ግንባታቸው እየተሳለጠ ያለው የከተማዋ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ለማሻሻልና ለማዘመን እየሠራ ይገኛል፡፡ መንገዶች የአገልግሎት ዘመናቸው የተራዘመ እንዲሆን ለማድረግ የጥገና ሥራዎችን ይሰራል። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መንገዶች ላይ የከተማዋን የመንገድ ኔትወርክ በማስተሳሰር የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ግንባታዎችንም ያካሂዳል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የበርካታ መንገዶች ግንባታ መካሄዱንና እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከሚያካሂዳቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች መካከልም በዋና ዋና መንገዶች አደባባዮች ላይ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ እንዲያስችሉ የሚገነቡት የማሳለጫ መሻገሪያ ድልድዮች ግንባታ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኢያሱ ባለሥልጣኑ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረውን የቦሌ ሚካኤል ማሳለጫ ድልድይን ጨምሮ በከተማዋ የተለያዩ መንገዶች ላይ ወደ ስድስት የሚደርሱ የማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድዮች ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በውስጠኛው ቀለበት መንገድ/ ከመገናኛ በቦሌ፣ ቃሊቲ፣ ለቡ መካኒሳ አየር ጤና፣ ኮልፌ አዲሱ ገበያ ያለው/ በዋና ዋና የመጋጠሚያ ቦታዎች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በሶስት ቦታዎች ላይ የማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድዮች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም የቦሌ ሚካኤል፣ የኢምፔሪያልና የለቡ ቀለበት የመንገድ መጋጠሚያ የትራፊክ ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድዮች ግንባታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የቦሌ ሚካኤል ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድይ

አቶ ኢያሱ እንዳሉት፤ የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆና ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡ ማሳለጫ ድልድዩ በአጠቃላይ ወደ 600 ሜትር ርዝመት እና 30 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋትም አለው፡፡ የግንባታው ሥራውም በአጠቃላይ በአካባቢው የተሰሩትን የመቃረቢያ መንገዶችን ጨምሮ ከ787 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት የተከናወነ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ2013 ሲሆን፣ በአካባቢው መነሳት የነበረባቸው በርካታ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች ነበሩበት፡፡ በሁለት አቅጣጫ /ከቦሌ ወደ ቡልቡላ/ ወደ መንገድ መጋጠሚያ የሚመጡ መንገዶችን ጨምሮ የግንባታ ሥራው ተከናውኗል፡፡

የዚህ ድልድይ ግንባታ ለየት የሚያደርገው ነገር እንዳለም ነው አቶ ኢያሱ ያስታወቁት፡፡ ግንባታው የተከናወነው በሀገር ውስጥ ተቋራጭ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ ግንባታውን ያካሄደው የሀገር ውስጥ ተቋራጭም አሰር ኮንስትራክሽን ድርጅት እንደሚባል ጠቁመዋል፡፡

የዚህን ፕሮጀክት ጨምሮ የዘጠኝ ፕሮጀክቶች የግንባታ ወጪ የተሸፈነው በሀገር ውስጥ በጀት መሆኑን ጠቁመው፣ የግንባታ ሥራዎቹም ሙሉ ለሙሉ ከማማከር አንስቶ ዲዛይንና ግንባታው በኢትዮጵያውያን መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

የለቡ ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድይ

ይህ ተሻጋሪ ድልድይ በአጠቃላይ አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር ርዝመትና አርባ ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ይገኛል፤ ለግንባታውም ከ634 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተመደለት ነው፤ ፕሮጀክቱ በቻይና ፈርስት ሀይዌይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራ ተቋራጭነት እየተከናወነ ሲሆን፣ የማማከር ሥራው ደግም ስታዲያ በተባለ ድርጅት ነው የሚከናወነው፤ ባለፈው ክረምት ወቅት የዚህ ተሻጋሪ ድልድይ አብዛኛዎቹ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት ተደርጎ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አቶ ኢያሱ ጠቅሰው፣ አሁን የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኤምፔሪያል ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድይ

ይህ ተሻጋሪ ድልድይ አጠቃላይ 300 ሜትር ርዝመት እና 40 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ነው። መቃረቢያ መንገዶችን ጨምሮ ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሆን ፕሮጀክት ነው፡፡ ግንባታውም በቻይና ፈርስት ሀይዌይ ኢንጂነሪግ ኩባንያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራም በአሁኑ ወቅት 91 በመቶው መጠናቀቁንም ኃላፊው አስታውቀው፣ ከ814 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተመደበለት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የዚህን ፕሮጀክት /በሁሉም አቅጣጫ በቀኝ መታጠፊያ በኩል ባሉ የመንገድ መተላለፊያዎች ላይ/ አስፋልት የማልበስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቀሩትን የመንገዱን አካሎች አስፋልት የማልበስ ሥራ መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡

