ያላለፈ ትናንት …

እናትና ልጅ…

ብቸኛዋ ሴት ስለ መኖር ያልሆኑት የለም። ለዓመታት ትንሹን ልጅ ይዘው ተንከራተዋል። ያለ አባት የሚያድገው ሕጻን ከእናቱ ሌላ ዘመድ አያውቅም፡፡ በእሳቸው ጉያ በላባቸው ወዝ ያድራል፡፡ በሚከፍሉት የጉልበት ዋጋ እንደነገሩ ይኖራል፡፡ ለእሱ ሕይወትና ተስፋው፣ ዛሬና ትናንቱ ከእናቱ ተቆራኝቷል፡፡ ትንሹ ልጅ ዓባይነህ ሀብታሙ ፡፡

የዓባይነህ እናት ብርቱ ሴት ናቸው፡፡ ልጃቸውን ለማሳደግ በየቤቱ እንጀራ ይጋግራሉ፡፡ የሚታጠበው፣ የሚቆላ፣ የሚከካው፣ ከእሳቸው እጅ አያልፍም።፡ ለድካማቸው የሚያገኙት ምንዳ ደግሞ እዚህ ግባ አይሉትም፡፡ እንዲያም ሆኖ አዝነው፣ ተማረው አያውቁም፡፡ የያዙትን ይዘው ለልጃቸው ሆድ ይደርሳሉ።

ቤት ሲገቡ የጎን ማረፊያው አይመችም፡፡ ሁሌም የደባል ቤታቸው እንደሾህ ነው፡፡ እፎይታ ይሉት የለውም፡፡ በምቾት አልባ ዕንቅልፍ ሌቱ ይነጋል፡፡ ቀኑ በተለምዶ ድካም ያልፋል፡፡

ትንሹ ዓባይነህ …

ዓባይነህ የእናቱ ልጅ ነው፡፡ ችግር መከራ፣ ብርቁ አይደለም፡፡ ሁሌም የእሳቸው ሕይወት ሕይወቱ ነው፡፡ ፈተናቸውን ይጋራል፣ ኑሯቸውን ይካፈላል። የእናትና ልጅ የእንክርት ኑሮ አላበቃም፡፡ ስለመኖር በደባልነት የሚከፍሉት ዋጋ ቀጥሏል፡፡

ከቀናት በአንዱ የዓባይነህ እናት ከሰዎች መከሩ። ምክሩ ልባቸው ሲገባ አልዘገየም፡፡ በቅርብ የሚያውቋቸው አንዲት ሴት ዓባይነህን ይዘው ከቤታቸው እንዲኖሩ ፈቅደዋል፡፡ ይህ የምሥራች ለቤት አልባዋ ሴት ቀላል አልሆነም፡፡ እስከዛሬ በደባል ቤት ኑሮ ተንከራተዋል፡፡ ያላለፈ ድህነት ተጭኖ ፈትኗቸዋል፡፡

ዓባይነህ ከእናቱ ጋር ወደ ተባለው ቤት አመራ። ግቢው በቆሻሻ ክምር የተከበበ ነው፡፡ እነሱ ከወለል አንጥፈው እንዲተኙ ተፈቅዷል፡፡ በቤቱ መሐል የሚያልፈው የመፀዳጃ ፍሳሽ የእነ ዓባይነህን መኝታ ጎብኝቶት ያልፋል፡፡

ዕድሜያቸው የገፋው ሴት ራሳቸውን መግዛት ካቆሙ ሰንብተዋል፡፡ ካልጋ የዋሉት ባላቸው ሕመማቸው ከፍቷል፡፡ ሁለቱም የሌሎች ድጋፍ ያሻቸዋል፡፡ በዚህ እውነታ እናትና ልጅ ከእነሱ ጋር ኑሮን ጀመሩ፡፡ ቢከብድም ይህ እንዲሆን ግድ ሆነ፡፡

