ወጣት ላይሽ ደረስ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ናት። በከበሩ ማዕድናት ቆረጣና ማስዋብ ሥራ ከተሰማራች ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል። በሥራው ለመሰማራት ካነሳሷት ምክንያቶች አንዱ በአካባቢዋ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት እሴት ሲጨመርባቸው መዳረሻቸው ባህር ማዶ መሆኑ ነው። የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር በዘርፉ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ውጤታማ አምራቾችን መመልከቷም ሌላኛው ምክንያቷ ነው። ይህን የአካባቢዋን የማዕድን ሀብት ተጠቅማ ውጤታማ ለመሆን በመነሳሳት ወደ ሥራው ገብታለች።
ወጣት ላይሽ እንደምትለው፤ የከበሩ ማዕድናት ምርቶች በአማራ ክልል ወሎ ደላንታ፣ በበለሳ፣ በጋይንት እና በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በብዛት ይገኛሉ።ኦፓል፣ አጌት፣ ሞሳአጌት፣ ጃስፐር፣ ሳፋየር እና የመሳሰሉት በርካታ የማዕድን ዓይነቶች በክልሉ በስፋት ይገኛሉ። ከእነዚህ የከበሩ ማዕድናት ብዙ ዓይነት ምርቶችን ማምረት ይቻላል፡፡
ወጣት ላይሽ ቀደም ሲል ከሌሎች ሰዎች ጋር በማህበር ተደራጅታ ስትሰራ የቆየች ቢሆንም፣ በወቅቱ የነበሩት የማህበሩ አባላት ሥራውን ሲለቁ በግል አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥታ ይህንኑ ሥራ እየሰራች ትገኛለች።እስካሁንም የምታመርታቸውን የከበሩ ድንጋዮች ወይም ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበች ነው፡፡
ባለፉት ጊዜያት በተለይ ከአምስት ዓመት በፊት የከበሩ ድንጋዮች ስላልተለመዱ ማንም አይገዛቸውም ነበር የምትለው ላይሽ፤ እያደር እየተለመዱ በመምጣታቸው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በገበያ ደረጃም ጥሩ የሚባል ገበያ እያገኙ መሆኑን ትገልጻለች።ከዚህ ቀደም ማዕድናቱ በአዲስ አበባ ከተማ በባዛር እና በኢግዚቢሽን ሲቀርቡ የሚሸመቱት አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ እንደነበሩ አስታውሳ፤ አሁን ላይ የገበያ አድማሱ እየሰፋ በክልሎች ደረጃ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ገበያ እያገኙ መምጣታቸውን ትናገራለች፡፡
እሷ እንደምትለው፤ የከበሩ ድንጋዮች በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ስላሉ በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም፤ ማዕድናቱን ለማግኘት ትልቁ ሥራ ያለው ማዕድን አምራቾች ዘንድ ነው። ወጣት ላይሽ ድንጋዮቹን ከአምራቾቹ በመረከብ እሴት ጨምራ አስውባና አስጊጣ ለገበያ ታቀርባለች።
በከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጦችን አምርታ ለገበያ የምታቀርበው ላይሽ፤ ጌጣጌጦቹ ለአንገት፣ ለጆሮ፣ ለእጅና ለተለያዩ አካላት ማጌጫነት እንደሚውሉ ትናገራለች። እሷ እንዳለችው ከከበሩ ማዕድናት የማይሰራ ነገር የለም።በማዕድናቱ እንደ ቀለበት፣ ማንኪያ፣ የቁልፍ መያዣ፣ የኢትዮጵያ ካርታ እና መስል ሌሎችንም ብዙ ዓይነት ነገሮችን መሥራት እንደሚቻል አብራርታለች፡፡
ምርቶቿን ባህር ዳር በሚገኘው መሸጫ ሱቅ እንደምትሸጥ የምትናገረው ላይሽ፤ አብዛኞቹ ምርቶቿን አዲስ አበባ ለሚገኙ ተረካቢዎች ትልካለች።ከገበያ አንጻርም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ተጠቃሚዎች ምርቱን እየሸመቱ ናቸው፤ ይህም ገበያው እየተሻሻለ ለመምጣቱ አንድ ማሳያ ነው ትላለች።በመንግሥት በኩል የሚቀር ሥራ ቢኖርም አሁን ላይ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ጥሩ የሚባል እንደሆነ ነው የገለጸችው።አነስተኛና ጥቃቅን ቢሮዎች ትኩረት ሰጥተው ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉም አመላክታለች።
