መንግሥት ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ አድርጓል

 አዲስ አበባ፦ በ2016 የመጀመሪያው የሩብ ዓመት በታለመለት የነዳጅ ድጎማ መንግሥት ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ብሔራዊ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰልማን መሀመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ በ2014 ሐምሌ ወር ተግባራዊ የተደረገ ሥርዓት ነው። በ2016 የመጀመሪያው የሩብ ዓመትም በታለመለት የነዳጅ ድጎማ መንግሥት ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጓል፡፡

የታለመለት ነዳጅ ድጎማ በ2014 ሐምሌ ወር ተግባራዊ ከተደረገበት ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ23 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪዎች ድጎማ መደረጉን አመልክተው፤ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪዎች ድጎማ መደረጉን አቶ ሰልማን ተናግረዋል።

መንግሥት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን በመለየት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አድርጓል ብለዋል።

እንደ አቶ ሰልማን ገለፃ፤ በድጎማ ሥርዓቱ የሚካተቱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የነዳጅ ድጎማ ሥርዓቱ ከተዘረጋ አንስቶ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 240 ሺህ 890 ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ ገብተዋል። በሩብ ዓመቱ ዘጠኝ ሺህ 872 ተሽከርካሪዎች ለድጎማ ተመዝግበዋል።

በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ከተሞች ተሽከርካሪዎች በሥርዓቱ እንዲመዘገቡ ተደርጓል ያሉት አቶ ሰልማን፤ በአጠቃላይ ከተመዘገቡት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 197 ሺህ 454 የሚሆኑት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህ ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች በሩብ ዓመቱ የድጎማ ተጠቃሚ የተደረጉ ናቸው ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ መረጃዎችን በመስጠት በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት በኩል ምዝገባ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በዚህም እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ81 ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You