አዛውንቷ ውሎ አድሮ ባሕሪያቸው ተቀየረ። የዕድሜያቸው መግፋት እንደልጅ ያደርጋቸው ያዘ። ‹‹ካረጁ አይበጁ››ን የተረቱ በርካቶች በሚያዩት ድርጊት ሸሽተው ራቁ፡፡ እነ ሀብታሙ እሳቸውን ሊተዉ አልቻሉም፡፡ ሴትዬዋን ቀርበው መጠበቅ መንከባከብ ያዙ፡፡ ይህ አጋጣሚ የእናትና ልጅን ጤና ፈተነ፡፡ ሁለቱም በጉንፋን ተሰቃዩ፣ በደረቅ ሳል ተንተከተኩ፡፡

አሁንም የሰው ቤት ኑሮ አልሆነም፡፡ ስቃይ የሞላው ሕይወት ፈተና በዛበት፡፡ በዘመኑ ለቀበሌ ነዋሪዎች ኩፖን ይሰጥ ነበር፡፡ እነሀብታሙ የሌሎችን ዕድል ተጠቅመው ለቀበሌው ማመልከቻ አስገቡ፡፡ ፍላጎታቸው ቤት እንዲያገኙ ነበር፡፡

የታሰበው አልሆነም፡፡ ያለመፍትሔ የሰው ቤት እንክርቱ ቀጠለ፡፡ የሀብታሙ እናት ተስፋ ቆረጡ። እያደር ኑሮ ይመር ይከብዳቸው ጀመር። ይህ እውነት ልባቸውን ለመንገድ አነሳሳ፡፡ አንድ ቀን በድንገት ብድግ ብለው ሀገራቸው ጎጃም ገቡ፡፡

ሀብታሙ እናቱ ከሄዱ በኋላ የብቸኝነት ኑሮን ተጋፈጠ፡፡ አሁን ከጎኑ ማንም የለም፡፡ ዘመድ ወዳጅ ይሉትን አያውቀው ልጅ በግራ መጋባት ቀናትን ቆጠረ። ሰፈርተኛው እናት ልጃቸውን ጥለው ስለመጥፋታቸው እያነሳ አወራ፡፡ እንዲህ መሆኑ ለትንሹ ልጅ የፈየደው የለም፡፡

ሀብታሙ በችግር አለንጋ ተገረፈ፡፡ የእናት እጅ የለመደው ሆድ መራብ መጠማቱ አልቀረም፡፡ የጎረቤት እንጀራና ወጥ እየሸተተው አንገቱን ደፋ፡፡ ለአዳሩ ካንዱ ቤት አንዱ እያለ ጊዜያት አሳለፈ፡፡ እንደ ቀልድ ጊዜው ገፋ፡፡ ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ፡፡

ያልተሸነፈ ችግር …

አንድ ቀን እናት ድንገት ካገር ቤት ተመለሱ፡፡ የትንሹ ልጅ ዕንባ ታበሰ፣ ከፊቱ ደስታው ተመለሰ፡፡ በናፍቆት የከረመው ሀብታሙ ውስጡ ሲያገግም ቀን አልፈጀም፡፡ የልጅነት ወዙ ተመልሶ ፈገግታው ደመቀ። እናት ከቆዩበት ሲመለሱ መልካም አልቆያቸውም። ቀድሞ ያስጠጓቸው ሰዎች ቤት እንዲፈልጉ ገፏቸው፡፡ እናትና ልጅ ከደባል ኑሮ ወጥተው ደባል ኑሮ ውስጥ ገቡ፡፡ የአምና ካቻምናው ዓለም አልተቀየረም፡፡ በነበረበት እንደነበረ ቀጠለ ፡፡

አድካሚው ኑሮ አሰልቺ እየሆነ ነው፡፡ በየሰበቡ ከጎረቤቶች የሚጋጩት ሴት ኃይለኝነታቸውን ሀገር አውቆታል፡፡ አዲስ በገቡበት ቤት ሰላም አልተገኘም። አሁንም ልጃቸውን ይዘው እንዲወጡ ተፈረደባቸው፡፡ ሀብታሙ የእንክርት ኑሮ ውስጡን ሰበረው፡፡ ሕይወት ይሉት ጣጣ ከበደው፡፡ ከአንዱ ወደ አንዱ መመላስ ከችግር መከራ አላመደው ፡፡