በከበሩ ድንጋዮች በመጠቀም ረገድ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ የምትናገረው ላይሽ፤ ብዙ ጊዜ የተለመደው ፕላስቲክ እና ብልጭልጭ ነገሮች በመጠቀም ማጌጥ እንደሆነ ትናገራለች።የከበሩ ድንጋዮች ሲባል በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ በጣም ውድ አድርጎና አግዝፎ የመመልከት ሁኔታ የሚስተዋል መሆኑን የገለጸችው ላይሽ፤ ማንኛውም ሰው እነዚህን የከበሩ ድንጋዮች በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ ሊያጌጥባቸውና ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ጠቅሳ፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን አሁን ግንዛቤው እያደገ ስለመምጣቱና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች እየመጡ እንደሆነ ትናገራለች። የከበሩ ድንጋዮችም እሴት ተጨምሮባቸው ውብ ሆነው የሚዘጋጁ እንደሆነም ተናግራለች፡፡
ከዚህ ቀደም ከከበሩ ድንጋዮች የሚመረተው ኦፓል ብቻ እንደነበር ጠቅሳ፣ ይህም እንደ ጥራቱ ዓይነት ዋጋው ውድ እንደነበር ታስታውሳለች፤ ይህም ሰዎች ጌጣጌጡን እንዳይጠቀሙት አድርጓቸዋል። አሁን ላይ የከበሩ የድንጋይ ዓይነቶች የተለያዩ እንደሆኑ ገልጻ፤ የከበሩ ድንጋዮቹ ከሦስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ብር እንደሚሸጥ ጠቁማለች።እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ማንኛውንም ማህበረሰብ ያማከሉ ስለሆኑ ሁሉም ሰው ገዝቶ መጠቀም እንደሚችልም ገልጻለች።
ቀደም ሲል በዚህ ሥራ ላይ በርካታ ሕገወጦች ይሰማሩ እንደነበርም ጠቅሳ.፣ ይህም ወደ ሥራው ለመግባት ለሚፈልጉ ሰዎች ስጋት ሆኖ መቆየቱን ገልጻለች።በአሁን ወቅት በማዕድን ሥራ ላይ ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው ለሚሰሩ አካላት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንና ሕገወጥነት እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁማለች።ለዚህም ‹‹ሜዳ›› የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት በዘርፉ የተሰማሩ ፈቃድ ያላቸው ሕጋዊ አካላትን በማስልጠን ሙያው መስመር እንዲይዝና በሥርዓት እንዲመራ እያደረገ መሆኑን ጠቅሳ፤ አሁን ወደ ዘርፉ ገብቶ መስማራት ለሚፈልግ ማንኛውም አካል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያመላከተችው።በመሆኑም በዘርፉ ይስተዋል የነበረው ሕገ ወጥነት መቀነስ ችሏል፡፡
‹ሜዳ› የተሰኘው ድርጅት በሙያ ረገድ ተከታታይነት ያላቸውን ስልጠናዎች በመስጠት፣ የማሽን ድጋፍ፣ ባዛርና ኢግዚቢሽን ላይ ወጪን ሸፈኖ እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲሁም መሰል ሥራዎችን ስለሚሰራ አብዛኛው በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት በድርጅቱ የታቀፉ እንዲሆኑ አድርጓል ትላለች።
ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው መሥራት ያስፈልጋል የምትለው ላይሽ፤ በተለይም ወደዚህ ሥራ የሚገቡ፤ በጥቃቅን ያልተደራጁ አምራቾችን መደገፍ አስፈላጊ ነው ብላለች። እሷ በግሏ አሁን ላይ ለሦስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለች ሲሆን፤ በቀጣይ ያላትን ካፒታል አጠራቅማ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ አላት።
ነዋሪነቷን ወልዲያ አካባቢ ያደረገችው ወጣት ሃይማኖት ጉማታው በተመሳሳይ በከበሩ ማዕድናት የጌጣጌጥ ሥራ የተሰማራችው ወጣት ናት። ወጣቷ የከበሩ ድንጋዮችን በማስዋብና ማስጌጥ ሥራ ላይ ከተሰማራች አምስት ዓመታትን ያህል አስቆጥራለች። ወጣት ሃይማ ኖት እነዚህን የከበሩ ድንጋዩች በቅርበት ከአካባቢዋ ታገኛለች፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችም ማዕድናቱን ታስመጣለች። አብዛኞቹን የከበሩ ማዕድናት ግን ከአማራ ክልል ሰቆጣ እና ደላንታ አካባቢዎች እንደምታገኛቸው ትናገራለች፡፡
