ለተሰንበት ግደይ ለስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ታጭታለች

የየትኛውም ውድድር መሠረትና ትልቅ ዋጋ ስፖርታዊ ጨዋነት ነው። ያለ ስፖርታዊ ጨዋነት ስፖርት ሊኖር አይችልም። ስፖርት ከአሸናፊና ተሸናፊነት ይልቅ አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና መከባበር ቅድሚያ የሚሰጣቸው መርሆቹ ናቸው። በዚህ ምክንያትም ነው በየትኛውም ስፖርታዊ ውድድር ለሰብዓዊነትና ለመልካምነት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው። የስፖርት ባለሙያዎች በየስፖርታዊ እንቅስቃሴና ክንዋኔ፤ ከአሸናፊነትም ጭምር ቀዳሚ የሚሆነው ስፖርታዊ ጨዋነት መሆኑን ያስቀምጣሉ። ለዚህም ነው ውድድሮች ላይ ስፖርታዊ ጨዋነት የራሱ ዋጋ ኖሮት የሚያሸልመው። በአንጻሩ ስፖርታዊ ጨዋነትን ያላከበረ ደግሞ መቀጣቱ የማይቀር ነው።

የትኛውም ድንቅ ብቃት ከስፖርታዊ ጨዋነት ሊበልጥ አይችልም፤ ጨዋታ አሊያም ውድድር ምርጥ ሊባል የሚችለው ሰላማዊ ድባብ ሲኖረው ነው። አንድ አትሌት አሊያም በየትኛውም ስፖርት ውስጥ ያለ ተወዳዳሪ ምንም እንኳ በልዩነት አሸናፊ ቢሆንና ክብረወሰኖችን መደርደር ቢችል በውድድር ወቅት ያሳይ የነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት ባህሪ ከፍተኛ ሚና አለው። በውድድር ወቅት ምንም እንኳን ስህተትን ባይፈጸምም ተቃራኒ ተወዳዳሪ ለሚደርስበት አደጋም ሆነ መሰል ጉዳይ አዎንታዊ አጸፋ መስጠትና ወዳጅነትን ማሳየትም የስፖርታዊ ጨዋነት ማሳያ ነው። ተሸናፊነትን በጸጋ መቀበልና ለአሸናፊው አካል ዕውቅና መስጠትም ከመገለጫዎቹ መካከል አንዱ ነው።

ከወራት በፊት በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የመክፈቻ እለት ከተከናወኑ የፍጻሜ ውድድሮች መካከል አንዱ በነበረው 10ሺ ሜትር የሴቶች ሩጫ መጨረሻ የተፈጠረው ድራማዊ ክስተት አይዘነጋም:: በውድድሩ የመጨረሻ ዙር ፍልሚያ በዜግነት ኔርላንዳዊት በትውልድ ደግሞ ኢትዮጵያዊት የሆነችው አትሌት ሲፈን ሃሰን በአሸናፊነት የርቀቱን የመጨረሻ መስመር ለመርገጥ በምትጣጣርበት ወቅት ድንገት የመውደቅ አደጋ ደረሰባት።

ኢትዮጵያዊያኑ ተፎካካሪ አትሌቶችም ከወርቅ እስከ ነሃስ ያሉትን ሜዳሊያዎች ለማጥለቅ ቻሉ። ነገር ግን አሸናፊነታቸውን ከማጣጣም ይልቅ በመውደቅ ከሜዳሊያ ውጭ የሆነችውን ተፎካካሪ አትሌት ተመልሰው በማቀፍ ፍጹም የሆነ የወዳጅነት ስሜታቸውን አንጸባርቀውላታል። በውድድሩ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ያሳየችው ስፖርታዊ ጨዋነት ደግሞ የተለየና ፍፁም ሰብዓዊነትን ያስመሰከረ ነበር። ለተሰንበት የተፎካካሪዋ ሲፈንን ጉዳት እየተመለከተች በማዘን ስታፅናናት የነበረው ስሜት የዓለምን ሕዝብ ያስደነቀ ነበር።በበርካቶች ዘንድም የለተሰንበት ስፖርታዊ ጨዋነት አድናቆትን አትርፏል።

ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት እንዲሁም እንደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያሉ ስፖርትን የሚመሩ ተቋማትም ስፖርታዊ ጨዋነት የውድድር ፍሬ ነገር መሆኑን በደንቦቻቸው ያካትታሉ። ከዚህ ባለፈ ዓለም አቀፉ የስፖርታዊ ጨዋነት ኮሚቴ መቋቋምም ጉዳዩ ያለውን ስፍራ የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ማህበራቱ በሚያዘጋጇቸው የስፖርታዊ ሽልማት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ምስጉን በሆነ ባህሪ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተግባር ያሳዩ ስፖርተኞችን ያካትታሉ። በቀጣዩ ወር በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመቱ ምርጥ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን ሊሸልም በማወዳደር ላይ ያለው የዓለም አትሌቲክስም ከሽልማት ዘርፎቹ መካከል ስፖርታዊ ጨዋነትን አካቷል።

በዚህ ዘርፍ ሊሸለሙ ይገባቸዋል ያላቸውን አትሌቶችንም በዝርዝር ያሳወቀ ሲሆን፤ የስፖርት ቤተሰቡን ድምጽ በማህበራዊ ድረ ገጾች በማሰባሰብ ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት ሁለት ሴት አትሌቶቿ በምርጥ ብቃታቸው እጩ የሆኑላት ኢትዮጵያ በስፖርታዊ ጨዋነት ዘርፍም ምርጧ አትሌት ከዝርዝሩ ውስጥ መካተቷ ተረጋግጧል። ከላይ እንደተገለጸው ተፎካካሪዋን በመደገፍ እንዲሁም አብሮነቷንና ለማሳየት ባደረገችው ጥረትም በዓመቱ በአትሌቲክስ ስፖርት ከታዩ ስፖርታዊ ጨዋነቶች አንዱ እንደሆነ ስለታመነበት በእጩነት መቅረብ ችላለች። ከቀረቡት ስድስት እጩዎች መካከልም ኢትዮጵያዊቷ ለተስንበት በቀዳሚነት የመመረጥ እድሏ የሰፋ እንደሚሆን ይገመታል።

በውድድሩ ወቅት ወድቃ ከሜዳሊያ ተፎካካሪነት ውጭ የሆነችው አትሌት ሲፈን ሃሰንም እንደ ለተሰንበት ሁሉ በእጩነት ልትቀርብ ችላለች። በወቅቱ የሆነውን ድንገተኛ ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በማየት እንዲሁም መሸነፏንም አምና በጸጋ መቀበሏም ነው ለእጩነት ያበቃት። ከቀናት በኋላም በሁሉም የሽልማት ዘርፎች የተሻለ ድምጽ በማግኘት ለፍጻሜው ውድድር ብቁ የሆኑ አትሌቶች የሚታወቁ ይሆናል። በመጪው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ደግሞ ሞናኮ ላይ በሚኖረው የሽልማት ሥነ ሥርዓት አሸናፊዎቹ ይፋ ይሆናሉ።

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You