1982 ዓ.ም፡፡ ይህ ጊዜ የመንግሥት ለውጥ ዋዜማ ነበር፡፡ ሀብታሙ ከወጣትነት ዕድሜ ደርሷል፡፡ እሱን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በወቅቱ ‹‹ኮርፖሬሽን›› ከሚባል ድርጅት ዳቦ እየገዙ ይሸጣሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ ለኑሯቸው በጎ ሆነ። አጋጣሚው እሱን ከሰዎች አገናኘው፡፡ ከአንድ ጋራዥ እየተከፈለው መሥራት ጀመረ ፡፡

ብርቱ እጆች …

ሀብታሙ የጋራዥ ሥራ አበረታው፡፡ ሙያ እየለመደ፣ ጉልበቱን ፈተነ፡፡ ከጎሚስታ እየዋለ የአቅሙን ታገለ፡፡ ይህ ጥረቱ ለኪሱ አላሳጣውም። እንደሌሎች ወግ ደረሰው፡፡ ለእሱና ለእናቱ ጉሮሮ ይዞ መግባትን አወቀ፡፡

1996 ዓ.ም፡፡ ሀብታሙ ዛሬን እንደትናንቱ አይደለም። ያለፈውን ችግር በጉልበቱ ድካም፣ በላቡ ወዝ ቀይሮታል። አሁን ሠርቶ ይገባል፡፡ ያለበት ዕድሜ ብርታቱ ነው፡፡ ከራስ አልፎ ለእናቱ፣ ለቤቱ ጎዶሎ ሙላት ሆነ፡፡ አንድ ቀን ሥራ ላይ ሳለ ከአንድ ሰው ጋር ተጋጨ፡፡ አብሮት የቆየ ባልንጀራው ነው፡፡

የጠቡ ሰበብ የገንዘብ ጉዳይ ነበር፡፡ የሁለቱ ጭቅጭቅ ተካሮ አንገት ለአንገት ተያያዙ፡፡ ያገላገላቸው፣ ያስማማቸው አልተገኘም፡፡ በድንገት የአንደኛው ኃይል በረታ፡፡ ላለመውደቅ እጅ ለእጅ ተጣምረው ታገሉ። ባልንጀራው ኃይሉን ተጠቅሞ የኋሊት ገፈተረው። ሀብታሙ ተደናቅፎ በጀርባው ተዘረረ፡፡ አልተነሳም፡፡ ከመሬቱ ቀድሞ ያገኘው ትልቁ የመኪና ታኮ ከወገቡ አርፎ አቅሉን አሳጣው ፡፡

ሀብታሙ ዕለቱን ለሕክምና ደረሰ፡፡ ውሎ አድሮ ግን ችግሩ ከፋበት፡፡ አከርካሪውን ያገኘው ጉዳት ወደ ነርቩ ተሻግሮ መላ ሰውነቱ ተያዘ፡፡ አድካሚው የሆስፒታል ምልልስ ያለማቋረጥ ቀጠለ፡፡ ትናንት የሚያውቁት ዛሬን ጎኑ ቆመው የቻሉትን አገዙ፡፡ እንደትናንቱ ቆሞ መራመድ አልሆነለትም፡፡

ክፉ ቀናት …

ሀብታሙ ድኖ ለመቆም በብዙ ጥረት ለፋ። የውስጡን ሕመም ታግሎም ሊራመድ ታገለ፡፡ አሁንም እንዳሰበው አልሆነም ፡፡ እግሮቹ ከክራንች ድጋፍ አላለፉም፡፡ እንዲህ መሆኑ ሥራ አስፈትቶ ከቤት አዋለው፡፡ ይህ አጋጣሚ ለጆሮው ክፉ ቃላት እያቀበለ ሆድ ያስብሰው ያዘ፡፡ የሰዎች ጨዋታና ንግግር ሁሉ ትርጉሙ ተለየበት ፡፡