የቃሊቲ ቱሉዲምቱ መንገድ ፕሮጀክቶች ድልድዮች

አቶ ኢያሱ በቃሊቲ ቱሉዲምቱ መንገድ ፕሮጀክት ላይም የተለያዩ ድልድዮች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ከእነዚህም መካከል ቃሊቲ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ላይ እየተገነባ ያለው ድልድይ አንዱ ሲሆን፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢም የሌላ ትልቅ ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታ መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡ በተለምዶ ጋሪ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይም እንዲሁ 50 ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ እንዲሁም የቃሊቲ አደባባይ ቡልቡላ ቂሊንጦ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ግንባታዎቹ ይከናወኑ የነበሩት ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰው፣ ፕሮጀክቶቹ በገጠማቸው የፋይናንስ አቅርቦትና የወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት መጓተታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ወሰን ማስከበር እንዲሁም ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር፣ የከተማ አስተዳደሩ በብድር ተወስዶ እንዲሰራ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በመፈታቱ ግንባታቸው በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ሌሎች ማሳለጫዎችን እንደ ፋይናንስ አቅርቦቱ እና የማሳለጫዎቹ ተገቢነት እያየ እንደሚገነባም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በአየር ጤና ሌላ የማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታ እንደሚካሄድም አመልክተዋል፡፡ የአየር ጤና አካባቢ ከፍተኛ የመንገድ መጨናነቅ እንደሚታይበት ጠቅሰው፣ የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ከአየር ጤና አደባባይ አንስቶ እስከ ወለቴ እንደሚዘልቅ አስታውቀዋል፡፡ የግንባታው ውል ባለፈው ዓመት መፈጸሙንም አስታውሰው፣ ወደ ግንባታ ሥራው ለመግባት ግን የወሰን ማስከበር ሥራዎች ያልተጠናቀቁበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ይህ እንደተጠናቀቀ ወደ ግንባታ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

በ2016 የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት፣ አንዱና ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው፣ ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ ባለፈው ዓመት ውል ተገብቶባቸው ወደ ግንባታ ያልገቡ ፕሮክቶችን የወሰን ማስከበር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ማስገባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከመሀል ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚገነቡ መንገዶች የትራፊክ ማሳለጫ የሚጠይቁ ከሆነ አካተን እንገነባለን›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹በቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ላይ ሶስት ማሳለጫዎች የተገነቡትም ለዚሁ ነው›› ብለዋል፡፡

የከተማዋ የመንገድ ኔትወርክ ደህንነት የተጠበቀና ከትራፊክ መጨናነቅ ውጭ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ባለሥልጣኑ እንደሚገነዘብ ጠቅሰው፣ ሁሉንም ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ፋይናንስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት ከሚመድብባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የመንገድ ዘርፉ ነው፤ የከተማዋ በጀት በየዓመቱ ቢያድግም የኮንስትራክሽን ዋጋውም በዚያው ልክ እየጨመረ ነው፤ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም፣ መሥራት የሚቻለው ባለው አቅም በመሆኑ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድዮቹ ትሩፋቶች

የቃሊቲ ቱሊዲምቱ መንገድ የከተማ ዋና የሀገሪቱ የወጭ ገቢ ንግድ ኮሪደር መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ማህበራዊ ፋይዳውም ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት። በዚህ መንገድ ላይ የተካሄዱ የማሳለጫ ድልድይ ግንባታዎች ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ከከተማ ውጪ በሚል እሳቤ የተገነባውና አሁን ከተማ ውስጥ የገባው የከተማዋ የውስጥ ቀለበት መንገድ (37 ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ) ትልቅ የትራፊክ ፍሰት የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአጠቃላይ ለከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች መካከል እንደሚጠቀስም ተናግረዋል፡፡

በዚህ መንገድ ላይ ማሳለጫ እየተገነባባቸው ባሉ ሥፍራዎች ላይ ቀደም ሲል አደባባዮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ከዚያም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ሲፈጠር አደባባዮቹን በማፍረስ በትራፊክ መብራት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ጥረቶች በወቅቱ የነበረውን ችግር በተወሰነ መልኩ ማቃለል መቻሉን አመልክተው፣ ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ባለመፍታታቸው በትራፊክ ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድይ እንዲቀየሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ትላልቅ የመንገድና የማሳለጫ ድልድዮች ግንባታዎችን ሲያካሂዱ ከቆዩ የውጭ ተቋራጮች ስለተገኘ እውቅትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኢያሱ በሰጡት ምላሽ አንድ ተቋራጭ በማሳለጫ ግንባታ ላይ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ በውስጠኛው ቀለበት መንገድ ላይ ከሚገነቡት ድልድዮች የቦሌ ሚካኤሉ የተገነባው በሀገር ውስጥ ተቋራጩ አሰር ኮንስትራክሽን መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያውያን ተቋራጮች ትልቅ የመፈጸም አቅም እያዳበሩ ስለመምጣታቸው የዚህ ኩባንያ አፈጻጸም ያመለክታል ብለዋል፡፡