የተለያዩ ማዕድናት፣ በብዛት ጠንካራ ድንጋዮችን እና ኦፓል በተሰኙ የከበሩ ድንጋዮች ላይ ትኩረት አድርጋ በማስዋብ ለገበያ እንደምታቀርብ የምትናገረው ሃይማኖት፤ እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ብዙ እንደማያስወጡም ነው የምትገልጸው፤ የሰውን ኪስ በማይጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ሰርታ ለሽያጭ ታቀርባለች። እሴት ጨምራ በማስዋብ የከበሩ ድንጋዮች ለሀገር ውስጥ ገበያ እንደምትቀርብ ጠቅሳ፣ የገበያ መዳረሻዎቿ በአብዛኛው አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ገዢዎች እንደሆኑ ትገልጻለች።
የገበያ ሁኔታውን አስመልክታም ህብረተሰቡ ለጌጣጌጥ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ነው። ‹‹ህብረተሰቡ እነዚህን የከበሩ ማዕድናት ከመግዛት ይልቅ ወርቅ መግዛት ይመርጣል።ከወርቅም የሚበልጥ ማዕድን እንዳለ ሰው አይረዳም፤ እውቀቱም የለውም›› በማለት ገልጻለች።
ለገበያ የሚቀርበው እሴት የተጨመረበት ማዕድን በሀገር ውስጥ ገበያ ሲሸጥ ካለው ዋጋ ዝቅ እንዲል ተደርጎ ነው የምትለው ሃይማኖት፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ህብረተሰቡ ገዝቶ መጠቀም እንዲችል እግረ መንገዱንም እንዲያውቀውና ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም ትናገራለች። በተለይ በሀገር ውስጥ እነዚህ ማዕድናት በደንብ አይታወቁም፤ ሸማቹ ጠይቆ አውቆ ሲረዳቸው ግን ለመግዛት ወደኋላ አይልም፤ ለራሱ ለማጌጥም ሆነ ለስጦታ እና ለመሰል አገልግሎቶች ገዝቶ ይጠቀማል ትላለች።
ማዕድናቱ ላይ እሴት የመጨመር ሂደት እጅግ ልፋትን የሚጠይቅና አድካሚ ሥራ መሆኑን ትገልጻለች። አሁን ኦፓል ቀለበት ስድስት ሺ ብር እና ከዚያ በላይ እንደ ኦፓሉ ዓይነት እንደሚሸጥም ነው የጠቆመችው።ነጭ ቤዝና ብላክ ቤዝ የሚባሉ ኦፓሎች ዋጋቸው እስከ 12 ሺ ብር እንደሚደርስም ትናገራለች። ከ800 እስከ አንድ ሺ 500 ብር ድረስ ዋጋ ተመን ያላቸው የከበሩ ድንጋዮች እንዳሉ ትጠቁማለች። አሁን ካለው ገበያ ሁኔታ አንጻር ለገበያ ማቅረብ ብዙም ትርፋማ እንደማያደርግም ጠቅሳ፣ ወደፊት ህብረተሰቡ ዘርፉን በደንብ ሲያውቅ የሚመጣውን ለውጥ በማሰብ እየሰራች መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይ እሴት ጨምራ የምታመርታቸውን የከበሩ ማዕድናት ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለትም ገልጻለች፡፡
ሃይማኖት፤ ማዕድን ላይ እሴት የመጨመሩን ሥራ የጀመረችው በማህበር ተደራጅታ ትሰራ በነበረበት ወቅት ነው።በዘርፉ ተሰማርቶ መስራት በርካታ ፈተናዎች ማለፍን እንደሚጠይቅ ጠቅሳ፣ ሌሎች ጓደኞቿ ሥራውን ሲተውት እሷ ግን ብቻዋን ፈቃድ አውጥታ መስራት ቀጥላለች።በዘርፉ ላይ ለተሰማሩ አካላት ስልጠና በመስጠት፣ የፋይናንስ እና ማሽን ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የገበያ ትስስር በማመቻቸት ሰፊ እድል በመፍጠር ድጋፍ እያደረገ ያለው ‹‹ሜዳ›› የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለእሷም ድጋፍ ማድረጉን ገልጻለች፡፡
እስካሁን በዘርፉ ብዙ እንዳልተሰራበት ሃይማኖት ጠቁማ፣ ዘርፉ ብዙ ሥራዎችን እንደሚጠይቅ ነው ያመለከተችው። ባለሙያው የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን መሥራት እንዳለበት ትጠቁማለች። ማዕድን ሀገር መለወጥ የሚችል ሀብት መሆኑን ጠቅሳ፣ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተደርጎበት እንዲሰራበትም ጠይቃለች።