ከሁሉም አንድ ቀን አንዲት ጎረቤታቸው ‹‹ጉልቻ›› ብላ ሰድባኛለች የሚልበትን ክፉ ቃልና ቀን አይረሳውም። ሴትየዋ ንግግሬ ለሌላ ነው ብትልም እሱ ግን የሀሳቧ አቅጣጫ ስለራሱ መሆኑን አምኖ ዛሬ ድረስ በዕንባ ያወሳዋል፡፡ ይህን ሲናገር በጥልቅ የኃዘን ስሜት ተውጦ ነው፡፡

ከሀብታሙ ጉዳት በኋላ የኑሮ ሸክም መልሶ በእናቱ ትከሻ ወደቀ፡፡ ደግነቱ ለዓመታት ሲጠይቁት የቆዩትን የቀበሌ ቤት አግኝተዋል፡፡ ሀብታሙ አሁን መሥራት አይችልም እሳቸው ዕድሜያቸው እየገፋ፣ አቅማቸው እየደከመ ነው፡፡ ዛሬን እንደትናንቱ ልብስ አጥበው፣ እንጀራ ጋግረው አይገቡም ፡፡

የሚኖሩበት አካባቢ በርካታ ተግባር አለው። ሮጦ የሚገባው፣ ዘርፎ የሚሮጠው፣ ተቀምጦ የሚለምነው ሲተራመስበት ይውላል፡፡ በዚህ መንደር ሕይወታቸውን በሴትኛ አዳሪነት የሚመሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ለነዚህ ሴቶች በዕለት ቤታቸውን የሚያከራዩ ነዋሪዎች የቀን ገቢ አላቸው፡፡ በእጃቸው በሚገባ ገንዘብ ቤታቸውን መርተው ልጆች ያሳድጋሉ ፡፡

የነ ሀብታሙ ቤት ዕጣ ፈንታ ከዚህ አላላፈም። ሴቶቹ ክፍሉን በፈለጉት ጊዜ አከራይተው ገንዘብ ይወስዳሉ፡፡ የእናትና ልጅ ሕይወት ለዓመታት በዚህ መንገድ ተጓዘ፡፡ በሴቶቹ የዕለት ገቢ ሕልውናቸው ቀጠለ፡፡ ሀብታሙ እግሮቹ ያለክራንች አይታገዙም። ያለሥራ መቀመጡ ሰውነቱን አግዝፎታል፡፡ አሁን አንዳንድ የቅርብ ሰዎች ሀብታሙ ትዳር ሊይዝ ይገባል እያሉ ነው ፡፡

ድንገቴ በረከት …

አንድ ቀን የሀብታሙ እናት ድንገት ተነስተው ሀገር ቤት ተጓዙ፡፡ ከቀናት በኋላ ሲመለሱ ብቻቸውን አልነበሩም፡፡ አንዲት የገጠር ልጅ አብራቸው መጥታለች። ይህች ጉብል ቀድሞ የተመከረባት፣ ለትዳር የታጨችው የሀብታሙ ሚስት ናት ፡፡

ያለአንዳች ትውውቅ በወላጆች ይሁንታ የቆመው ትዳር አራት ልጆች አፍርቶ ዓመታት ቆጠረ፡፡ ባለቤቱ ሚስትም እናትም ሆነችለት፡፡ ይህ እውነታ ግን ብቻውን በጎ አልሆነም፡፡ የኑሮ ሸክሙን ከእሷ ትከሻ አሳርፎ አንገዳገዳት፡፡ ሀብታሙ ራሱን ችሎ አለመሥራቱ ለድህነት ስር ሆኖ ቀጠለ ፡፡

ያልተራመዱ እግሮች…

ዛሬ የሀብታሙ እግሮች ከክራንች አልፈው ከዊልቸር ከዋሉ አስራ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። የትናንቱ ብርቱ አሁን አቅሙ ደክሟል፣ ምላስ አንደበቱ ተይዟል፡፡ ጎልማሳው አባወራ ሁሌም ቤተሰቦቹን እያስቸገረ መሆኑ ይሰማዋል ፡፡ በሰው እጅ መውጣት መግባት፣ መታጠብና መጸዳዳት እጅጉን ይከብዳል፡፡ በሕመሙ ሳቢያ በሚስቱ ትከሻ ማደሩ ለእሱ የዘወትር ኃዘኑ ነው፡፡

ሀብታሙ ከበሩ ደጃፍ ተቀምጦ የሞባይል ካርድ ሲሸጥ ይውላል፡፡ ከእጁ የሚገባው የካርድ ሽያጭ ኑሮን የሚለውጥ አይደለም፡፡ ማንነቱን የሚያውቁ የሰፈሩ ሰዎች ችግሩን አይተው ይገዙታል ፡፡ አንዳንዶች ቀሪውን መልስ አይቀበሉም ፡፡

ሥራን በምጽዋት…

አንዳንዴ ደግሞ ሀብታሙ ከእጁ ሲያጣ ምጽዋት ይጠይቃል፡፡ የሚያዩት የተዘረጋ እጁን አያልፉትም። የቻሉትን ይጥሉለታል፡፡ በምስጋና ተቀብሎ ለልጆቹ ዳቦ ይሰጣል፡፡ አሁን እንደቀድሞው ቤታቸው ለሴተኛ አዳሪዎች አይከራይም፡፡ ለልጆች የዕለት ጉሮሮ፣ ለአስፈላጊ ወጪዎች ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ይህን የሚያውቀው ሀብታሙ የአቅሙን እየሞከረ ሕይወትን ይታገላል፡፡ በዚህ ብቻ የኑሮ ቀዳዳ አልተደፈነም፡፡ ችግር ከሰው ፊት አቁሞታል፡ ይሉኝታውን ሰርቆበታል፡፡ የትናንት ብርቱ እጆች ለልመና ሲዘረጉ አይተዋቸውም፡፡ የተሰጠውን አመስግኖ ይቀበላል ፡፡

ሀብታሙ በሰፈሩ ዓመታትን ቆጥሯል፡፡ አንጋፋ ነዋሪ ነውና እንደሌሎች የዕድር አባል ነው፡፡ እንደወጉ ግን ወርሐዊ ክፍያ ማሟላት ተስኖታል፡፡ ችግሩን የሚያውቁ፣ የአቅሙን ማነስ የሚረዱ ወር ሲመጣ አስበው ይከፍሉለታል ፡፡

ዓውደ ዓመት ሲመጣ፣ መልካም ልብ ያላቸው ዝም አይሉትም፡፡ ሁሌም ያሰቡታል፡፡ ለልጆቹ፣ ፍላጎት ለእሱ ወግና ክብር የሚጨነቁ ሰላምታቸው ባዶ አይደለም፡፡ ትናንት ሠርተው ያደሩ እጆች ዛሬ ለልመና ተዘርግተዋል። ቀኑን ሙሉ ፀሐይ ከዝናብ ሲታገል የሚውለው አባወራ ነገ ልጆቹ ተምረው ታሪክ እንዲቀይሩ ይሻል፡፡

ያላለፈ ትናንት …

ዛሬ በነሀብታሙ ቤት ችግሩ ብዙ ነው። አራት ልጆችን መግቦ አሮጊት እናትና ባልና ሚስት፣ማስተዳደር ቀላል አልሆነም፡፡ ይህ ሁሉ ሸክም በሚስት ጫንቃ መውደቁ ደግሞ ጫናውን አክብዷል፡፡ ዕንባና ኃዘን በማያጣው ጎጆ አንዳንዴ ጦም ውሎ ማደር ብርቅ አይደለም፡፡

ዛሬም እንደ ትናንት ያላለፈው ችግር መላው ቤተሰብን እየፈተነ ነው፡፡ ባዶውን የቀየረ እጅ፣ ረሀብ የፈተነው ሆድ፣ ተስፋ የለሽ ዓይኖች የሌሎችን እገዛ ይናፍቃሉ፡፡ የመልካም እጆች በረከት፣ የቅን ሰዎች ልቦና መፍትሔ ቢሆናቸው፡፡

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You