እስከ አሁን የትላልቅ ማሳለጫ ድልድዮች ግንባታ በሀገር ውስጥ ተቋራጮ የሚደፈሩ አልነበሩም ያሉት ኃላፊው፣ አሁን ግን ይህ ሁኔታ መቀየሩን ጠቅሰዋል። በሀገር ውስጥ ተቋራጭ የተሰራው የቦሌ ሚካኤል ማሳለጫ ድልድይ በሌሎች አካባቢዎች ከተሰሩት ማሳለጫዎች ጋር ሊወዳደር የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። አሰር ኮንስትራክሽን በዚህ ደረጃ መገኘቱ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች አቅም እየተገነባ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩ ተቋራጮች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከቻይና ኩባንያዎች ብዙ ልምድ የተወሰደበትና በዚህም ተገልጋዩ ህብረተሰብ እየተደነቀ ያለበት ሁኔታ እንዳለ መረዳት የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የመንገድ መሰረተ ልማቱ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው

ከመንገድ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ለሚታየው የፕሮጀክት መጓተት ትልቁ ምክንያት እየሆነ ያለው ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያለው ችግር መሆኑን አቶ ኢያሱ አስታውቀዋል። የወሰን ማስከበር ችግር በፍጥነት ከተፈታ ሥራዎችን በፍጥነት ማከናወን እንደሚቻል፤ በዚያው ልክም ችግሩ ካልተፈታ ሥራዎቹ ምን ያህል ሊጓተቱ እንደሚችሉ ሁለት ፕሮጀክቶችን በማሳያነት ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

ኃላፊው ለዚህ በአብነት ያነሱት አንዱ ፕሮጀክት የአሌክሳንደር ፑሽኪን ጎፋ ማዞሪያ ጎተራ መንገድን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው በ2012 መስከረም ሲሆን፣ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ትላልቅ ስትራክቸሮችን አካቶ የተገነባ፣ ሶስት መቶ ሃያ ሜትር ዋሻ ያለው፣ ከላይ መተላለፊያ ድልድይ የተካተተበት ነው፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የአውቶብስ ተራ መሳለሚያ 18 ማዞሪያ መንገድ ፕሮጀክት ከዚሁ ፕሮጀክት ጋር አብሮ ነው የተጀመረው፡፡ ነገር ግን የወሰን ማሰከበር ሥራው ሲጓተት በመቆየቱ በተፈለገው ደረጃ ግንባታውን ማከናወን አልተቻለም፡፡ ለፕሮጀክቶች መጓተት ትልቁ ፈተና የሚሆነው የወሰን ማስከበር ችግር ለመሆኑ ይህ አንድ ማሳያ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አንዳንዴ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ይገጥማቸዋል፤ ለእዚህም የቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ፕሮጀክት በአብነት ተጠቅሷል። ከሥራ ተቋራጮች የመፈጸም አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ የሚገጥም ችግርም አለ፡፡ ለእዚህም ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው በቅርቡ ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት የተደረገው የአራራት ኮተቤ ካራ መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡

‹‹በመንገድ ግንባታ ወቅት ትልቅ ፈተና እየሆነብን የመጣው የወሰን ማስከበር ሥራ አለመጠናቀቅ ነው›› የሚሉት አቶ ኢያሱ፣ ብዙውን ጊዜ የወሰን ማስከበር ሥራ ሳይጠናቀቅ ለምን ወደ ሥራ አትገቡም የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ እንኳንስ ወሰን የማስከበር ሥራ ያልተከናወነላቸው ፕሮጀክቶች፣ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ቀሪ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን ለማከናወን በግንባታ ሥራ ላይ ትልቅ ፈተና እየገጠመን ይገኛል›› ብለዋል፡፡

የወሰን ማስከበር ሥራው ሙሉ ለሙሉ ካልተጠናቀቀ ፕሮጀክቶቹ እየተገፉ ለረጅም ጊዜ ሳይጀመሩ የሚቆዩባቸው ሁኔታዎች እንደሚገጥሙ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በተቻለ መጠን ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ ጀምረን ወሰን ማስከበር ሥራውን ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመሥራት ግንባታዎቹን በፍጥነት ለማከናወን ጥረት እያደረግን ነው፤ በዚህም የተሻለ ስኬት አለ ተብሎ ይወሰዳል›› ብለዋል፡፡

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You