ዘርፉ ሕገ ወጥነት የተጋለጠ መሆኑን ሃይማኖትም አረጋግጣለች። አምራቹ የሚገባውን ጥቅም ሳይገኝ ሕገ ወጦች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ትናገራለች። ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ቢወጣ እና እነዚህ ማዕድናት በሕገ ወጥ መንገድ በሚያስተላልፉ አካላት ላይ ከባለሙያው ጀምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቁጥጥር ቢያደርጉ ሕገ ወጥነትን በመቀነስ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል ብላለች።
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው በክልሉ የከበሩ ማዕድናት በአብዛኛው በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን እንደሚገኙ ይናገራሉ።የከበሩ ማዕድናት በተለይ በኦፓል ማዕድን ልማት ላይ ለ69 አምራች ኢንተርፕራይዞች ፍቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል።ኢንተርፕራይዞቹ ኦፓል እያመረቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆ ኑንም ይገልጻሉ።
ከእነዚህ በተጨማሪም በከበሩ ማዕድናት እሴት ጭመራ ወይም ፕሮሰሲንግ ላይ ተሰማርተው እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾች እንዳሉ አቶ ታምራት ይናገራሉ።በ2016 በጀት ዓመት ለ30 አምራቾች የከበሩ ማዕድናት እደ ጥበብ ብቃት ለመስጠት ታቅዶ፤ ለሦስት አምራቾች ፍቃድ መስጠቱን ነው የተናገሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ በማዕድን ዘርፉ ላይ እነዚህ አምራች ኢንተርፕራይዞች ሕገ ወጥነት ችግር እየፈጠረባቸው ይገኛሉ።በተለያዩ ቦታዎች ሕገ ወጥ የሆኑ የማዕድናት ዝውውር ይስተዋላል።ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው ማዕድን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያዘዋውሩ፣ የሚሸጡ፤ የሚገዙ አካላት እየተበራከቱ ይገኛሉ።እነዚህ አካላት ሕጋዊ መስመር ተከትለው የሚሰሩ ወጣቶችንም ሆነ ባለሀብቶችን ከመጥቀም ይልቅ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ በአቋራጭ ማዕድን ለመውሰድ የመፈለጉ አዝማሚያ የሚታይ ባቸው አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል።
እንደ ክልል ይህን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ሁለት መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል።ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት የሚከላከል ግብረ ኃይል በክልሉ ተቋቁሟል።ይህ ኃይል ከተለያዩ አጋር አካላት ከፖሊስ፣ ከፍትሐና ከሰላም ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት ኬላ በማቋቋምና ፍተሻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ በዚህም በየወረዳውና በየቀበሌው የሚዘዋወሩ ሕገ ወጥ የማዕድናት አዘዋዋሪዎችን የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። ሕገ ወጥነትን የመቆጣጠርና የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ሌላኛው የሚነሳው ጉዳይ የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት አምራቾች ምርታቸውን መሸጥ አለመቻላቸው ነው የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የከበሩ ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የገበያ ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።ክልሉ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ከማዕድን ሀብት ተጠቃሚ ለመሆን የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ የሚያስቀጥል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም