠር ባንችልም በሂደት ተተኪ እና ሥነምግባር ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለማምጣት እንሠራለን›› ብለዋል፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚኖራቸው ቆይታ በውሉ መሠረት አንድ ዓመት ቢባልም ሊራዘም እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

ሁለት ቡድኖችን በአንዴ ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ስለሚኖረው አስቸጋሪ ሁኔታ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኙ፤ ችግር ሊኖረው ቢችልም ሥራቸውን ትኩረት ሰጥተው በተገቢ ሁኔታ በመሥራት እንደሚያቻችሉትም ገልጸዋል፡፡ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አንድ ቦታ የሚከናወን መሆኑ ሊኖር የሚችለውን አስቸጋሪ ሁኔታ በማቃለል ረገድም የጎላ ሚና አለው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁለት ቡድኖችን መያዝ የጥቅም ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ይህንን በሚመለከትም አሠልጣኙ ቅድሚያ የሚሰጠው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደመሆኑ ቡድኑን የሚመጥን ተጫዋች ከየትኛውም ቡድን ሊመረጥ እንደሚችል አስረግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስንብት በኋላ በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ዳንኤል ገብረማርያም ጊዜያዊ አሠልጣኝነት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም አዲስ አሠልጣኝ የሾመው ፌዴሬሽኑ፤ አሠልጣኙን በዋናነት ለዓለም ዋንጫ እና አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እንዲመሩ የቀጠራቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በስምምነት ሥነሥርዓቱ ላይ መግለጫውን የሰጡት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፤ ሥራ አሥፈጻሚው አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ለመቅጠር ከስምምነት ላይ የደረሰው ከአምስት ወራት በፊት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን አሠልጣኙ ከክለባቸው ጋር ውል ያላቸው እንደመሆኑ ንግግር በማድረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ አሠልጣኝ ከክለብ ጋር ውል እያለው ብሔራዊ ቡድኑን ማሠልጠን አይችልም የሚል ሕግ በፌዴሬሽኑ ሲተገበር የቆየ ቢሆንም፤ ሥራ አሥፈጻሚው ለፌዴሬሽኑ ጥቅም ሲባል ሕጉን አሻሽሏል፡፡ በመሆኑም ለአንድ ዓመት በሚኖረው ቆይታ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ሲኖሩ ፕሪምየር ሊጉ የሚቋረጥ በመሆኑ አሠልጣኙ ዋሊያዎቹን በማዘጋጀት በጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You